ግብጽ የገባችበት ቅርቃርና የኢትዮጰያ አበሳ (ከባጤሮ በለጠ)

1
ግብጽ ከፍተኛ የታሪክና የጥቅም ትስሥር ካላት ከኢትዮጰያ ጋር አምርራ ችግር ውስጥ ለምን ገባች በተለይም ደግሞ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደመጨርሻው እየደረስ በሚገኝበትና የማስቆም እድሉ እጅግ ጠባብ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ ለምን ግብጽ ደጋግማ ጸብ መቆስቆሱን አበዛች የሚለው ሁሉንም የሚያነጋገርና የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው። እኔም የሚከተለውን እይታ ላካፍላችሁ።

egypt ethiopia zehabesha

የግብጽ መንታ ውጥረቶች

ግብጽ በሁለት ታላታቅ ችግሮች ተወጥራ ትገኛለች ።
የመጀመሪያው ኢኮኖሚያዊ ሲሆን በተለይም ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ግብጽ እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ነች
ሁለተኛው ወጥረት ደግሞ ፖለቲካዊ ሲሆን ፐሪዚደንት አል ሲሲ በተለይም ከእስልምና ወንድማማቷች ፓርቲ እና ከተከታዮቹ እየደረሰባቸው ያለው ታላቅ ተጸእኖ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ተደማምሮም ፐሬዚደንት ኢል ሲሲን ከራሳቸው አልፈው ለኢትዮጰያም የሚተርፍ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ፤ከፍቅር ይልቅ ወደ ግጭት እንዲያመሩ አድርጓቸዋል።

የኢኮኖሚ መዳሽቅ

ግብጽ በአረቡ አለም ድሀ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ የምትመደብ ነች። ራሷን ለመቻል ያደረገችው የዘመናት ጥረትም እዚህ ግባ የሚባል ወጤት አላስገኘም። ግብጽ ከአቅሟ በላይ የሆነ ሰራዊት ገንብታ የምታገኛትን ትንሽ እድገት ለዚሁ ተቋም ማንቀሳቀሻ እያዋለች የሌላው ህዝብ እድገትም እጅግ የታፈነ እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡ የግብጽ ወታደር የሀገር ማከላከያ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክ 60% እስከ 70 % የሚቆጣጠርም ነው። ይህም በመሆኑ ከሰራዊቱ ውስጥ ብቅ የሚሉ መኮንኖች የህገር መሪ ሆነው ለረጅም ጊዜ የበላይነታቸውን አስፍነው ይኖራሉ። ይህ ሁኔታ አሁንም ቀጥሏል።

የግብጽ ህዝብ ከአውሮፓ አቆጣጠር በ 2015, 27.8%, በ 2018 32.4% in 2018 አሁን ደግሞ ክ40% ያላነሰው ከድህነት ወለል በታች ይገኛል።ይህ ስለሆነም ከሶስት አጅ ግብጻውያን ውስጥ አንዱ የወር ገቢው ክ 47 ዶላር ማለትም በቀን ክ 1 .60 ዶላር በታች ነው ።ይህ ማለት ሲጀመርም ግብጽ ኢኮኖሚያዋ እጅግ ብዙ ለሆነው ዜጋዋ የማይመች ነው ማለት ነው።

ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ደግሞ ግብጽ ትልቅ ችግር ውስጥ ገብታለች። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዳሽቋል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 2.5 ሚሊዮን ግብጾች ሰራ አጥ ሆነዋል። ኢኮኖሚስቶች እንደሚናገሩት ኮሮና ከጀመረ ጀምሮ 26% ግብጻውያን ከስራ ተባረዋል።
የሀገሪቱ አምራች ፋብሪካዎች በአብዛኛው ቴክስታይል ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ከኤክስፖርት መውደቅ ጋር ተያይዞ ይህ ክፍለ ኢኮኖሚም በአጭር ጊዜ ተመልሶ የሚያንሰራራበት ሁኔታ አይታይም። ኮሮና የሀገሪቱን ቱሪዝም ክፉኛ አሽመድምዶታል፣ በዚህም መሰረት በአመት 70 ቢሊየም ዶላይ ያስገኝ የነበርውና 12% የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚወክለው ይህ ክፍል በ 70% ድባቅ ተመትቶ ታላቅ ኪሳራ ውስጥ ነው።
ይህ የኢኮኖሚ ቀውስ ባለፈው አመት ታላቅ የህዝብ አመጽ ቀስቅሶ ነበር። አሁንም ሁኔታው እየባሰ በመሆኑ ወደ ተመሳሳይ ሁኔታ የሚያመራበት እድል እጅግ ሰፊ ይመስላል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ድቀቱ የሀገሪቱን 60- 70 % የሚቆጣጠረውን የሀገሪቱን የጦር ሀይል ገቢ እጅግ ጎድቶታል። ለጊዚው መጎዳት ብቻ ሳይሆን የሚያንሰራራበት ጭላንጭል እጅግ የጨለመ በመሆኑ ሰራዊቱና አመራሩ በአል ሲሲ ላይ እጅግ እንዲከፋ አድርጎታል። Praetorian spearhead: the role of the military in the evolution of Egypt’s state capitalism 3.0 – LSE Research Online

ይህ ሁሉ የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያስከትለው የፖለቲካ አንደምታ የ አል ሲሲን መንግስትና ደጋፊዎቻቸው የሆኑ ሀገራትን እጅግ አሳስቧቸዋል። Poverty Uprising in Egypt: Causes and Consequences ( dohainstitute.org )

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለፍትሕ ሲባል፤ ሥርዓቱ ይፍረስ! (ተመስገን ደሳለኝ)

የሞስሊም ብራዘርስና የሌሎች ተቃውሞ መጠናከርና የአል ሲሲ የፖለቲካ ጭንቅ

ከላይ ከተገለጸውን ብሶት ጋር ታያይዞ ግብጽ ሞስሊም ብራዘርስ የሚባለውም ተቃውሚ ድርጅት ውስጥ ውስጡን የአልሲሲን መንግስት ከፍተኛ ግፊት በማድረግ እያስጨነቀው ይገኛል። ሞስሊም ብራዘርስ የግብጽ ምድር በየቦታው ትልቅ ድጋፍ አላቸው ከጥቂት አመታት በፊት በምርጫ 51% አግኝተው አሽንፈው እንደነበርና አል ሲሲም እነርሱን ገልብጠው ወደ ስልጣን እንደመጡ ይታወሳል። ይህ የሚያሳየው የህዝብ ድጋፋቸው ሰፊ እንደሆነ ነው።

ይህ ቡድን (የሞስሊም ብራዘርስ ) አሁን በተለይም በገጠሩ መሳሪያ አንስቶ እየተፋለመ ሲሆን የድህነቱ መባባስ እጅግ ትልቅ ድጋፍን ያስገኝለታል ተብሎ ይታሰባል። የሰራ አጥነትና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ግብጻዊያን በተለይም ድሀ በሆኑት ደቡባዊ የግብጽ የገጠር ክፍለ ሀገሮች እስከ 52% ይደርሳል። በአንዳንድ ቦታዎች ሁኔታው ከዚህ የባሰ ነው : ለምሳሌ በ አስይት (Asyut) ክፍለ ሀገር 66% በሶህግ (Sohag) ደግሞ 57%. የሞሆነው ህዝብ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። የሞስሊም ብራዘርስ እንቅስቃሴም በነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው ይነገራል። የኢኮኖሚ ሁኔታው ሳይሻሻል እየቆየ ሲሄድም ተቃዋሚዎች ከህዝብ በኩል የሚኖራቸው ድጋፍ ይበልጥ ሊጠነክር ይችላል ተብሎ ይገመታል።

ክዚህ ሁሉ ጋር ተያይዞ አትዮጰያ ሕዳሴን መገንባት መጀመሯ ለአልሲሲ ተቃዋሚዎች ትልቅ የፐሮፓጋንዳ መሳሪያና ህዝብንም ማነሳሻ ሆኖ እያገለገላቸው ነው። ተቃዋሚዎች በመደጋገም “መንግስት የሀገር ጥቅም ሽጠ” እያሉ አል ሲሲን ብጥልጥላቸውን እያወጡት ነው።

ሰለዚህም ይህ ሁሉ ተደራርቦ ግብጽ በታላቅ የአመጽ በር ላይ እንድትደርስ አል ሲሲም ለፖለቲካ ስልጣናቸው በሚያሰጋ አደጋ ውስጥ እንደከበቡ መደረጉን ያሳያል። የሞስሊም ብራዘርስ ቃል አቀባይ የሆኑት ታላት ፍህሚ (Talaat Fahmy ) በቅርቡ ከቱርክ – ኢስታምቡል የሚከተለውን ብልዋል ” የሀዝብ ትግስትና የሚሆነውን ሁሉ ችሎና ተሽክሞ መኖር እስከ ወዲያኛው የሚቀጥል አይደለም ፣ መቼ እንደሚሆን ቀኑን በትክክል መናገር ባልችልም የግብጽ ህዝብ በአመጽ ወደጎዳና መውጣቱ ግን አይቀሬ ነው “New Egypt uprising ‘inevitable,’ say Muslim Brothers ( alaraby.co.uk )

ከላይ የተጠቀሰው የህዝብ ብሶት ማደግ፣ የሰራዊቱ መሪዎች ኪስ ማራቆትና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በተለይም የሞስሊም ብራዘርስ እየተጠናከረ መምጣት አል ሲሲንም ሆነ የግብጽ ሽርኮቻቸውን እጅግ አስደንግጧቸዋል።

ማስተንፈሻ ፍለጋውና ለኢትዮጰያ የተረፈው አበሳ

አል ሲሲና ሽርኮቻቸው በአንድ በኩል በግብጽ ህዝብ እና በአልሲሲ መንግስት መሀል በሌላ በኩል በተቃዋሚዎችና በአል ሲሲ መንግስት መሀል እንዲሁም በአል ሲሲና በግብጽ ወታደራዊ መሪዎች መሀል የሰፈነውን ውጥረት ለማስተንፈስ፣ ትኩረትን የሚያስቀይርና ለችግሩ ሁሉ ስበብ አድርገው የሚፈርጁት ጠላት ይፈልጋሉ ፡፣

ለዚሀም ምቹ ሆና ያገኟት ለጊዜው ሀገራችን ኢትዮጰያን ነው። አል ሲሲ ትኩረታቸውን ሁሉ በኢትዮጰያ ላይ በማድረግ የህዝቡን ቀልብ በሀገራዊ ስሜት ለማማለል ብዙ ይጥራሉ፡፤

ሰራዊቱም የሻከረ ሆዱን ወደ ጎን አድርጎ ትኩረቱን በኢትዮጰያ ላይ እንዲያሳርፍ በተከታታይ ስብሰባና የሽንገላ ንግግር ታላቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ህዝባቸውንም ኢትዮጰያ የምትባል ጠላት አባይን ልታሳጣህ ነው፣ ጥቅምህን አስጠብቅ ሀገርህን አድን ” በሚል ፐሮፓጋንዳ እንዲሸበርና ትኩረቱን ከውስጥ አጀንዳ ለማስቀየስ አጠናክረው እየሞከሩ ነው።

ይህን በማድረግም እያሽቆለቆለ የመጣውን ቅቡልነታቸውን እንደገና ማድረግ ይቻላል ብለው ያስባሉ። ይህም ሰለሆነ ከኢትዮጳያ ጋር ወደ የጋራ ጥቅምን ሰላም ሳይሆን ወደ ንትርክና ግጭትና ጥፋት ማተኮራቸውን እናያለን።

ክግብጽ የውስጥ ችግር ግዙፍነት ጋር ተያይዞ ሲታይ ግን እቅዳቸው አል ሲሲን ብዙም ላያስኬዳቸው ይችላል። ኢትዮጰያን ስበብ አድርጎ መጮህ ለጊዜው ትኩረትን ዘወር ያደርጋል እንጂ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ማለትም ሰራ አጥነትን፣ የኢኮኖሚ ቀውሱን የድህነት መብዛትን ወዘተ አያስቆመውም።ከዚህ በተጨማሪም ተቃዋሚዎቹ ከስር ከስር እየተከታተሉ አል ሲሲ አንድ ጊዜ ከኢትዮጰያ ጋር ሌላ ጊዜ ከቱርክ ጋር ግጭት የሚቀሰቀሱት ትኩረት ለማስቀየር የሚደረግ ሴራ ነው ብለው በሰፊው ማጋለጣቸው የሚጠበቅ ነው።

ስለዚህም ይህ ሙከራ አልሲሲ የጠበቁትን ውጤት ካላስገኛቸው ሌላ ምን ሊያደረጉ ይችላሉ? ብሎ ማስብ ተገቢ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እያወቁ ማለቅ፡ የብሔር ግጭት ከበደሌ እስከ ሱማሌ | ስዩም ተሾመ

ትኩረትን ለማስቀየር የሚደረግ ጠላት ፍለጋና ትንኮሳ ከተራ ማስፈራሪያነት አልፎ እስከ እውነተኛ ግጭትና ጦርነት ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ሀገራት ታሪኮች ያስተምሩናል።

ግጭትን እንደ ማስተንፈሻ የሚመለከቱ ህይሎች በአንድ በኩል የሚመለክቱት በሚጫረው ግጭት በአሽናፊነት እንወጣለን ወይስ አንወጣም የሚለውን ሳይሆን ሀዝባችንን በስፊው ሊያሰባስብልንና የውስጥ መከፋፈልና ትኩረቱንስ ለማስቀየር ይችላል ወይ የሚለው ነው።

ከግጭቱ በአሽናፊነት መውጣቱ ትልቅና ተጨማሪ ጥቅም ቢሆነም የዚሀ አይነት ግጭት መሰረቱ እውነተኛ ጥቅምና ወታደራዊ አሽናፊነትን ማረጋገጥ ሳይሆን መህበራዊ፣ ፖሊቲካዊና ስነልቦናዊ ግብ ላይ ያተኮረ ማሳሳቻ ሰለሆነ ትኩረቱ በጦርነት የማሽነፍ ጉዳይ ሳይሆን የህዝብን እይታ ወደፈለጉት አቅጣጫ መውስድ ነው።

ሊላው ጉዳይ ደግሞ በዚህ ግጭት ውስጥ ብንገባ በአካባቢው መንግስታትና በአለም አቀፉ ህብረተስብ በኩል የሚኖረው ድጋፍና ወግዘት ምን ሊመስል ይችላል ይህስ ሁኔታ በህዝባችን ስነ ልቦና ላይ ( ላስብነው ህዝብን ማነሳሳት፣ ትኩረት ማስቀየርና ማስባስብ ) ምን ተጸእኖ ይኖረዋል ለሚለው እሳቤን ትኩረት የሚስጥ ነው።

የአል ሲሲ መንግስትና ወዳጆቻቸው ኢትዮዮጰያ በበአሁኑ ሰአት በውስጥ መከፋፈልና ግጭት እንዲሁም በውጭው አለም የተለያየ ተጸእኖ ስር ተወጥራ እንዳለች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከዚህ አልፈውም ለውስጥም ሆነ ለውጭው ውጥረት የብዙዎቹ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ እጅ ትልቅ አስተዋጻኦ እንዳለው ግልጽ ነው።

ይህም በመሆኑ አልሲሲና ደጋፊዎቻቸው ከኢትዮጰያ ጋር ወታደራዊ ግጭት ብንቀሰቅስ እንኳ የሚደርስብን የአለም አቅፍ ውግዘትና ተጸእኖ ከምናገኛው ጥቅም አንጻር ዝቅተኛ ጥቅሙ ደግሞ ከፍተኛ ነው ብለው እንደሚያስቡ መገመት ይቻላል፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ በሁለቱ ሀገሮች መካከልም ሆነ በአጠቃላይ በቀጠናው ለሰፈነው ውጥረት በተለይም ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ለጊዜው ግብጽን በተጠያቂነት የሚከስ የጎላ ድምጽ እንደሌላ ማስታውስ ተገቢ ነው። ሆኖም ግን የአለም አቀፍ ማህበረስቡም እይታ በተለያየ ምክንያት ቶሎ ሊገለበጥና ከዝምታ ይልቅ ወደ ውግዘት ሊዞር የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ ነው። አል ሲሲ በህዝባቸው ላይ የሚያደርጉት ተከታታይ የግፍ ስራ በአለም አቀፉ ማህበረስቡ ፍቅርን አትርፎላቸው አያውቅም።

ኢትዮጰያ በአፍሪካም ሆነ በአለም ማህብረስቡ ካላት ትኩረት ሳቢነት አኳያ ተጨማሪ ተንኳሽነትም በሌሎች ዘንድ በትግስት መታለፉ የሚያበቃበት አውድ ሩቅ አይመስልም። ይህም ግብጽን በአንድ በኩል በጠብ አጫሪነት እንድትቀጥል ያበረታታታል በሌላ በኩል በቀጥታ በተራዘመ ግጭት ውስጥ እንዳትገባ ያደርጋታል።

ይህን ሁሉ አያይዘን ስንመለከት የአል ሲሲ መንግስት የገባባት አረንቋ እጅግ ጥልቅ ሲሆን ራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጰያንም ታላቅ አደጋና ጦስ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ይመስላል። የአል ሲሲ መንግስት ( ግብጽን)፡ የተራዘመ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የኢኮኖሚ አቅምም ሆነ የህዝብ ድጋፍ ባይኖራቸውም፣ የህዝብን ቀልብ የሚስቡ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመሰንዘር እና በኢትዮጰያና በቀጠናው ውስጥ ውጥረቱ እንዲቀጥል ለማደርግ የሚገፋፋቸው ሁኔታ ግን ሰፊ ሆኖ እናየዋለን።

ግብጽ ከሀገር ሀገር እየዞረች ሱዳንን ኮንጎን ፣ ጅቡቲን፣ ኬንያን ወዘተን “አይዟችሁ አኔ አለሁላችሁ” ማለቷ ለ ወታደራዊ ጥቃት እቅዷ አለም አቅፍ ድጋፍን የማስባስቢያ ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችልና የዲፐሎማሲ ትግሉ የዚህ ሁሉ አንዱና ትልቁ አካል እንደሆነ መገመት ስህተት አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከ “ናስ ማሰር - አፍ ማሰር”   - ይገረም አለሙ

የአኛስ ድርሻ?

ብዙ የወታደረዊ ሙያ ሊቃውንት የሚጠቀሙበት “ስላምን ከፈለግክ ለጦርነት ተዘጋጅ If you want peace be prepared for war” የሚል የቀደመና ሰፊ ተቀባይነት ያለው መርህ አለ። በሀገራችንም አይመጣምን ትትህ የመጣልን አስብ፣ ያልጠረጠረ ተመነጠር ወዘተ የሚሉ ተመሳሳይ አመለክት ያላቸው ብሂሎች ለዘማናት የቆዩ ናቸው።
ሰለሆነም የምናውቀው ሁሉ እንዳለ ሆኖ ከግብጽ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃትና ተጨማሪ ትንኮሳ ሁሉ ለማምከን፣ ከተሰነዘርም ለማክሽፍና በአሽናፊነት ለመወጣት ምን ይደረግ የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው።
የኛ ዋናው አደጋ ከውጭ የሚሰነዘረው ከበባ ብቻ ሳይሆን የእርስ በርሳችን አንድነት መላላትና እርስ በአርስ በማያባራ ግጭት ውስጥ መሆናችን ምናልባትም አንዳዶች ሀገር ወደጦርነት ብትገባ የፖለቲካ ግባችንን ለማሳካት የተሻለ እድል ያስገኘናል የሚል አደገኛ እይታ ይዘው መጓዛቸውም ጭምር ነው። የተከፋፈለ ህዝብ ለጥቃት ተጋላጭ ነው።

በዚህ አኳያ ሀገርና ህዝብ ላይ የታቃጣውን አደጋ ለመመከት ትልቅ ሰራ አሁኑኑ መሰራት ይኖርበታል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አስቸኳይ የፖለቲካ ድርጅቶች የሀይማኖትና ሲቪክ ማህባራት ስብስባ ጠርተው የውጭውን አደጋ በጋራ ለመመከት የጋራ ሀገር አድን አቋም እንዲወሰዱ ህዝብንም በዚሁ መልክ ማስተባበር እንዲጀመር ምክክር ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ይህን ሁኔታ እቀጣይነት የሚያቀነባብር ከተለያዩ ባለድርሻዎች የተውጣጣ አካል ባስቸኳይ ማቋቋምና ወደስራ መግባት ያሻል። በዚህ አኳያ ባለፊት ሳምንታት ኢህ አፓ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ አብን ኢዜማ እንመካከር ብለው ጥሪ ማቅረባቸው በልሂቃኑ መሀል የመተባበር ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ ፍንጭ ሲሆን ይህን እውን ማድርግ ቀጣዩና አጣዳፊው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

የፖሊቲካ ልሂቆቻችንም በሀገርና ህዝብ መሰረታዊ ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ ምን ያክል ግዙፍ እንደሆነና ይህን ችግር መቋቋምም የጋራ ሀላፊነት እንደሆነ በመገንዘብ በአንድነት የመቆሚያው ጊዜ እና እያንዳንዳቸውም ያላቸውን ታላቅ ጥበብ ለሀገር ማዳኛ ሊጠቀሙበት የሚገባው አሁን መሆኑን በመረዳት ሀላፊነታቸውን ለመወጣት እጣዳፊ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል። ታላቅነታቸውንና አርቆ አሳቢነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል።ነገ ሳይሆን ዛሬ፡ ይህ ነው ከመሪ የሚጠበቀው።

ኢትዮጰያን ፈጣሪ ይባርክ

©

1 Comment

  1. ይህ ጽሁፍ ጥሩ የ ንቃት ደወል ነው። አሁን አሁን ጦርነት አይቀሬ ይመስላል። ስለዚህ መንግሥት ህዝባችንን ለተደቀነብን አደጋ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ተዘጋጅቶ መገኘትን የመሰለ ጥሩ ነገር የለም። ዋስትና ነውና።

    ህዝባችን እንደ አባቶቻችን ህብረት ፈጥሮ ጠላቶቻችንን ለ መመከት ሳይውል ሳያድር መዘጋጀት አለበጥ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.