ሰብአዊ መብት እና ፍትህ ለኢትዮጵያ!!! – ከተማ ዋቅጅራ


ሰብአዊ መብትና ፍትህ ለኢትዮጵያ በሚል ርእሰ ጉዳይ ለይ የአውሮፓ ግብረ ኃይል ዲሰንበርሽ 9 እና 10 German- Frankfurt ከተማ ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ለይ ብዙ ሙሁራን እና የፖለቲካ አክቲቪስቶችን በመጋበዝ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እና ወደፊት መሆን በሚገባው ነገሮች ላይ ሰፊ ዳሰሳ ተደርገዋል። ተጋባዝ እንግዶቹ በተሰጣቸው ርእሰ ጉዳይ ሰፋ ባለ መልኩ በጽሁፍ ደረጃ በማዘጋጀት ብዙ የሚያወያይ እና ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሱ ሃሳቦችን በመድረኩ ላይ ማቅረብ ቢችሉም ከተጋባዝ ተናጋሪዎች መብዛት የተነሳ የተሰጣቸው ደቂቃ በጣም አጭር ስለነበረ የተዘጋጁበትን ጽሁፍም ሆነ ከህዝቡ ሊቀርብላቸው የነበረውን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ አልተቻለም ነበረ። ሙሁራኖቹ እና አክቲቪስቶቹ ያቀረቡት ነገር ጥሩ ነበር ህዝቡም ጠንካራና በሳል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ተጋባዝ እንግዶቹ የተዘጋጁበትን ጽሁፍ አንብቦ ከመድረኩ መውረድ ብቻ ሳይሆን ከህዝቡ ለሚቀርብባቸው አንከር ያሉ ጥያቄዎች መልስም መስጠት ነበረባቸው። የፕሮግራሙ ይዘት ጥሩ የሚባል ነበረ እንደነዚህ አይነት አገራዊ ጉዳዮችን በስፋት የሚዳስስ መድረክ በስፋት ቢዘጋጁ መልካም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።

ምስጋና!
አባይ ሚዲያ ከጅምሩ ጀምሮ እስከፍጻሜው ድረስ  የተላለፉትን ዝግጅቶች  በቀጥታ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ በማስተላለፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ላቀርብ እወዳለው።

ለአውሮፖ ግብረ ኃይል አዘጋጆች ጥሩ የሚያስብል ፕሮግራም በመቅረጽ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አደገኛነቱን በመረዳት ወቅቱን ያገናዘበ ጉዳዮችን ሙሁራንንና የፖለቲካ አክቲቪስቶችን በመጋበዝ ጥሩ መልእክቶችን እንድንሰማ  በማድረግ እና የትግል እንቅስቃሴዎች እና የለውጥ አቅጣጫዎችን እንዲቃኙ በማድረግ ስላደረጋችሁት ጠንካራ እንቅስቃሴ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው።

“የመድኃኒት ጣፋጭ የለውም እየመረረህ ትውጠዋለህ” ከመድረኩ ከተነገረ የተወሰደ ቃል ነው።
ይህ ቃልን የወሰድኩት ከሙሁራኑ እና ከአክቲቪስቶች የተነሱ ሃሳቦች የተለያየ ትንታኔ እና የተለያየ አተያየት ወይም አመለካከት የነበራቸው ነበሩ። በወቅቱ ከሙሁራኑም ይሁን ከአክቲቪስቶች በተላለፈው መልእክ በጣም የመረረው አለ ወይንም በመካከለኛ የመረረው አለ አልያም ደግሞ ያልመረረው አለ።  ተናጋሪው  ሲናገር የሚከታተለው ህዝብ ውስጥ እነዚህ ሶስት ነገሮች ይከናወናሉ። ቁም ነገሩ ግን እየመረረንም መዋጥ አለብን። የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲድን ከፈለግን የሁሉንም ሃሳብ መስማትና የምንስማማበትንም ሆነ የማንስማማበት ሃሳብ ለይ መልስ መስጠት መልካም ነው ግን ደግሞ የሃሳብ ልዩነትን ቢመረንም ተቀብለን መዋጥ አለብን። ይሄ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መድኃኒት ነውና።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለታማኝ ሚዲያ ታማኝ አምባሳደር

ሌላው ለፖለቲካ ትርፍ ተብሎ የሚሰሩ አደገኛ ስህተቶች ምንም የማያውቀው እና በሰላም በአገሩ መኖር የሚፈልገው የኢያትዮጵያ ህዝብ በማያውቀውና ባልሰራው ስራ ከፍተኛ አደጋ እየደረሰበት ይገኛል። ለምሳሌ ህዝብን እንደጠላት አድርጎ ለትግል መነሳት፣ ሃይማኖትን እንደ ጨቋኝ መደብ አድርጎ ቅስቀሳዎችን ማድረግ፣ እውነተኛ ታሪክን አዛብቶ የፈጠራ ታሪክን በመንገር ህዝብና ህዝብን ሊያቃርኑ የሚችል ነገሮችን መስራት በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለመደ ሆኗል።

ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ በጣም ስላስገረመኝ ነው በስም ደረጃ ጠቅሼ ማንሳት የፈለኩት።
አንድ ጠያቁ ከመድረክ እንዲህ በማለት ይጠይቃል፦ እርሶ ይላል ጥያቄውን ሲጀምር ዶክተር አረጋዊን ማለቱ ነው እርሶ የህወአት መስራች ኖት ህወአት ገና ሲመሰረት ከአመሰራረቱ የአማራን ህዝብ እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለማጥፋት እንደሆነ በማኒፌስቷቹህ እና በህወአት ቀደምት ታጋዮች ተነግሮናል አማራውንና ኦርቶዶክስን አከርካሪውን ሰብረነዋል  በማለት ታዲያ እርሶ ጫካ የገቡት ይሄንን ለማስፈጸም   ጸረ ኢትዮጵያዊ ሆነው ነው።   ታድያ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ወደ ኢትዮጵያ አቀንቃኝነት ሊመጡ የቻሉት..
…?

መልስ፦ አማራውና ኦርቶዶክስ የተባለው የፖለቲካ ስልት ነው። በተግባር ግን እየሆነ አይደለም። ወደ ትግል ሲገባ ለህዝብ መቀስቀሻ እና ድጋፍ ለማግኛ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይገባሉ ግን ተፈጻሚነት የላቸውም። እንደዚህ አይነት ነገሮች ከፖለቲካ ታክቲክ ውጪ ሌላ ነገር የላቸውም………..?

የኔ ጥያቄ ህዝብንና ህዝብ የሚያምነውን ሐይማኖት አጠፋለው ብሎ የትግል ስልታቸው ውስጥ በማስገባት መንቀሳቀስ ወንጀል አይደለም ወይ? እንድዚ አደገኛ የትግል ስልት አድርገው በሚንቀሳቀሱቱትስ በህግ የሚጠይቃቸው አካል የለም ወይ? ህዝብን፣ ሐይማኖትን እና ታሪክን እናጠፋለን ብለው አሁንም በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ ለዚህም ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል ታድያ ይሄንን አደገኛ አካሄድ የሚከተሉትን በህግ የመጠየቅ አሰራር መከተል አይቻልም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለው

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይ ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ወይንስ የነፃነት ትግላችን!

ሳጠቃልለው እንደዚህ አይነት መድረኮች በሰፊው ቢዘጋጁ መልካም ነው። በተጨማሪም ፖለቲከኞችና ሙህራኑ በአንድ መድረክ ላይ ፊት ለፊት በማገናኘት ህዝብ በተሰበሰበበት ሃሳባቸውን በማቅረብ ከህዝብ ለሚነሱት ጥያቄ መልስ የሚሰጡበት መድረክ ቢሰራ መልካም ነው እላለው። አበቃው