ኢትዮጵያ እየነደደች ነው!!! (ኡመር ሽፋው)

1

2019 9 16 churchattackfinal

(ኡመር ሽፋው – May 3, 2021)

ባለፉት ስልሳ ዓመታት በኦሮሞ ሊሂቃንን ኋላም ላይ በትግራይ ተገንጣዮች በአማራው ህልውና ላይ የተጀመረው ዘመቻ ዛሬ ላይ ውጤቱን እያየነው ነው። በተለይ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተቀናጀ መልክ አማራ እንደበግ በመታረድ ላይ ይገኛል። በቅርቡ አንዳንዶች ባቀረቧቸው ትንተናዎች መሠረት ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የአማራን ዘር ከማጥፋት በስተጀርባ እጁ እንዳለበት ተጠቁሟል። ከዚህ ተነስተን የሚታረደውን አማራ እስከአሁን ድረስ በስም ጠርቶ ግድያውን ያላወገዘበት ምክንያት የሆነኝ ብሎ ግድያውን ማስቆም ስለማይፈልግ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚያዳግት አይሆንም። የሆነው ሆኖ እጁም ኖረበት አልኖረበት፣ እነሺመልስ አብዲሳ ከሱ ትእዛዝ ውጭ አደረጉት አላደረጉት፣ በአማራ ላይ የዘር ፍጅት ሲፈፀም ጠ/ሚንስትሩ የሃገሪቱ መሪ ስለሆነ በምንም መንገድ ከተጠያቂነት አያመልጥም።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለችግራችን ምርጫ እንጂ ሌላ መፍትሄ የለም በማለት ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት ፈቃደኛ አለመሆኑ የሚያመላክተው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን የአማራን የህልውና ጥያቄ ለማድበስበስ እንደሚፈልግ ነው። ከአሁን ቀደም ከመስከረም 30/2013 በኋላ መንግሥት የለም ያሉት ላይ በተለያየ መንገድ እርምጃ እንዳልወሰደ ሁሉ፣ ዛሬ “የለም ጊዜህን አራዝመህ ግዛን፣ ግን የአማራውን መገደል አሁኑኑ አስቁምልን” ሲባል፣ እንቢ አሻፈረኝ፣ ምርጫ መደረግ አለበት ማለቱ እንደተጠረጠረው የአማራን መጨፍጨፍና ተጠራርጎ ከኦሮሚያ ክልል መውጣት ያምንበታል ማለት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በእርግጥም ከባድ እንዳይሆን ያደርገዋል።

ምርጫ እንደታቀደው ቢካሄድ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወይም የኦሮሞ ብልፅግና በአጋሮቹና እንደኢዜማ ባሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማካይነት የበላይነቱን እንደሚይዝ ይታመናል። ይህ ማለት ጠ/ሚንስትሩ ያራመደው የኦሮሙማ (የተረኝነት) ፕሮጀክት እስካሁን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በወታደራዊ መስኮች በመጓፈፍ ያገኘውን የበላይነት እንዳለ ሊያቆይ ከመቻሉም በላይ ፕሮጀክቱን የማጠናከርና የማስፋፋት እድሉም ከፍተኛ ይሆንለታል ማለት ነው። ሌላ አማራጭ ከሚባሉት ውስጥ ለምሳሌ ሁሉን አካታች የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ስምምነት ላይ ቢደረስ፣ እስካሁን በተደረገው የኦሮሙማ መስፋፋት ላይ ጥያቄ ይቀርባል፣ ብሎም ድርድር እንዲደረግ ግድ ይላል ማለት ነው። ይህ ጠ/ሚንስትሩንም ሆነ ሌሎቹን የኦሮሞ ሊሂቃንና የጠ/ሚንስትሩ የቅርብ አማካሪዎች እነሌንጮ ለታን፣ ዲማ ነገዎን፣ ሌንጮ ባቲን እንዲሁም የኦሮሞ ብልፅግናን አመራር ሥጋት ላይ እንደሚጥላችው ግልፅ ነው። ከዚህ በኋላ 3000 ዓመት ኦሮሞው ይገዛል የሚሉት እነሌንጮ ባቲ እስካሁን በደባ ባገኙት ትርፍ ላይ እንዲጨመርላቸው እንጂ በምንም ታእምር እንዲቀነስባቸው አይፈልጉም። እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበቤ እንዝህላልነትና በአማራ ብልፅግና አጎብዳጅነት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለይም የኢዜማ አሳልፎ ሰጪነት በኦሮሙማ ፕሮጀክት አዲስ አበባ እየተዋጠች ስለሆነ ለወደፊት የጋራ መዲናችን ለድርድር እንድትቀርብ ስለማይፈለግ እነዶ/ር አብይ አህመድ ከምርጫ ሌላ ስሌሎች አማራጮችን መስማትም ሆነ በረጅም ዘንግ መንካት አይፈልጉም።

የሽግግር መንግሥስትን አስመልክቶ እነዶ/አብይ አህመድ የማይደግፉበት ሌላው ምክንያት በሽግግር መንግሥት ውስጥ ወይም ከዚያ በኋላ ሰላም ሰፍኖ ሁሉም በሚስማማበት ወቅት ሰላም ቢደረግ አማራው በተለይ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችን አስተባብሮ የበላይነት ይይዛል የሚል ፍራቻም ስላላቸው ነው። አማራው ካወቀበት የበላይ የመሆንም ወይም የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ሕወሃትን ተክተው ሁሉን ነገር የተቆጣጠሩት የኦሮሙማ አራማጆች የደቡቡን ማህበረሰብ ከመከፋፈል አንስቶ በተለያየ መንገድ ስለተተናኮሱትና በየጊዜው ስለሚያስፈራሩት ከአማራው ጎን እንደሚቆም የሚያጠራጥር አይደለም። ቢሆንም በሃሠት ትርክት የተተበተበው የኦሮሙማ እሳቤ ማእከል ያደረገው አማራን ማድቀቅ፣ መስበር ወይም እንዳልነበር ማድረግ ስለሆነ መጬም ይሁን መቼ አማራው የበላይነት ቢቀዳጅ እነ/ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ዛሬ እንደሚያወሩት ሳይሆን ያቺ ቀን ስትመጣ አራትኪሎን አሳልፈው ለማንም እንደማይሰጡ ግልጽ ነው። በተለይም እነሽመልስ አብዲሳ ኢትዮጵያን ኦሮሞ እናስመስላታለን ብለው ስለፎከሩና በሥራም ላይ የምናየው ይኸንኑ ስለሆነ በቁጥጥራቸው ሥር ያለውን መከላከያና በተደጋጋሚ ያሠለጠኑትን ልዩ ሃይል ተጠቅመው በአምባገነንነት በስልጣን ላይ እንደሚቆዩ ወይም ካልተመቻቸውና ጫና ከበዛባቸው “የኦሮሚያ ሪፐብሊክን” እንደሚያውጁ ሳይታለም የተፈታ ነው። እነዶ/ር አብይ አህመድ የሽግግር መንግሥት አጥብቀው የሚቃወሙት አሁን ካለው የበላይነታቸው ጋር የተሳሠረውን ጥቅማቸውን ሊያጡ ስለሚችሉ ብቻ ሳይሆን፣ በይበልጥ ግን የበታችነት ስነልቦናቸው ስለማይፈቅድላቸውም ጭምር ነው።  ስለዚህ ‘ምርጫ’ ወይም ‘ሞት ማለታቸው ሊገርመን አይገባም።

ምርጫው አሁን መሆን አለበት  ከሚለው እሳቤ ጀርባ መጪው ጊዜ ከዚህ ከአሁኑ ጊዜ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ እንዳለ መገመት ይቻላል። ከምርጫው በኋላ የሃገሪቱ ቀውስ እንደሚባባስ ማመንን ያመላክታል። የሚባባሰውም አሁን የኦሮሙማ ፕሮጀክት የደረሰበት ደረጃ በይዞታም ሆነ በባህል መስፋፋቱን፣ ስልጣን መጓፎፉን፣ የኢኮኖሚን አውታሮች በፍፁማዊነት መቆጣጠሩን አስመልክቶ ወደሚቀጥለው አርከን መሸጋገሩ ስለማይቀርና፣ ሃገሪቱ ከውጭ ጠላቶች እየገጠሟት ያሉት ወከባዎች እንደተጠበቁ ሁነው፣ ከአማራውና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጉዞው ብዙ ፈተና ሊገጥመው ስለሚችል ነው። ስለሆነም ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ስለሚያውቁና በተወሰነ ደረጃ ሕጋዊ ቁቡልነት ያስገኝልናል ብለው ስለሚያምኑ  እንዲሁም ወደሚቀጥለው የኦሮሙማ ምዕራፍ ስለሚያሸጋግራቸው ምርጫው ለነሱ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው። ስለዚህም ነው አገሪቱ እየነደደች ባለችበት ሰዓት ምርጫ ወይም ሞት ብለው የተነሱት!!!

የምርጫ ፅንሰሃሳብ የዲሞክራሲ እሳቤን ያዘለ ነው። ማለትም ሁሉም ዜጋ የዜግነት መብቱ ተጠብቆ የሚሳተፍበት ማለት ነው። ዛሬ በሃገራችን የሰላም እጦት ምክንያት በአብዛሃቸው የሃገሪቱ ክፍሎች ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ስለሆነም ይህ ምርጫ ቢካሄድ እጅግ በጣም አነስተኛ የሆነውን ሕዝብ ፍላጎት ብቻ ስለሚያንፀባርቅ፣ ቅቡልነቱ ከሕግም ሆነ ከሞራል አንፃር ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል። በስተቀር የአናሳውን የምርጫ ፍላጎት በብዙሃኑ ላይ መጫን ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መንገድ የሚመረጥ የፌደራል መንግሥት ይቅርና ብዙዎቹ የክልል መንግሥቶች ውስጥ ምርጫውን አብዛሃኛው ሕዝብ ስለማይሳተፍበት የተሟላ የህዝቡን ህጋዊ ይሁንታ ወይም ቅቡልነት ሊያጎናጽፍ አይችልም። ቢበዛ ቢበዛ ይህ ምርጫ ሰላም በሰፈነባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በወረዳ ደረጃ ለሚመረጡ የወረዳ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ቅቡልነት ሊያላብስ ይችላል ይሆናል።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ በንዴት …. መጮህ መፍትሄ አይሆንም፣ መፍትሄው ምርጫ ብቻ ነው፤ በማለት በአማራ ክልል ከተሞች “አማራን መግደል ይቁም” በማለት ድምፁን ያሰማውን ሰልፈኛ የወረፈበትን አባባሉን ያየን እንደሆነ ምርጫው በሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን ከአራት ኪሎ በሚወጣ ትእዛዝ እየተጫነ እንደሆነ ያመላክታል። ማለትም ምርጫው ከጅምሩ ዲሞክራሲያዊ አይደለም ማለት ነው። ሕዝቡ ሳይወድ በግድ ምርጫው በጉሮሮው እየተሸጎረበት ነው ማለት ነው። ስለሆነም ይህ የታሰበው ምርጫና ዲሞክራሲ የሚኖራቸው ግንኙነት የጠራ አይደለም ማለት ይቻላል።

በሃገር ውስጥም ከሃገር ውጭም የሚገኙ የተለያዩ የሊሂቃን ስብስቦች ባለፉት ሶስት ዓመታት በሃገራችን ላይ የዘነበውን የመከራ ዝናብና የሕዝቡን ትዕግስት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በምርጫ ፋንታ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከአሁን ቀደምም ሆነ በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ወደሰላምና ዲሞክራሲ ለማሸጋገር በራሱ በጠቅላይ ሚንስትሩ የበላይ መሪነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ምሁራኖችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን ወዘተ ያካተተ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት እና የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፋንታ ሁሉም በጋራ እንዲወሰን ሃሳብ አቅርበውለታል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን የኦሮሙማ ፕሮጀችት ከሽግግር መንግሥት እንደማያተርፍ ስለገባውና ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲያወራ ቢያስደምም በግልጽ ወገንተኝነቱ ስለባሰበት በመደጋገም እንቢ አሻፈረኝ እንዳለ ይገኛል። ስለሆነም በየዕለቱ አማራው በአሰቃቂ ሁኔታ እየታረደ፣ በውጭና በውስጥ ጠላቶች ቅንጅት ኢትዮጵያ እየተወረረች፣ እየተዋከበችና እየነደደች ትገኛለች !!!

 

 

1 Comment

  1. በእነዚህ የዘር ጭፍጨፋዎች የጠፉት መተኪያ የሌላቸው የአማራዎች ህይወት አሳዛኝነት እና አሳሳቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በእነዚህ በቅርቡ የአማራ ዘርን ማጥፋት በሚያክያሂዱት የእሳት ማንደድ ተቃጥለው እየጠፉ ካሉት ሀብት እጅጉን የሚበልጥ ሀብት የሚጠፋው በዝርፊያ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል። ከመከላከያ የአንድ ወር ባጀት የበለጠ ገንዘብ ይኸው እነዚህ ዘራፊዎች በአንድ ቀን ዝርፊያ ሊያካብቱ በቅተዋል ። በሳምንትማ ምን ያህል እንደሚዘርፉ ይታያችሁ። ባንክ ቤቶችን ፣ የመንግስት እና የግል ተቋማትን በመዝረፍ ተቆጥሮ የማያልቅ ሀብት ለማግኘት እና ይዘው ለመሰወር በቅተዋል ። ይህም የሚያሳየው የዘር ጭፍጨፋን ያዘለ ውንብድና ሌብነት እንደሆነ ነው እየተካሄደ ያለው። በእሳት ሀገሪቷን የሚያነዱትም ምንም ሀብት ሳይዘረፍ የተቃጠለ ለማስመሰል ነው እንጂ በስርቆት የተዘረፈው ሀብት ስፍር ቁጥር የለውም። የፌደራል ፖሊስ እና መከላከያም ጥቃት በተሰነዘረባቸው ቦታዎች ደርሰው ዘራፊዎቹን ከለላ እየሰጡ ስላስመለጡዋቸው ዘራፊዎቹ ከእነ ዘረፉት ሀብት የደረሱበትን ለማወቅ አልተቻለም። በተሰረቁ ከባድ መኪናዎች እየተዘዋወሩ የተዘረፈ ሀብት እየጫኑ ማምለጣቸውም አሁን ለደረሱበት የገንዘብ ጥንካሬ አብቅቶዋቸዋል። የኢትዮጵያ መከላከያና የፖሊስ ተቋማትም ጥንካሬ ሳስቶ ሳስቶ ይኸው አሁን ለአለንበት የደከመ አቅም የበቁት ከዘራፊዎቹ ጋር በገንዘብ ትስስር ስላላቸው ነው። አሁን ላይማ የዘረፉትን ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውሩ ምስክር እንዳያያቸው መንገድ ላይ የተገኙ ተጉዋዦችንም እያስቆሙ መግደሉን ተያይዘውታል። ሌባን ሌባ ካላሉት የሰረቀውን ይዞ ተጨማሪ እየዘረፈ ፤ ሊጨምርም ስለሚሞክር ይታሰብበት።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.