የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ያለበት ሁኔታ በተራ አማኝ እይታ: (አልማዝ አስፋ – ዘረ ሰው)

3

mathias

ይህ አስተያየት የእምነቱ ተከታይ የሆነችው ግለሰብ ትዝብት መሆኑ መዘንጋት የለበትም::

የሁላችንንም ልብ ከፍቶ የሚያየው መድኃኔአለም ብቻ ነው:: እውነቱንም ውሸቱንም የሚታዘበው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው:: ቤተክርስትያን የምንሄደው : መስቀሉን የምንሳለመውና የምንፀልየውም ለምንሰራው ኃጢአት እሱ ይቅርታ እንዲሰጠን ነው:: በመድኃኄአለምና በመስቀሉ የምንምል ከሆነ እውነትንና ሃቅን የሕይወታችን መሰረትና ምሰሶ ማድረግ የእያንዳንዳችን የኦርቶዶክስ ክርስትያን አማኞች ግዴታ መሆን ይገባዋል:: እውነት መናገር : አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ከተሳሳትንና ስህተታችንን ከተገነዘብን ተሳስተናል ማለት የእውነተኛ አማኝ በእውነት የመኖር መሰረታዊ ግዴታ ነው ተብሎ ይታመናል:: ይህን ግዴታ ተግባራዊ ካላደረግነው ቤተክርስቲያን መሄዳችን : መስቀል መሳለማችን ጥቅሙ ምንድነው? ሰው ላይታዘበንና ላያቅብን ይችላል:: ግን ፈጣሪያችን በፈለገው ሰአት ምንጊዜም ገልጦ እንደሚያየን የማይካድ ሃቅ ነው:: ታዲያስ ይህንን የእምነት ሃቅ የምንረዳው ስንቶቻችን ነን?

ይህንን ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ሃይማኖታችን ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሲወዳደር በምን ደረጃ ላይ ነው የሚል ጥያቄ ራሴን በመጠየቄ ነው:: እንደ ኢትዮዽያዊነት: ይህንን ሃይማኖት ከቤተሰቦቼ ስለወረስኩት: ኦርቶዶክስነቴን ያለአንዳች ቅሬታና ትካዜ በመቀበል : የማይፋቅ የማንነቴ መግለጫ አድርጌዋለሁ:: ይህ የማንነቴ መግለጫና መኩሪያ የሆነው እምነቴ እየተስፋፋ ወይስ እንደጠባብ ጎሰኞች አእምሮ እየጠበበና እያነሰ የራሱን አማኞች ማቀፍ እየተሳነው አሳልፎ ለሌላ እምነት እያስረከባቸው ነው ወይ? የአገራችን ሕዝብ ቁጥር እያደገ ሳለ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት በመጠኑ አድጏል ወይ? ተተኪ ምእመናንና ተከታዮች እያፈራና እያጎለመሰ ነው ወይ? ከኢትዮጵያዊያን ውጭ የሌላ አገር ዜጎችን ወደ እምነቱ እየሳበና እያመጣ ነው ወይ? እነዚህና መሰል ጥያቄዎችን ካላነሳን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነትን እድገትና ውድቀት : መሻሻልና ወደሗላቀርነት መገምገም አይቻልም:: በእኔ ግምት የተከታዩ ቁጥር እያነሰ መሆኑን እረዳለሁ:: ይህ ለሁላችንም ለእምነቱ ተከታዮች በጣም አሳሳቢ መሆን አለበት:: እውነትንና ሃቅን መቋቋም የሂሊናን ሰላም ያመጣል::

የሰው ልጅ በሕይወት ሳለ ማንነቱ እንዲያበራ ወይም እንዲኮነን ከሚያደርጉት ዋና መዛኙ : እውነተኝነት ነው:: ሁላችንም የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደምናውቀው ለእውነት የቆመው : በእሱ ሞት ሕይወትንና ንፅህናን እኛ ያገኘንበት : መዲኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በድንጋይ ተመቶ : በሚስማር ተወግቶ : መስቀል ላይ የተሰቀለበት ምክንያት መስዋእትነትንና እውነትን ለእኛ ለሰዎች ለማስተማር ነበር:: እየሱስ ክርስቶስ ተሰቀለ ሞተ ስንል እውነትንና ሃቅን የማንደራደርበት : ዘመድ አዝማድ የማንልበት : በጏደኝነት የማንበገርበት : ለነፍሳችን የማንፈራበት የሕይወት ጉዞ ለማድረግ አምነን ስለተቀበልን ይመስለኛል:: እንዲያው ለይስሙላና ለማህበረሰባዊ ኑሮ ስንል ወደ ቤተክርስቲያን የምንሄድ ካለን : የሃይማኖት ትምህርት የሚሰጠንን ዋናውን ምክንያት ዋጋ ማሳጣት ይሆናል::ይህም እውነትንና ሃቅን የሕይወታችን መመሪያ መሰረት ማድረግ ነው:: በአለማችን የሚፈፀሙ ሰው ሰራሽ አስከፊ ችግሮች ምንጭ የሌሎች መልካም ባህሪዎች ጉድለት ቢሆኑም በዋናነት እውነትንና ሃቅን ዋጋ በማሳጣታችን ነው::

ይህንን ካልኩስ ምን ይሆን አንቺ ሴት የታዘብሽው ብትሉኝ: ከቤተሰቦቼ ከወረስኳቸው የማንነቴ መግለጫዎች አንዱ የሆነው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሃይማኖቴ ያለበት ደረጃ እየመነመነ መሄዱ ስላሳሰበኝ ነው:: በአገር ቤትም ሆነ በዲያስፖራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሃይማኖት አዲስ ተከታዮች እያፈራ በማደግ ሳይሆን: በሃይማኖቱ ውስጥ የተወለዱትን አማኞቹን በሚገባ ማቀፍ ባለመቻሉ ወደ ሌላ እምነቶች እንዲኮበልሉ በማድረግ የሌሎች እምነቶች ሲሳይ አያደረገ ነው:: ምንድነው ወይም ምንድናቸው ምክንያቶቹ ብንል : በእኔ በሃይማኖት ትምህርት መሐይም በሆንኩት እይታ ታላላቅ ድክመቶች የምላቸውን ብጦቅም:-

 1. ሃይማኖታችንን ለማስፋፋት የሚረዳ መመሪያ ከጥንቱ ጀምር በቤተክህነታችን አመራርና አስተዳደር ማለትም በሲኖዱ ውስጥ አለመታሰቡና ሃይማኖታችንን የምናሳድግባቸው መንገዶች አለመነደፋቸውና አለመታቀዳቸው:: በዚህ አጋጣሚ ከሶስት አመታት በፊት የሲኖዶስ የውስጥና የውጭ በሚል አኳያ በነበረው ክፍፍል ጳጳሶቻችን የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖታችንን ልእልናና አንድነትን ላይ ከማቶከር ይልቅ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ በመግባት የሃይማኖት ግዴታቸውን አለመፈፀማቸው በየደብሮቹ በተለይ በዲያስፖራው የተከሰቱት የመከፋፈል ልዩነት እስክዛሬ ድረስ በየአካባቢው ለእምነታችን እድገት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል:: ይህ ሃቅ ሊቀለበስ ወይም ሊካድ አይቻልም:: ለአለፈው ክረምት ቤት አይሰራም የሚለውን አነጋገር ተግባብተንበት በማለፍ ይህን ያህል ለሃይማኖታችን ውድቀት የሚሆኑ ጥፋቶች እንዳይደገሙ ከሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች እስከ ተራ አማኝ ለሃይማኖታችን እድገትና መስፋፋት እያንዳንዳችን ምን ማድረግ ይገባናል የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ ነው::
 2. ቤተክህነታችን የእሁድ ሆነ የበአላትን ቀናት አግልግሎቶች ከማካሄድ በስተቀር ምእመናን በሚስብ መንገድ የመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት አሰጣጥን አለማስፋፋቷ አንዱ ትልቅ ድክመት ሆና ይታየኛል:: በአገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ አካባቢዎች ያሉት ቤተክርስትያናት በግላቸው ተነሳስተው በየቤተክርስትያናቸው የመሰላቸውን የመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጡ እንጂ : የተቀነባበረ ማዕከላዊ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን በማህበረሰባችን ውስጥ በመስጠት የኦርቶዶክስ ሃይማኖታችንን ለማስፋፋት የሚደረግ ጥረት አለመኖሩ በጣም ያሳዝናል::እንደሰው ቤተክርስቲያኖችም ደሃና ሀብታም ሊባሉ ይችላሉ:: ይህም ማለት አንዳንድ ቤተክርስትያኖች በገንዘብና በገቢ የበለፀጉ ቢሆኑም : ከቁጥር አንፃር በአገር ቤት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቤተክርስቲያኖች በጣም ደሃዎች ናቸው:: ይህ የሚያሳየው የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አስተዳደር ክፍል ያለውን ሀብት በመጠቀም ደሃ ቤተክርስትያኖችን ከመርዳት ይልቅ : ከጧፍ ሽያጭ ሳይቀር ሲሶውን በመውሰድ : በድህነት ላይ ተጨማሪ ድህነት በመደረብ የእምነታችንን የወደፊት እርምጃ ጎትቷል::
 3. ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ነጥቦች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ቤተክርስቲያኖች ቢመለከቱም የእንፋሎቱ ወላፍን ዲያስፖራ ውስጥ ያሉትን መቷቸዋል:: ከሌላ እምነቶች የምንገነዘበው አሰራር ግን ሀብታም ቤተክርስቲያን ደሃውን የእምነት ቤታቸውን በገንዘብም ሆነ በሃሳብና በቁሳቁስ እየረዳ እምነታቸውን ወይም ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል:: ሌላዎቹን ተመሳሳይ ተቋሞችን ያዳበረበትንና ያሳደገበትን የእድገትና የልማት መንገድ ገልብጦ ወይም ኮርጆ መጠቀም የአስተዋይ ባህርይ ነው:: የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎቻችንና በዲያስፖራ የሚገኙ ቤተክርስቲያኖች አስተዳደር ቦርዶች አሰራርና አመለካከት : ትራክተር እያለለት በጥንድ በሬ አርሳለሁ ብሎ ድርቅ ከሚል ገበሬ አስተሳሰብ ጋር ይመሳሰልብኛል:: ይህም ምንም እንኳ ስለሲኖዶስ አሰራር የማውቀው ነገር ባይኖረኝም : በኢትዮጵይ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አስተዳደር የአመት ባጀት ሲነሳ ሰምቼ አላውቅም:: በተመሳሳይም ባለሁበት ዲያስፖራ ባሉት አብዛኛዎች ቤተክርስቲያኖችም ሆኑ ራሴ በምሳተፍበት ደብር ስለአመት ባጀት ሲወራና ሲቀርብ አይሰማም:: እንዴት አንድ ድርጅት ያለባጀት ይነቃነቃል? የሃይማኖቱ ተከታዮች የየቤተክርስትያናቸውንና የአጠቃላይ የሃይማኖታቸው ተቋምን ወጭና ገቢ በማወቅ የሃይማኖት ግዴታቸውን መወጣት ይችላሉ:: ይህ ግልጥነት የሌለበት አሰራር ለየቤተክርስትያኖቹና ለሃይማኖታችን ውድቀት ያመጣል:: ባለሁበት ዲያስፖራ ማንኛውም ትንሽም ሆነ ትልቅ ድርጅት የሚካሄድበትና የሚተዳደርበት የአመት ባጀት አለው:: የካቶሊክ የሜቶዲስት የፕሮቴስታንት ፔንቴኮስታል እንበለው የሉትራን ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ሆነ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የአመት ባጀት ነድፎ ለተከታዮቹ ለአባላቶች በየአመቱ ያሳውቃል:: በዲያስፖራ ኖረው ይህን አሰራር የማይከተሉ ግለሰቦች በየቤተክርስትያኖቹ አስተዳደር ቦርድዎች ውስጥ ገብተው ወጭያችንና ገቢያችን ምንድነው ሲባሉ: ለምን ተጠየቅን በማለት የሚጠይቀውን እንደሁከት እንሺ በማድረግ አንጃ በመፍጠር ሃይማኖታችንን እያቀጨጩት ይገኛሉ:: ይህ ትራክተር እያለ በአንድ ጥንድ በሬ አርሳለሁ የሚል አሰራር ከሗላቀርነትም ሌላ ውጤተ-አልባ ነው:: የዘመኑን የአሰራር ዘይቤ የማይከተልና የዘመኑን ቴክኖሎጂ የማይጠቀም ማንኛውም ተቋም መጨረሻው ውድቀት ነው:: የኦርቶዶክስ ሃይማኖቴ አድጎ ማየት እሻለሁ::
 4. ሌላው ተደጋግሞ የሚታየው ችግር : ባለሁበት የዲያስፖራ አገር በተለያዩ ግዛቶችና ከተማዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚፈጠሩት በግለሰቦች የሃሳብና የአመለካከት ልዩነቶች ምክንያት ተወያይተውና ተነጋግረው ከመግባባት ይልቅ : ተገንጥሎ በመውጣት የቤተክርስትያን ግንቦች ቁጥር መጨመርን : በማህበረሰቡ ውስጥ የሃይማኖታችን እድገትና መስፋፋት ለማስመሰል የሚጥሩም አሉ:: በግል ጥላቻ ላይ ተመስርተው አንድን የአምላክ ቤት አዘግቶ ሌላ መክፈት የምን ፈሊጥ እንደሆነ ወይም የትኛው የመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምእራፍ ላይ እንዳለ የሚነግረኝ አለ? ኧረ ለመሆኑ የሃይማኖት ትምህርት ዋናው አላማ ይቅር ለእግዚአብሔር መባባል አይደል? ይቅርታን የማይለዋወጡ : አኩርፈው ያንን ቤተክርስትያን አልሳለም የሚሉ : ቢቻላቸው የበፊቱ ቤተክርስትያን ቢዘጋ ደስ የሚላቸው : በጋራ የመስቀልን ወይም የጥምቀትን በአል ለማክበር አሻፈረኝ የሚሉ : ልባቸውን በጥላቻ የሞሉ ሰዎች : አማኞች ነን ቢሉ : ፈጣሪስ አይታዘባቸውም? ይህ ነው ሃይማኖተኛ : ፈርሃ እግዚእብሔር የሚያሰኘው? ይቅር ለእግዚአብሔር ብሎ ያለውን ቤተክርስትያን ከማጠናከር : ኢሀደግ ኢትዮጵያን በክልል ቅርጫ አድርጎ ዛሬ በሕዝባችን ላይ መከራ እንደጣለ: እነዚህም የግል ጥቅም አሳዳጅ የሆኑ ካህናትና አጨብጫቢ ምእመናን ቤተክስቲያንናችንን ቅርጫ እያደርጉ እያኮሰሷት ይገኛሉ:: ይህ አካሄድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውድቀት መንገድ ነው:: ታዲያስ በ10 ኪሎሜትር ውስጥ በዲስ ከተማ በፊት በአንድ ቤተክርስትያን ሕንፃ ውስጥ የሚገለገሉ ምእመናን ለምንስ ሶስት ቤተክርስቲያን አስፈለጋቸው? የአማኝ ቁጥር ጨምሮ ሳይሆን በቡድንነትና በወገናዊነት አድማ ላይ የተሞረከዘ ክፍፍል ስላጠቃ ነው:: በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በአባላት መሃል ወይም በካህናት መሃል ወይም በካህናትና በአባላት መሃል የሚፈጠረውን ያለመግባባትንና ውዝግብ አጣጥመው በሰላም በአንድ ደብር ውስጥ ማገልገልንና መገልገልን ከማስቀደም ይልቅ አኩርፎ በመውጣት የቤተክርስቲያን ሕንፃ ክፍያና ሌላ ወጭዎች በአማኞች ጫንቃ ላይ ማብዛትና የተወሰኑትን አማኞች ከሃይማኖታችን ማሸሽ እንጂ ሃይማኖታችንን አላስፋፋም:: አላሳደገም::
ተጨማሪ ያንብቡ:  የዶ/ር ቴድሮስ ነገር ………….| በጌታቸው ማሩ እና ሳጅን ዮሮሱን 

 

ከላይ የተጠቀሱት የሃይማኖታችን እድገትና መስፋፋት እንቅፋቶች የሆኑት : የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም : እኛ ሁላችንም የሃይማኖቱ ተከታዮች ለሃይማኖታችን ቅጨጫ ተጠያቂዎች ከመሆን ነፃ ልንሆን አንችልም:: አብዛኛው አማኝ ከመመራት አስተሳሰብ ወጥቶ የመሪነት ስሜት ውስጥ መግባት ይኖርበታል:: ሁሉም በአንዴ አመራር ውስጥ መሳተፍ አይችልም:: በአንድ ጊዜ የሚኖረው አንድ አስተዳደር እስከሆነ ድረስ በዚያ የሚሳተፉ ግለሰቦች በቁጥር ናቸው:: ግን ሌሎቹ አባላት መሪዎችን ተወካዮቻቸው እንጂ ገዢዎቻቸው አድርጎ ማሰብ እነዚህን መሪዎች ከተጠያቂነት ይልቅ አምባገነንነትን እንዲያራምዱ መንገድ ይከፍትላቸዋል:: ይህ አይነት አመራር በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በድርጅቶች ላይም ይከሰታል:: ይህንን የተዛባና እኔ አውቅላችሗለሁ የሚል ግብዝነት ለአገራችንም ሆነ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖታችን እድገት አይጠቅምም:: ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት የእድገት ጉዞ የአማረ መንገድ ቅየሳ እያንዳንዱ የሃይማኖቱ ተከታይ ተገቢ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት:: ለዚህም ነው በየቤተክርስትያኖች የመረጧቸውን ወኪሎቻቸውን ለሚሰሩት ስራ ተጠያቂነትና ግዴታቸውን መወጣታቸውን ምእመናን ክትትል ማድረግ አለባቸው የምለው:: ለሃይማኖቱ የሚቆረቆር : በግሉ ለሃይማኖቱ እድገት ምን ላድርግ ብሎ አስቦ እርምጃ መውሰድ ግዴታው ማድረግ ተገቢ ነው የሚል አመለካከት አራምዳለሁ:: ወንድም ለኃላፊነት ሲመረጥ : ሌላው ወንድም ዝምድናውን ለቤት ውስጥ ትቶ: እንደቤተክርስትያን አባል : አስተዳደር ላይ ያለውን ወንድሙን ለተመረጠበት ግዴታ ለደብሩ : ሰላም : አንድነት: እድገትና መስፋፋት የችሎታውን ያህል ያበረክታል ወይ ብሎ መጠየቅ የእውነተኛና ሃቀኛ ሰው ተግባር ነው:: በተመሳሳይም እያንዳንዳችን እኔ እምነቴን የማዳብርበት ሃይማኖቴን የማራምድበት ደብር ነው የምንለውን ቤተክርስትያን እንዴት ላሳድገው : እንዴት አባላት ላብዛለት : እንዴት ሃይማኖቴን ባለሁበት አካባቢ ላስፋፋ : ሃይማኖቴን ለማያውቁት እንዴት ላስተዋውቅ በማለት ስለ ቤተክርስትያኑ እድገትና ስለሃይማኖታችን መስፋፋት ማሰብ የኦርቶዶክስ ክርስትያን ግዴታችን ማድረግ ተገቢ ይሆናል እላለሁ:: በአሁን ሰአት እንኳን አዲስ ተከታዮች ማፍራት ይቅርና : ከእኛ የወጡትን ልጆቻችንን በእምነታችን ውስጥ አቆይተን ወራሽ ማድረግ አልቻልንም:: አንዳንዶቹ የሃይማኖት መሪዎቻችንንና አስተማሪዎቻችን ከሃይማኖታችን ጥንካሬ ይልቅ የግላችውን አለማዊ ምቾት ሲያጎለምሱ እንታዘባለን:: የረሱት ነገር ሃይማኖቱን ለማሳደግ ያንን ያህል ቢጥሩና ቢሰሩ : ሃይማኖታችን ሲጠናከር እነሱም እንደሚበለፅጉ ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዮናታን ተስፋዬ ከወንጀል ነፃ ስለመሆኑ ያረጋገጠ ነው | ስዩም ተሾመ

 

በተለይ በዲያስፖራ ያሉት ቤተክርስትያኖቻችን የተቋቋሙት በሲኖዶስ መመሪያና እርዳታ ሳይሆን የእምነቱ ተከታዮች ለሃይማኖታቸው ባላቸው ፅኑ አቋም በግል ፍላጎት ተነሳስተው ነው:: እነዚህ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ተሰባስበው አቅማቸው የፈቀደውን ከኑሮአቸው እየቆጠቡ በያሉበት ቤተክርስቲያን ከፍተው እምነታቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ:: ይህቺ እምነት ወይም ይህች ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የዛሬ 50 አመት ምን ያህል ተከታዮች ይኖራታል? በአለም ደረጃ በእምነት ወይም በሃይማኖት አኳያ ቦታዋ ምን መሆን ይገበዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች ተከታዮቿ አንስተን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዘልአለማዊ ዘለቄታና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት እድገት በያለንበት የተቻለንን ያህል ማበርከት ይኖርብናል በሚል አመለካከት በያለንበት እንድንወያይበት መነሻ ለማድረግ ነው::

 

ኢትዮጵያ ባቀፈችው ሕዝቦቿ አንድነትና ሕዝቦቿ በተቀበሏቸው ሃይማኖቶች ተጣጥመውና ተፋቅረው እስከዛሬ በጋራ እንደኖሩት : ከትውልድ ወደ ትውልድ ልእልናዋንና ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም በየትውልዱ ድርሻቸውን ይወጣሉ እላለሁ:: መጀመሪያ ግን ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም ከሌሎች ሃይማኖቶች ለአገር ልእልናና ለሕዝባችን አንድነት በጋር እየሰራን በሰላምና በፍቅር አብረን እየኖርን: ስለእድገት የራሳችንን መንገዶች እየፈለግንና ከሌሎችም እየተማርን ኦርቶዶክስ እምነታችንን ሌላውን ሳንጎዳ እናራምዳለን::

 

ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች የሚካሄዱበት : ባህሎች የሚታዪበት : ቋንቋዎች የሚነገሩበት ጥንታዊ ሀገር መሆኗን ሁልጊዜ እያስታወስን : በኢትዮጵያዊነት መኩራት ይኖርብናል:: ጥቂት ደንቆሮ ምሁራን ለግል ጥቅማቸው ማራመጃ አንዲመቻቸው የሌለ ታሪክ በመፍጠር ጊዜያዊ ሁከታ ቢፈጥሩም ኢትዮጵያን አያንበረክኳትም:: ምክንያቱም መንበርከክ አታውቅም:: ለዚህም እንግሊዞችን : ጣሊያኖችን ስለበፊት ሙከራቸው : ዛሬ ደግሞ አሜሪካንን መጠየቅ ይቻላል:: ከጥቂት ባንዳዎችና ሀገር ሻጪዎች በስተቀር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የጀግንነት እንጂ የመንበርከክ ታሪክ በፊትም ተፅፎ አያውቅም : አሁንም ሆነ ወደፊት አይፃፍም::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቪድዮ: ለወ/ሮ አዜብ መስፍን የተሰጠ አስቂኝ ምላሽ - ጸሐፊ: ክንፉ አሰፋ - ተራኪ: ደምስ በለጠ

 

ንጉሥ ኃይለሥላሴ የተናገሩትን ጥሩ አባባል በማስታወስ:- “ሃይማኖት የግል ነው:: ሀገር የጋራ ነው::” ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሔሮች የሚኖሩባት : ከመቶ አስር በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት : ግለሰቦች የመሰላቸውን እምነት የሚያራምዱባት 3000 አመታት የኖረች በጠባብ ጎሰኞች የማትበተን ሀገር መሆኗ መገንዘብ አለብን::

 

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች!!

 

3 Comments

 1. ልቤን ፍርሀት ፍርሀት አለው ተጋዳላዮች መሀል አዲስ አበባ ተንከባለው በአምቡላንስ አንሱኝ እንዳይሉ ነው። አረጋዊ በርሄ ተሹሞ ታዲዮስ ታንቱ ይታሰር? እውነትም ሳንረገም አንቀርም ከድፍን ትግሬ አንድ ጤናማ ሰው ሲጠፋ

 2. “በሃይማኖቱ ውስጥ የተወለዱትን አማኞቹን በሚገባ ማቀፍ ባለመቻሉ ወደ ሌላ እምነቶች እንዲኮበልሉ በማድረግ የሌሎች እምነቶች ሲሳይ አያደረገ ነው::”
  ነው ብለሽ? “it should be about the game not the players”. ማንም ሰው የፈለገውን ህይማኖት ይከተል። ሥጋት አይግባሽ፤ “ኦርቶዶክስ ሃገር ናት” ምእመናኗ ተጨልፈው አያልቁም።
  ማሳሰቢያ ለዘሃበሻ፡ [እርሳቸውን በግል የሚመለከት እስካልሆነ ድረስ] ለሌላ የኦርቶዶክስ ዜናም ሆነ ለነጻ አስተያየት የብጹእነታቸውን ፎቶ መጠቀሙ ቢቆም ጥሩ ነው።
  በምርጫ ብቻ!

 3. ለአልማዝ አሰፋ
  እውነት፤ትክክለኛ እና ሀቅን ነው የተገለጸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ እና የቤተ ክርሥቲያን አለቆች፤ መስቀሉንም የሚያሳልሙን ቀሳውስቶች ቀደም ሲል ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ቢገነዘቡት ኖሮ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በዚህ ደረጃ ባልሆነም ነበር። በመሆኑም ከላይ የጠቀስሻቸው ሁሉ የተከሰቱት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ፓትሪያሪክን በተወሰኑ ጳጳሳት የግል ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል ጥቅምም ለማሳደድ ሲባል ለደርግ አስተዳደር አቤቱታ በማቅረብ እንዲታሰሩ እና እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አይን እዬጨለመ መጣ።በቤተ ክርሥቲያን አለቆችም ዘንድ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስም የግል ስልጣን ፍለጋ እና ጥቅም ማሳደድ እየጎለበተ፤ ፍቅረ ንዋይ እየበለጸገ፤የቡድን እና የአካባቢ የጵጵስና ሹመት እና ሺረት እያደገ፤ በደርግ አጋዛዝም እምነቱን ከማስፋፋት ፤ በመስቀሉ ከመባረክ ይልቅ ከነአካቴውም የኢስፓኮ አባል የቀይ ደብተር ተሸካሚ መሆኑ ጎልብቶ መጥቶ፤ደርግ የአገዛዝ ስልጣኑን ሲያጣ ደግሞ ተጀምሮ የነበረው የሥልጣን ጥም ማርኪያው፤የቡድን ሹም ሺረት እና የፍቅረ ንዋይ ማሳደዱን የሚናጋ መሆኑ ታምኖበት በህመም ምክንያት በጡረታ በመገለል ስደት ተጀምሮ የውጭው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚል ተመስርቶ ቤተ ክርስቲያን ከሁለት ተክፍላ አንቺ እንዳልሼው(እርስዎ) እኔም የዲያስፐራው አባል ስለሆንኩ በ10 ኪሎ ሜተር እርቀት ብቻ ሳይሆን በ5 ኪሎ ሜትር በማይሞላ እርቀት በካህናት አስተባባሪነት በቅዳሴ ስነሥርአት ላይም የከሌ ጳጳስ ስም አንሳ አታንሳ (ጥራ አትጥራ) በመባባል በተፈጠረው አቲካራ ምዕመናንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፈቀደውን ካህን በመከተል ሆድ እና ጀርባ ሆኖ የተመሠረተውን ቤተ ክርሥቲያን ዘግቶ ያለ የሌለውን በማዋጣት በዌር ሀውስና በመሮሪያ ቤት ሌላ ቤተ ክርሥቲያን በመክፈት፤ክፉ እና በጎውን አብሮ ያሳለፈ፤ህመምተኛን የጠየቀና ያስተዛዘነ ዛሬ እንደማይተዋወቅ የጎረጥ እይተያየ የኦርቶዶክስ እምነት እንዲዳከም ሆኖአል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ወይም ፌዝ ኤንድ ኦርደር እንዲህ ይላል ” አንድ ካህን ወይም ቄስ ያለ ጳጳሱ ፈቃድ ቤተ ክርሥቲያን ቢከፍት እና መስዋዕት ሰውቶ ቁርባን ቢያቆርብ የተወገዘ ነው” ይላል። ታዲያ ይህ ትእዛዝ እያለ በጣም የሚያሳዝነው ነገር በአለሁበት አካባቢ ቄሶቹ ተጣልተው አንደኛው የራሱን ቤተ ክርሥቲያን በመክፈቱ ለምን እንዲህ ያለ ተግባር ተፈጽመ በካህናት መካከል ያለውን አለምግባባት በመነኮሳት እና በካህናት መፍትሄ ማግኘት ይቻላል ብየ ሃሣቤን አዲሲ ለከፈተው ካህን ሳቀርብ የተመለሰልኝ ነገር፤ታቦት ከሚኒሶታ ከተማ ስለአመጣሁ የራሴን ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ ሲለኝ በጳጳሱ ተባረከ ወይ ብዬ ስጠይቅ ደግሞ እኔም ቄስ ጳጳሱም ቄስ ብሎኝ ቁጭ። ከአመታት በሁሏ ሥሰማ ደግሞ ይኸው ካህን ከምዕመናኑ ጋር ባለመስማማት ቤተ ክርስቲያኑን ትቶ ሲሄድ ከሚኒሶታ አመጣ የተባለውን ታቦት ወስዶ ከቤቱ ክሎዜት አስቀምጦታል ነው።በዚሁ ካህን የተናደዱ ምዕመናኖች ደግም ገንዘብ በማዋጣት አንድ ምዕመን ኢትዮጵያ ልከው ሟቹ አቡነ ጳውሎስ ከአልባሳት ጋር ከአንድም ሁለት ታቦት ተሸልሞ ማለት ይቻላል ይኸው ዛሬ በአንድ መነኩሴ ይቀደስበታል።ታዲያ ይህንን ማለት አልፈልግሁም ነበር ነገር ግን አልማዝ አሰፋን የኦርቶዶክስ እምነት እየጎለበት እና እያደገ ሳይሆን እየተዳከመ በመምጣቱ እኔንንም ስለሚቆረቁረኝ እና ስለሚያሳስበኝ ለክርሥቲያን ምእመናን ለማሳሰብ ፤ እየተዳከመች የመጣቸው በቤተ ክርሥቲያን አለቆች በመሆኑ በምዕመናን በክሉ እንዲታሰበበት ሲሆን በዕምነቱ ተከታይነቴ የአልማዝ አስፋ የትዝብት አስተያየቷን ከልብ በመነጨ ስለአመንኩበት በመሆኑ እና እምነቴ በመሆኑ ነው።ምናልባት ይህንን በማለቴ የሚከፋ ካለ ይቅርታ ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.