ሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

5

“እኔ አልዋሽም፤ ውሸት የሚባል ነገር አልወድም!” የሚል ሰው ካለ የመጀመሪያው ውሸታም እሱ ነው፡፡ ለበጎም ይሁን ለክፉ ሁላችንም እንዋሻለን – በዚህ አንወሻሽ፡፡ ማጋነንም ውሸት ነው፤ እውነትን ላለመናገር መታቀብም ውሸት ነው፤ ላለመዋሸት ዝምታን መምረጥም ውሸት ነው፤ የቅለት ክብደቱ ደረጃና ዓላማው ይለያይ እንጂ ሁላችንም እንዋሻለን፡፡ ውሸት ወይም ሀሰት የሕይወት አንዱ ቅመም ነው – ጠቃሚ ነው ማለቴ ግን አይደለም፡፡

አሁንም ቢሆን “ሰማይ ዝቅ፣ መሬት ከፍ ይላሉ እንጂ እኔ ዋሽቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም ቢሆን እመብርሃን ታጥፋኝ አልዋሽም” የሚለኝ ካለ መብቱ ነው፡፡ እኔ ግን ወደተነሳሁበት ጉዳይ ገባሁ፡፡ በነገራችን ላይ የሦስቱም የውሸት ደረጃ አንዱ ከሌላው ሳይበልጥ ተመሳሳይ ሚዛን በመርገጡ ሦስቱም አንደኛ ናቸው፡፡ ሌሎች ባለደረጃዎች ከአራተኛ ይቀጥላሉ፡፡

ውሸት ደረጃ አለው፡፡ ትልልቅ ውሸቶች አሉ – ሰውን ከሰው የሚያቆራርጡ፤ የሚያገዳድሉም ጭምር፡፡ ለጨዋታና ለፈገግታ ሲባል የሚሰነዘሩ ቆይቶ ግን እንዳስፈላጊነታቸው ሀሰት መሆናቸው የሚነገሩ ትንንሽ ውሸቶችም አሉ፡፡ በጓደኛሞች መካከል ብዙ እንተዛዘባለንና ስለውሸት ያለን ግንዛቤ የሚናቅ አይመስለኝም፡፡ ከትልልቅ ውሸታሞች መካከል ሦስቱን አሁንና ዛሬ በ2013 የትንሣኤ ዋዜማ ላይ ላስተዋውቃችሁ ነውና ተዘጋጁ፡፡ በሪከርድ ደረጃ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስን መዝገብ ያለተቀናቃኝ በተመሳሳይ ነጥብ በአንደኝነት የሚወጡትን ውሸታሞች ማለቴ ነው እንጂ ከደረጃ አራት ጀምሮ የሚሰደሩትን ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገራት ውሸታሞችን ካየን ዘርዝረን አንጨርሳቸውም፡፡ በተለይ በዚህ ባለንበት ዘመን ውሸት እንደፋሽን ሆኖ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አልሆነም፡፡ ሙስናም እንደዚሁ፡፡ ማንም ይሁን ማን፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣንም በለው የበታች ሠራተኛ ከመሬት እየተነሣ እንደጣቃ ሲቀደድ ማየት የዘመኑ አሳዛኝና አሳሳቢ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ተተኪው ትውልድም ይህን መረን የለቀቀ ዘመን አመጣሽ መጥፎ ልማድ እየተከተለ በመጥፋት ላይ ይገኛል፡፡ የማያሳፍረው እያሳፈረ፣ የሚያሳፍረው የልብ ልብ በመስጠት እያጀገነ ትውልድ ሲዘቅጥ በስፋት ይታያል – በሃይማኖቱም በዓለማዊውም፡፡

ውሸት ምን እንደሆነ ታውቁታላችሁና ስለምንነቱ መናገር አያስፈልገኝም፡፡ ዋሾነት ግን ከተፈጥሮ ባሕርይም፣ ከጤና መቃወስም፣ ከተጋቦትም፣ ከኅልውና ማስቀጠያነትም፣ ከቅጣትና ወቀሳ ማምለጫም፣ ከዐመልም (ከባሕርይ ጋር ይቀራረባል) ወዘተ. ጋር ይገናኛል፡፡ እኔ አሁን የምጠቅሳቸው ውሸታሞች ግና ይበልጡን ከጤንነት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ምን ማለቴ ነው – እነዚህን ዓይነት ሰዎች ካልዋሹ ይታመማሉ፤ ደጋግመው ካልወሻከቱ ህመማቸው ይጸናባቸውና ምናልባትም እስከሞት ሊደርሱ ይችላሉ – እነዚህን ሰዎች የጤና ሣይንሱ “Pathological liars” ይላቸዋል – መለስ ዜናዊም የዚህ ደዌ ተጠቂ ነበር፤ ምን እሱ ብቻ ሁሉም ሕወሓታውያን የዚሁ ልክፍት ሰለባዎች ናቸው፡፡ ልናዝንላቸው ይገባናል፡፡ ችግሩ በሥልጣን መሰላል እንደምንም ተንጠላጥለው ወደላይ ከወጡና ትልቁን ሀገርን የመምራት ቦታ ከያዙ የሚመሯትን ሀገር ድምጥማጧን እስከማጥፋት መድረሳቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ሀገራቱና ሕዝቦቻቸው ወዮላቸው! አንድ የሀገር መሪ ጨዋ ሲሆን የሚመራው ሕዝብም ጨዋ ይሆናል ተብሎ ይገመታልና የመሪ አመራረጥ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አለዚያ መሪው ዋሾ ዱርዬ፣ ተመሪውም ቀልማዳ ዱርዬ ይሆኑና ሀገሪቷ የለየላት የኳስ አበደች ሀገር ትሆናለች – ልክ እንደኛዋ፡፡

ከሦስቱ አንደኛ ውሸታሞች ሁለቱ ከኢትዮጵያ ሲሆኑ አንዱ ከውጭ ሀገር ነው፡፡ ከውጪው ልጀምር፡፡ ኢራቃዊ ነው፡፡ በሣዳም ሁሤን አገዛዝ ዘመን ብቸኛው ክርስቲያን ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበር፡፡ አሊ ሀሰን አብድ አልማጂድ አል ቲክሪቲ ይባላል፡፡ በኩርዶች ላይ የኬሚካል የጦር መሣሪያ በመጠቀሙ ምክንያት ኢራቃውያን “ኬሚካል አሊ” በሚል ቅጽል ስም ይጠሩት ነበር፡፡ የአሜሪካ ጦር ባግዳድን እየከበበ ባለበት ወቅት ይህ ሰው “ባግዳድ የአሜሪካ መቀበሪያ ትሆናለች” እያለ ዓለምን በሣቅ ጦሽ ያደርግ የነበረ ሰው ነው፡፡ እውነቱን እኮ ያውቀዋል፡፡

ቀጣዩ ዋሾ የኛው ጉድ አቢይ አህመድ ነው፡፡ ክርስቶስ “አፌን በምሣሌ እከፍታለሁ” እንዳለ አቢይም “አፌን በሀሰት ንግግር እከፍታለሁ” ብሎ የሰባተኛነት ንጉሥነቱን የእናቱን ትንቢት ለማስፈጸም ቆርጦ ሳይነሣ አልቀረም፡፡ ሰውዬው ውሸታምነቱ ሳያንሰው የሚናገረው ሁሉ የትናንቱ ከዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ደቂቃ ንግግሩ ከሁለተኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሴከንዶች ንግግሩ ጋር እርስ በርስ ይጋጫል ወይም ይላተማል፡፡ ገራሚ ሰው ነው!!

ሦስተኛው አንደኛ ዋሾ የወያኔ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ነው፡፡ ይህም ሰው ልክ እንደ ኬሚካል አሊ “መቀሌ የወራሪው አቢይ ጦር መቀበሪያ ትሆናለች” በሚለው ንግግሩ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን ከአንዱ ጎሬው ውስጥ ሆኖ ብዙ የአማራ ልዩ ኃይሎችን በ10 ደቂቃ ውስጥ እንደደመሰሰና በርካታ የኤርትራ ክፍለ ጦሮችንም ከ20 ምናምን ታንኮች ጋር ድባቅ እንደመታ፣ በአሥር ሽዎች የሚቆጠሩ የጠላት ወታደሮችን እንደገደለና እንደማረከ እየተናገረ ነው – “ለአፍ አቀበት የለውም” መባሉ እንዴቱን ያህል ትክክል አባባል መሰላችሁ፡፡

እነዚህ ሦስት ውሸታሞች አእምሯቸው በተለዬ ሁኔታ ካልተመረመረና መንስኤው ካልታወቀ ጦሱ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ኅልውና ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከሀሰት ንግግር እግዜር ይጠብቀን!!

 

 

5 Comments

 1. ለሰላሳ አመታት እኛ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በብድር እየተበደርን ከውጭ መንግስታት ቤተሰብ መመስረቱን ተያያዝነው ፤ልጆችም ያለ እቅድ በብዛት እየወለድን ማሳደጉን ተያያዝነው። ልጆች በብዛት እየወለድን ስንመጣ ልጆቻችንን ለመቀለብ ስንሞክር የተበደርነውም አልበቃን አለን። ብድሩንም መልስን ለመክፈል ስለተሳነን ይኸው እንደ ሀገር ትልቅ ፈተና እና ችግር ላይ ወደቅን። ፈተናው እጅና እግር አውጥቶ የእያንዳንዳችንን በር አንኩዋኩቶ ገብቶም እያለ ፤ ገበናችንን እየደበቅን አሁንም በውሸት የህልም አለም መኖሩን ተካንንበት ፤ አብይ አህመድም የእኛን የውሸት ምኞት መውደድ አውቆ ተጠቀመበት። ውሸት እየመገበን ቀጠለ ፤ እኛም ውሸት እንደሆነ ልባችን ቢያውቀውም እውነታውን መጋፈጥ ስለማንፈልግ ለአብይ አህመድ ማጨብጨቡን ቀጠልንበት። አብይ አህመድ እውነት ቢናገር የአብዛኛዎቻችንን የእርሱ ደጋፊዎች ድጋፍ እንደሚያጣ ስለሚያውቅ ውሸቱን ተካንነበት።

  በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤት ሆንዋል ልጆቻችንን የሚቀልበው ፤ ልጆቻችንም አድገው ስራ ፈት ስለሆኑ ብድሩ ከእነወለዱ ጣራ ሊነካ ተቃርብዋል። እኛ እውነቱን ባንነግራቸውም ልጆቻችንም እየገባቸው መጥትዋል በውቨት እና በጉራ በተመሰረተ ጋብቻ ፤ የገዛ ልጆቻችንን የወደፊት ዕጣ በብድር እያስያዝን ባገኘነው ብድር እንደሆነ የኖርነው ፤ አሁን ላይ አዲሱ ትውልዶችም ይህንን እንዳያውቁብን አብይ አህመድን አንግሰን እየዋሸልን እውነቱን ከልጆቻችን እንዲደብቅ ሞከርን ፤ ሰርተን አምርተን ሳይሆን እንዲሁ በብድር በመጣ ገንዘብ እንደሆነ የሀገር ባጀት ሲደጎም የነበረው እንዲታወቅ ስለማንፈልግ ይኸው እየገደለንም አብይ አህመድን ማሞካሸቱን ቀጠልንበት ። ምዕራባውያንም ለኢትዮጵያ ያበደሩት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ስለሚመኙ ምንም ያህል የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፤እነርሱ የሚታያቸው ያለው በትግራይ ውስጥ ያለው የሰብዐዊ መብት ጥሰት ብቻ ሆንዋል ፤ ምክንያቱም በትግራይ ውስጥ በሚካሄደው የሰብዐዊ መብት ጥሰት ኤርትራም ስለተሳተፈችበት ነው ፤ ብድር የሌለባት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ መጣልም ስለሚችሉ የትግራይን ህዝብ ሞት ከአማራው ሞት በላይ አሳሳቢ ነው እያሉን ይገኛሉ ምዕራባውያን ፤ ስለ አማራው ዘር መጨፍጨፍም ለማወቅም ጥረት አያደርጉም ያሉት።

 2. ማስተካከያዎች
  1። አል፟ቲክሪቲ (Chemical Ali) “በሣዳም ሁሤን አገዛዝ ዘመን ብቸኛው ክርስቲያን ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበር፡፡”
  አል፟ቲክሪቲ (Chemical Ali) ሙስሊም ነበር። አንተ የምትለው ብቸኛው ክርስቲያን የባዝ ፓርቲ አባል እና ከፍተኛው ባለስልጣን ጣሪቅ (ታሪክ) አዚዝ ይባላል። በአልም አቀፍ ደረጃም የሚጠላም ሰው አልነበረም። የሳዳም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠ/ሚር ድረስም ደርሶ ነበር።
  2። አል፟ቲክሪቲ (Chemical Ali) “ባግዳድ የአሜሪካ መቀበሪያ ትሆናለች” እያለ ዓለምን በሣቅ ጦሽ ያደርግ የነበረ ሰው ነው፡፡
  ይህ ሰው አልቲክሪቲ አይደለም። መሃመድ ሰኢድ አልሳሃፍ ይባላል። በወቅቱ የኢራቅ የማስተወቂያ ሚኒስትር ነበር። ታዲያ ከባግዳድ መያዝ በኋላ በዓለም ሁሉ፣ በአሜሪካ ዜጎች ሳይቀር፣ እኔንም ጨምሮ በጣም ተወዳጅነትን አትርፎ “እንዳታስሩት” እስከመባል ድምጾች ተሰምተው ነበር።
  3. አልሳሃፍ “ኬሚካል አሊ” ሳይሆን “ኮሚካል (Comical) አሊ” ተብሎም ተጠርቷል።
  በምርጫ ብቻ!

 3. አንተ እራስህ ትልቁ ውሽታም ነህ ስም አጥፊ ነህ የተከበረውን የአገር መሪ ስትሳደብ ልአፍህ ለከት የለህም ቁጭ ብለህ ወሬ ከምታወራ ሰፈርህ ያለውን ቆሻሻ አንሳው

 4. ከድር ሰተቴ ለሰጠኸኝ ማስተካከያ ከልብ አመሠግናለሁ። ጊዜው ራቀና ጭንቅላትም ላላና ስህተቱ ሊከሠት ግድ ሆነ። ቅን አንባቢ እንደዚህ ቢያርም ቢይንሥ የጸሐፊዎች ቀሪ ጽሑፎች የመሥተካከል ዕድል ይኖራቸዋልና ይህ ልምድ ግሩም ነው።
  ብዝተረፈ “በምርጫ ብቻ”

 5. በመጀመሪያ ለከድር ሰተቴ የማስተካከያ ሀሳብህ ምስጋና ይድረስሕ። አምባቸውም የውሸት አይነቶችን መዘርዘሩ መልካም ቢሆንም በሁም ዘንድ ከመታወቅ አልፎ በተግባርም ስለሚፈጸም ትንታኔው ባላወቅኸው ታሪክ ገብተኽ! ከከድር የተሰጠውን እውነተኛ ማስተካከያ ሀሳብ ማለቴ ነው። ለሌላው ሳይሆን ” ለአንተ ጉድ የሆነብህ አቢይ አህመንድን” ለመሳደብ ስትል አንተኑ ቀጣፊ፤አንተኑ የማውቅ ታሪክ ፈትፋች እና ከአለህበት ደረጃ በታችም አያደረገኽ በመሆኑ በዉነተኛ ታሪክ ተመርኩዞ መጽፉን ልመድበት።እንዲሁም ስህተቱ ሊከሰተ ግድ ሆነ ከማለትም አለማወቅህን ማመኑም ታላቅ እውቀት ስለሆነ አለማወቅህን እመንበት።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.