/

ግጥም: አንድነት | ዳንኤል ጎበዜ ዘ-ጎንደር


አንድነት

የኢትዮጵያ ትግል ገድል አንሳፎ የሚጥል ጅረት፣
የስደት ማቆሚያዉ ተዉኔት የኢትዮጵያ ዉዳሴ የነጻነት ማህሌት፤
የትብብር መገለጫ የጭቁኖች አንደበት።
የሃይላችን መደብር የህዝብ ዝሃ መዘዉር፣
ከዚያም ከዚህ ድር ሲያብር የጠላት ነብስ የሚሰዉር፣
ወልጋዳ ስርዓት የሚሰብር።
የዲሞክራሲ ዉጋግራ ፤ለተከፉት መከታ የፍትሕ የቤት ጣራ፣
የቆራጥ ጀግና አዝመራ ለተራቡት ጎተራ፣
በጎንደሩ ጋራ ሸንተረር በጎጃም አባይ ጎራ፣
በወልድያ፤ ቆቦ/መርሳ ሸንተረር በማይጨዉ ተራራ፣
በመዲናዉ የትግል ችቦ እያበራ ሃረር ወለጋ ሲጣራ፣
ለዘረኞች አንጀት ቆራጭ ለጨቋኖች ደብተራ፣
በሩቁ የሚሰማ ለጠላት የሚያስፈራ፣
ለኢትዮጵያ የድል ጎራ ለታጋዮች ከዘራ፣
ለወልቃይት ለጠገዴ በሁመራ ጎንደር ጎራ
ይዘምራል ጀግናዉ አስመላሽ ትዉልድ በተከዜ የጎንደር ወንዝ በራስ ደጀን ተራራ።

አንድነት

የኛ ወሎ ኬኛዉ አምቦ በህብረቱ ሲስማማ
ሆ! ብሎ ሲጓዝ በለቀምቶች በነመቱ ከተማ
በነጻነት ጃን ሜዳ በጀግና መንደር አዳማ
የሰይጣን ባንዲራ አዉርዶ ይሠቅላል ሰንደቅ ዓላማ፣
ከጎንደር እስከ ቦረና በነካሣ መሃል አገር በነባልቻ ከተማ።

አንድነት
የፍቅር ጽዋ አቃማሽ የድል ጃኖ አላባሽ፣
የህዝብ መብትን አዉራሽ የዘረኞች ምኞት አፍራሽ፣
ለተበደሉት ፈጥኖ ደራሽ፤ የሕዝብ መብት አስመላሽ።
አንድነት
ተሞሻሪ ጮሌወችን አስወግዶ፤የበዝባዥ ጭልፊቶችን በወስፈንጠር ቀይዶ፣
የጠላት ቁራን አሳዶ፤ የጠነዛዉን ስርዓት አቆራፍዶ፣
በምጽዓት ተጸንሶ ጀግና በምጥ ተወልዶ፣
የሕዝባዊ ሕብረት ሥር ሰዶ ፍትህ ያነግሳል ጨቋኙን ሥርዓት ንዶ።
አንድነት
የዜግነት ትርጓሜ የመብት ጠበቃነት ፤የህዝብ ስልጣን አጋርነት፣
የትግላችን ኃዋሪያ የድላችን ሰላም እረፍት፣
የጥንት አባቶች ቅኝት የናቶቻችን ሥሪት፣
ታላቅ ኢትዮጵያዊነት የነፃነቱ ጉልበት፣
ክቡር አፍሪካዊነት የጥቁር አራያነት፣
የነሉሲ ተወላጆች የትዉልድ ሃረግ ባለቤት፣
የዓለም ዘር ሁሉ መነሻ የጽዮን ማረፊያ ቤት።
አንድነት
የጡንቻችን ፍርጣሜ የጉግ ማንጉግ ስያሜ፣
ለሴረኞች የሞት መርዶ የቀብራቸዉ ፍጻሜ፣
የድል ዋዜማ ምሸት ጎህ የሚያበራዉ ዝማሜ
የጀግና ትዉልድ ማማ በቃኝ ብሎ ቅዋሜ።
አንድነት
የትግል አቡጊዳ የዜግነት መከዳ፣
የትብብር ናኩተከ የድርጅቶች አኮፋዳ፣
በአዲስ ትዉልድ አሃዱነት ጠላትን የሚነዳ፣
አስተማማኝ የትግል ሜዳ የዉይይት ሰሌዳ፣
ለጭቁኖች መዘዉር ለገዳዮች የሞት ፍዳ።
የህዝብ አመጽ ስይመት አርማ አንጋቢ በህዝብ እምነት፣
የቆራጥ ትዉልድ እድመት የጀግና ልጆች ዋቢነት፣
ለተማመኑ ዝክረት ለከፋፋዮች ሹም ሽረት፣
ለጠባቦች እፍረት ለካሃዲወች ዉርደት፤ ለተገፋዉ ህዝብ ድፍረት፣
ለታሪክ ማህደር እዉነት ለአምባ ገነኖች ሃፍረት።
የመልካችን ወርቀ ማህለቅ፤የሃይማኖት መቻቻል የጋራ ኑሮ ሰንደቅ፣
ወገን ሲደነቅ መሰሪ ጠላት ሲጨነቅ፣
አምባገነን ሲብረከረክ የዉስጥ ሴረኛ ሲንበጫረቅ፣
ባጉል ስራዉ ሲሸማቀቅ በጀግናዉ ህዝባችን ሲጨፈለቅ፣
ሳይወድ በግድ ስልጣን ሲለቅ፣
ዘረኛ ሃጣን በዲያብሎስ ሲነጠቅ፤ጀግናዉ አርበኛዉ ሲጸድቅ።
አንድነት
የፍቅራችን ሰንሰለት የህዝባዊ ትግል ስምረት፣
የዉድ ኢትዮጵያ ጸሎት፤ የጥንት አባቶች ዉርሰት፣
የዳር ድንበር አለኝታ የታሪክ ምስክርነት፣
ለጭቁኖች አንደበት ለተሰዉት ህያዉነት።
ከቀይ ባህር እስከ ቦረና ፤ከሃረር እንዳባጉና ፤
እስከ አፋር የሱልጣን ዝና፣
ከራስ ደጀን እስከ ሁመራ ከዋልድባ እስከ ብቸና፣
በነዘራይ የጀብድ ዝና በነ አባ ጅፋር ጎዳና፣
በነካሳ ቆራጥ ፈለግ በነሣህለ የጦር ጀግና፣
በነባልቻ የድል ዜና በነ በላይ አባይ ጣና፣
ኢትዮጵያችን ኢትዮጵያ ሁና የአፍሪካ ክብር ቀስተ ደመና፣
በነኩሽ ቅዱስ መሬት በኖህ ዘመን መዲና፣
በፋሲሎቹ አባ ጃሌ በነጣይቱ የሴት ጀግና
አገራችን ነጻ አዉጥተን በሰላም መኖር በጤና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፕሬዝደንት ኢሳያስ ከዕይታ መሰወር ምክንያት ምን ይሆን?

ቅኔ
ያልጠቀመን እድገት ከምን የመጣ ነዉ፤
ለማ የምንለዉ መብት ሲከበር ነዉ፤
አብይ አላማችን እስከ ነጻነት ነዉ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ
ዳንኤል ጎበዜ ዘ-ጎንደር