በኢትዮጵያ ማንነት ላይ በተመረኮዘ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ (Genocide) በመቃወም የተሰጠ የአቋም መግለጫ

toronto

እኛ የኢትዮጵያ ማኅበር በቶሮንቶና አካባቢው አባላት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ በውድ አገራችን በመተከል፣ በቤንሻንጉል፣ በምዕራብ ኦሮምያ፣ በአጣዬና ሌሎችም ኣካባቢዎች በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ከፍተኛ የሆነ ማንነት ላይ ያተኮረ የዘር ማጥፋት ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን በተደጋጋሚ እየሰማን ነው። ይህም በመሆኑ ከምንም የላቀ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲካሄድ ለሚመለከተው ሁሉ ጩኸታችንን ማሰማት ግዴታ ሆኖ አግኝተነዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምንሰማው በቁጥራቸው ከልክ በላይ የሆነ ሰላማዊ ስዎች ከምንም ነገር ውስጥ የሌሉ ንጹሐን ግለሰቦች፣ ወንድና ሴት አዛውንት፣ ጎልማሶችና ወጣቶች ልጆች ሕጻናትም ሳይቀሩ ከየቤታቸው እየተወሰዱ መገደላቸውን እየሰማን ነው። በተለይም በአማራው ብሄረሰብ ላይ የሚፈጸም ዘር ተኮር ወይም ጀኖሳይድ (genocide) መሰል ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን ስንሰማ ሁኔታው ለአገሪቱ የወደፊቱ አመራርና አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል በጉልህ ግልጽ ሆኖ ይታየናል። ይህም በአገሪቱ ላይ በቀላሉ የማይታረቅ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ ባለበት ከፍተኛ ሃላፊነት መሠረት መንግሥት ባስቸኳይ እርምጃ መውሰድ የሚገባው መሆኑን እንረዳለን።

ከዚህም በላይ በጠቅላላ ሙሉ መሣሪያ ታጥቀው የሚዘዋወሩ ሽብርተኞች አገዳደላቸው በጣም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ፣ ማለትም የከተማው ሰላማዊ ነዋሪዎች ሌሊት በተኙበት በማይታሰብ ሰዓት መደበኛ በሆነ የጦር መሣሪያ ታጥቀውና በተጨማሪ በፍጹም ጭካኔ በተሞላበት በዘግናኝ አኳኁዋን በቆንጨራ መቆራረጥና መግደል እንዲሁም ቤት ማቃጠልና አባሮ ማፈናቀል፣ በመሆኑ በጣም ዘግናኝ ድርጊት እየተካሄደ መሆኑን ተገንዝበናል።

በአገራችን ይህን ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ከጣሊያን ጊዜ ወዲህ በፍጹም ታይቶም ተሰምቶም የሚታወቅ አይመስለንም። ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ ወንጀለኞች፤ በሕፃናት፣ በልጆች፣ በአዛውንትና ምንም ነገር ውስጥ በሌሉ ንጹሐን ግለሰቦችና ገበሬዎች ላይ ባልተዘጋጁበት በየቤታቸው በሌሊት እየሄዱ ግድያ የሚፈጽሙ፤ በግላቸው ፈሪዎችና የሰው ኅልውና ምንነት ያልተረዱና ያልሰለጥኑ ሰዎች መሆኑን ከጭካኔያቸውና ግድያቸው መገመት ይቻላል።

እዚህ ላይ ጉዳቱ ለደረሰባቸውና በሞት ለተለዩት ወገኖቻችን ሁሉ ጥልቅ ሃዘናችንን ልንገልጽ እንወዳለን። ችግሩ ከመጠን በላይ የተወሳሰበ በመሆኑ በአስቸኳይ አስፈላጊው ነገር ታቅዶ ወንጀለኞቹና ተባባሪዎቻቸው ላይ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር አገራችን አልተፈለገ ችግር ውስጥ እንዳትገባ እጅጉን አሳስቦናል። በአሁኑ ወቅት በጣም ጭቆና ከበዛበት የኢሕአዴግ አገዛዝ አገራችን ተላቃ በአዲስና ዴሞክራሳዊ ሥርዓት ለመመራት ጥረት በሚደረግበት ጊዜ ይህን ዓይነቱ የወንጀለኞች መስፋፋትና የሕዝቡን ሰላም ማደፍረስ ለአገሪቱ ሂደት ከፍተኛ ዕንቅፋት መደንቀሩ ግልጽ ይመስለናል።

የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ ዜጎች ተዘዋውረው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ሠርተው ካልኖሩ ሀብት ንብረት ካላፈሩና ሐብታቸው ካልተጠበቀላቸው፣ የሃይማኖታቸውና የግል እምነቶቻቸው ቦታ ካልተከበረ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሊሆን በማይገባ መልኩ መብታቸው የተጣሰባቸው መሆኑን ያሳያል። የፌዴራል መንግሥትም ዋናውን ግዴታውን ባለመወጣቱ ከተጠይቂነት ሊያመልጥ አይችልም። የራሱም ሕልውና ቢሆን አጠያያቂ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

ስለሆነም ባለበት የዜጎቹን ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነትና ተግባሩ በመሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥት የሚከተሉትን እንዲያስፈጽም በአንክሮ እንጠይቃለን።

  1. መንግሥት የወንጀሉን የክፋት ጥልቀትና ለዜጎቹ በገባውን ኃላፊነት ተገንዝቦ ባስችኳይ ቁርጠኝነት ባለው ሁኔታ ግዴታውን እንዲወጣ

 

  1. የተለያየ ዓይነት መሣሪያ እየታጠቁ የወንጀልና ወሮበልነት ተግባር ላይ ተሠማርተው ባገሪቱ የትም ቦታ የሚገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ተፈልገው እየተያዙ የሚገባቸውን ቅጣት እንዲቀበሉ

 

  1. ከወንጀለኞች ጋር የሚተባበሩ ግለሰቦች ተፈልገው ለፍርድ እንዲቀርቡ

 

  1. የሕዝብ ደኅንነት ለማስከበር የተሠማሩና ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ባልተወጡ የክልልም ሆነ ፌዴራል ሹማምንት ላይ ተገቢ ምርመራ ተካሂዶ እርምጃ እንዲወሰድ
  2. በአልባሌ የዘር ማጥፋት ግድያ (Genocide) በመፈጸምና በማስፈጸም ተግባር ላይ የተሠማሩ ድርጅቶች፥ ሕወሐትና ኦነግ ሸኔ፣ በአገሪቱና ዓለም አቀፍ ሕግጋት በሽብርተኝነት ተወግዘው እንዲፈረጁ

 

  1. ጉዳዩንም በሚመለከት እንደነዚህ ያሉ ወንጀሎች በእርግጠኝነት እንዳይደገሙና እንዳይስፋፉ አስፈላጊው ሥራና ጥናት ተደርጎ ማንኛውም የአገሪቱ ሕግና መዋቅር እንዲቀየርና እንዲሻሻል አጥብቀን እንጥይቃለን

 

  1. የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየመጡበት ቀያቸው እንዲመለሱና የተወሰደባቸው ሀብት ንብረት በካሳ መልክ እንዲከፈል መንግሥት በማስተባበር አስፈላጊውን እርምጃ እንዲያስወስድ

 

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.