አባይ ከዓለም አቀፍ ህግ እና ከፖለቲካ አንጻር ሲታይ – ኃያለማርያም ደንቡ

አባይ,ህግ እና ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ዕድገት እና ህልዉና ከሚነኩ ጥያቄዎች አንዱ ዛሬ የአባይ ግድብ ጥያቄ ነዉ።ከሙያ አንጻር አንድ ልበል። የዓለምን ማኅበራዊ ግንኙነት የሚያሽከረክሩ ሁለት ታላላቅ ኃይሎች አሉ።እነሱም መንግስትና የዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ድርጅቶች ይባላሉ።ከዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ድርጅቶች መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋነኛዉ እና አንደኛዉ ነዉ።በዓለም ዓቀፍ ህግ ሁለቱም መንግሥት እና የዓለም አቀፍ ድርጅት Subjects of international law ይባላሉ። የዓለም ዓቀፍ ግንኙነትን ለማቀነባበርና ለመምራት ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸዉ።መብትና ግዴታ።መንግስትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ይህንን መብት እና ግዴታ አላቸዉ።ስለ መብትና ግዴታ ስናወራ ስላ ህግ እያወራን ነዉ ማለት ነዉ።

የዓለም ዓቀፍ ህግ ልክ እንደህብረተሰብ ዕድገት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ አድጎ የመጣ ነዉ።የድሮዉ የሊጉ ኦፍ ኔሽንስ ህግ የሰለጠኑ አገሮች ህግ ተብሎ ይጠራ ነበር። የከበርቴ ሀገሮች የበላይነትን ይዞ ነበርና የአሁኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያደጉ የከበርቴ ሀገሮች የሶሻሊስት አገሮች እና ታዳጊ አገሮችን ጨምሮ የተዋቀረ ስለሆነ ከድሮዉ ሊጉ ኦፍ ኔሽንስ በዓይነት ይለያል።ይኸኛዉ ከድሮዉ ህግ አንጻር ከታየ ዴሞክራሲያዊ ነዉ። የአደጉ የከበርቴ አገሮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ይሁን በሌሎች እንደ ዓለም ባንክ በመሳሰሉት ዓለም ዓቀፋዊ መንግስታዊ ድርጅቶች የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት በመያዝ በታዳጊ አገሮች ላይ ጫና ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ እንጂ በመርህ ደረጃ የመንግስትን ሉዓላዊነትን ይቀበላሉ፡፡ የሁሉም መንግስቶች ከህግ አንጻር እኩልነትን ያምናሉ የአሜሪካን መንግሥትም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም እኩል ሉአላዊ መንግሥቶች ናቸው፡፡

ሉዓላዊ መንግስት የዉስጣዊም ሆነ የዉጫዊዉ የአገር ዓቀፍም ሆነ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት  የማካሄድ ሙሉ መብትና ግዴታ ያለዉ አማራጭ የሌለዉ ትልቅ ኃይል ነዉ። ይሁን እንጂ የታወቁ የከበርቴ የዓለም ዓቀፍ ህግ ባለሙያዎች እንደ ኸርሽ ላውተርፓክት ጂ ሸዋርትዘንበርገርና የመሳሰሉት መንግስት በዉጫዊዉ ፖለቲካ ሙሉ ሉዓላዊ ሊሆን አይችልምና ዉስናዊ ሉዓላዊነት (limited Sovereignty) ነዉ ያለዉ ይላሉ።ዘመናዊ ዓላም ዓቀፍ ህግ ይህንን አይቀበልም።መንግሥት በውጫዊ ፖለቲካውም ቢሆን ነፃ ነው፡፡ ይህንን ተናገር አትናገር፣ ይህንን አድርግ አታድርግ የሚለው ልዩ ኃይል የለም፡፡ ስለ መንግስት ሉዓላዊነት ስናወራ እንኳንስ በተፈጥሮ ሀብቱ በእሱ አስተዳደራዊ ግዛት ዉስጥ ያሉና የሚንቀሳቀሱ ተፈጥሮአዊና ህጋዊ ሰዉነቶች (Physical and legal person) እንኳን ሳይቀሩ በሙሉ በእርሱ ቁጥጥር ስር ያሉና የሚታዘዙ መሆናቸዉን መረዳት ያስፈልጋል። መንግስት እንኳንስ በራሱ ዜጋ በዉጭ አገር ዜጋም ቢሆን በግዛቱ ዉስጥ ሉዓላዊ ነዉ።መንግስት ያወጣዉን ህግ የማያከብርና የሚጥስ ከሆነ መንግስት ሁሉንም የመቅጣት ሙሉ መብት አለዉ።

የአንድ አገር የግዛት ዳር ድንበር ህዝብና የተፈጥሮ ሀብት የመንግስት ሉዓላዊነት ዋና መገለጫዎች ናቸዉ። በእነዚህ ላይ ከመንግስት በስተቀር ማንም ስለማያገባዉ ሁሉም መንግስቶች እና ድርጅቶች ይህንን መቀበልና ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ግዴታቸዉም ነዉ።አባይ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ነዉ። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መገለጫም ነዉ። እናም መከበር አለበት። መጀመሪያ ወዳነሳነዉ ወደ ዓለም ዓቀፍ ዋና አቀነባባሪዎች ስንመለስ ለብዙ ጊዜ አከራካሪ ሆኖ ቆይቶ የነበረዉ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት በቅድሚያ መመራት ያለበት በመንግስት ነዉ? ወይንስ  እንደተባበሩት መንግስታት በመሳሰሉት መንግስታዊ ድርጅቶች ነዉ? የሚለዉ ነበር። ይህ (Subjects of International law) አለቃዎች በሚለዉ አርዕስት የሚካተት በዓለም ዓቀፍ ህግ እንደ ልብና ሳምባ የሚቆጠር እምብርት ጥያቄ ነዉ።የምንኖርባት ዓለም እንደየተባበሩት መንግስታት በመሳስሉት በሚያወጣቸዉ መመሪያዎችና ህጎች መተዳደር አለባት እናም የዓለም ዓቀፍ ህግ ቀዳሚ ነዉ። ቀዳማይ በመሆኑም የሚያስተላልፋቸዉ ዉሳኔዎች ለመንግስት ግዳጃዊ መሆን አለበት ከሚሉት ዉስጥ የታወቀዉ የዓለም ዓቀፍ ህግ አዋቂ ሀንስ ኬልሰን ይገኝበታል።

ይሁን እንጂ አሁን ዓለም የምትመራዉ ሃንስ ኬልዘን በመሳሰሉት በሚሏቸው ሕጋዊ አስተሳሰቦች ሳይሆን በአዲሱ ዓለማቀፍ ሕግ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባጸደቀዉ ዓለም ዓቀፍ ህግ ነዉ።ህጎቹ በቻርተሩ ዉስጥ ተብራርተዋል።በዚህ ማብራሪያ መንግስት ቀዳሚ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተከታይ፣ መንግስት አንደኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለተኛ፣ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት አቀናባሪዎች አድርጎ አስቀምጧል። ሁለቱም አለቃዎች መብትና ግዴታቸዉ የተለያየ ነዉ። በመሆኑም በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዉስጥ ያላቸዉን ሚና አዉቀዉ መብትና ግዴታቸዉን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል።የአንድ አገር ህግ የአለም  ዓቀፍ ህግ ሆኖ ዓለምን መምራት እንደማይችል ሁሉ የዓለም ዓቀፍ ህግም የአንድ አገር ህግ ሆኖ አገርን መምራት አይችልም ።ስለዚህ ኢትዮጵያ የምትተዳደረዉ በቅድሚያ ራሷ ባወጣችዉ ህግ እንጂ በዓለም ዓቀፍ ህግ አይደለም። ይህም ማለት ኢትዮጵያ ተስማምታ በፈረመችው የዓለም አቀፍ ህግ አትተዳደርም ማለትም አይደለም፡፡ ሁለቱም የኢትዮጵያ ህግም  (municipal law) የዓለም አቀፍ ህግም ራሳቸውን የቻሉ የሕግ ክፍሎች ይሁኑ እንጂ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉም ናቸው፡፡

ስለዓለም ዓቀፍ ህግ እና ስለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲወራ በብዙ ሰዉ አዕምሮ ዉስጥ  የሚብሰለሰለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከማንም በላይ፣ ከመንግስትም በላይ የሆነና ሁሉንም  መንግስታት ማዘዝ የሚችል ኃይል አድርጎ በመቁጠር ነዉ።ሃቁ ግን እንደዚህ አይደለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅድሚያ የዓለም ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር መንግሥታት ተስማምተዉ የፈጠሩት ራሱን የቻለ ድርጅት እንጂ መንግስታትን የሚያዝ ድርጅት አይደለም ። መንግስት ሉአላዊ የተባለበት ዋናው ምክንያት በውስጥም በውጪም ግንኙነቱ እሱን የሚበልጥ እና የሚያዝ የበላይ አካል ባለመኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያዝ ምንም ኃይል የለም፡፡ ማንኛውም መንግስት ከፈለገ የዚህ ድርጅት አባል መሆን አልያም አለመሆን ይችላል። የመሆንና ያለመሆን መብት የሉዓላዊ መንግስት መገለጫዎች ናቸዉ።የምንኖረዉ በተወሳሰበ ግን አንድ ዓለም ዉስጥ ነዉ።መንግስት በጋራ እንጂ ብቻዉን የማይፈታቸዉን ዓለምዓቀፍ ችግሮች እየጎሉ መጥተዋል።የአየር መበከልና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለዚህ ጥሩ ማስረጃዎች ናቸዉ። ለእንደዚህ ዓይነቱን እና ሌሎችም የተወሳሰቡ ዓለማቀፋዊ ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለመሻት የሁሉም መንግሥቶች ትብብርን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ሉዓላዊ መንግስት በሙሉ መብቱ የፖለቲካ ነጻነቱን ጠብቆ የሚያካሂደዉ እንቅስቃሴ በራሱ ፈቃድ ከፈጠራቸዉ እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከመሳሰሉት ጋር ተቀናብሮ መስራት የዓለም ዓቀፍ ህግ መመሪያዎች ናቸዉ።የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል መሆን በዚሁ መንፈስ የሚታይ ነዉ።ኢትዮጵያ ለመስጠትም ሆነ ለመዉሰድ የዚህ ድርጅት አባል አገር ነች።

አባይን ለመስጠት ነዉ አባል የሆነችዉ ብለዉ የሚያስቡ ካሉ ጅሎች ናቸዉ። ማንም መንግስት የዚህ ድርጅት አባል ሲሆን አገሩንና ሕዝቡን ለመጥቀም እንጂ በተጻራሪው ሀገሩንና ህዝቡን ለመጉዳት አይደለም፡፡ ግብፅ ረግጦ ሲገዛት የነበረውን የእንግሊዝ የበላይነት ስሜት ተሸክማ ኢትዮጵያን በዛ መንፈስ መሳሏ ትገረማለች የፈረንጆችን ትዕዛዝ ለጥ ሰጥ ብላ እሷ ትቀበል እንጅ እኛ ኢትዮጵያንዊያኖች አንቀበልም፡፡እንደዚያ መስሏት ነው የአባይን ጥያቄ አማልዱኝ ብላ አንዴ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ለአለም ባንክ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለተባበሩት መንግስታት ፀጥታ ምክር ቤት የምታቀርበው፡፡ ኢትዮጵያ የዶናልድ ትራንፕና የአለም ባንክ ድርድር ከምንም ሳትቆጥረው አልተስማማኝም ብላ ስብሰባውን ለቃ ወጥታለች፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕና የአለም ባንክ እቅዷ አልሳካ ሲላት ጉዳዩን ለፀጥታው ምክር ቤት አቀረበች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሚናውን የሚያውቅ ድርጅት ነው ብለን አናምናለን፡፡ ምናልባት እሱም እንደ ግብፅ ዶናልድ ትራምፕና የአለም ባንክ አቅጣጫውን የሚስት ከሆነ እሱንም ምንም የምንፈራበት ምክንያት የለንም፡፡ ያውም የራሱ የሆነ ግዛትና ጦር የሌለው የተባበሩት መንግስት ድርጅትን? ኢትዮጵያ በአገሯ ላይ ከመጡባት በአይኔ መጡብኝ ነውና ማንንም አትፈራም ያደጉ የከበርቴ አገሮችም ሆነ የአለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ከመፍጠር ባሻገር የሚፈጥሩት ነገር የለምና አንፈራም፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቻርተሩ እንደተቀመጠዉ ከተቋቋመበት ዋና ዓላማዎች አንዱ ማንም በአንድ አገር በዉስጥ እና በዉጭ ስራዎች ዉስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት ነዉ።ጣልቃ ገብነት በዓለም ዓቀፍ ህግ እጅግ የተከለከለ ነዉ።ይህም በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም በሳንፍራንሲስኮ ስብሰባ ላይ የነበረዉ ትልቁ አከራካሪ ነጥብ (Matters which are essentially within the domestic jurisdiction of any state) የዉይይት አጀንዳ ሆኖ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት መቅረብ ይችላል? ወይስ አይችልም? የሚለው ነበር፤ መልሱ አይችልም ነው፡፡ በአንድ አገር መንግስት የዉስጥ ስራዎች ዉስጥ መግባት ጣልቃ ገብነት ነዉ።ግብጽ እና ሱዳን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛዉ አካል ለጸጥታዉ ምክር ቤት የአባይን ጥያቄ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጥያቄ ጣልቃ እየገቡ ነው፡፡ ጠባቂ ያላት በግ ላቷ እደጅ ያድራል እንደሚባለው ሆነና የአሜሪካንን መንግሥት ተማምነው ነዉ እንጂ በአባይ ጥያቄ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሞላ አስገዶም - ድከሚ ያላት ጥቁር ሴት እጇን ትነቀሳለች

በቅድሚያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስማማት ካልቻሉ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይሆን ለአፍሪካ ህብረት ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ የግብጽ መንግሥት በተለይ ጉዳዩን ለጸጥታ ምክር ቤት ከማቅረብም አልፋ ጦር አነሳለሁ ብላ እየፎከረችም ነዉ። በዘመናዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ማስፈራራትና መፎከር አይፈቀድም። ነገሩ ፎከሩም አልፎከሩም መታወቅ ያለበት የረጋ ዉሃችን ጣናም፣ ወራጅ ዉሃችን አባይም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸዉ። ይህም በመሆኑ በመሰረቱ ኢትዮጵያ ከማንም ጋር በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ መደራደር አልነበረባትም። ግብጽና ሱዳን የአባይን ዉሃ ተጠቃሚ ለመሆን የኢትዮጵያን መንግስት ትብብር መጠየቅ ሲገባቸዉ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት እንደ ጋራ ሀብት በመቁጠር ልማታችንን ለመግታት ጣልቃ እየገቡ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትስ? የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መንግስትን እንኳንስ በአባይ ጥያቄ በማንኛዉም  ሌሎች ጥያቄዎች ኢትዮጵያን የማዘዝ ህጋዊ መብት የለዉም ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግድቡን እንደዚህ ሙሉ፣ከሱዳንና ከግብጽ ጋር እንደዚህ ተደራደሩ ብሎ ኢትዮጵያን ማዘዝ ቀርቶ በራሱ ተነሳሽነት ስለአባይ አጀንዳ ላይ አስቀምጦ መወያየት እንኳን አይችልም ።በግብጽ ፣በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተነሳዉ አለመግባባት በቅድሚያ ችግሩን በጋራ ተወያይተዉ መፍትሄ ማምጣት ያለባቸዉ መንግስቶቹ ራሳቸዉ ናቸዉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚፈርድ ዳኛ አይደለም ።

እነዚህ መንግስታት ሳይስማሙ ቀርተዉ ከመካከላቸዉ አንዱ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢያቀርብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማድረግ ያለበት ልክ በግብጽ ላይ እንዳደረገዉ አስተያየትና ሃሳብ መስጠት ነዉ። አስተያየቱም ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር መስማማት ካልቻለች ጉዳዩን ለአፍሪካ ህብረት እንድታቀርብ ሃሳብ መስጠት ነበር።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረበዉን ሃሳብ መቀበልና ያለመቀበል የሉዓላዊ የግብጽ መንግስት መብት ነዉ። ያምሆነ ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀረበለት በአባይ ጥያቄ ላይ የሚያሳልፋቸዉ ማናቸዉም ዉሳኔዎች ለግብጽም ሆነ ለኢትዮጵያ አስገዳጅ አይደሉም።ሊሆኑም አይችሉም።ቢሆኑማ ኖሮ ጣልቃ ገብነት ይሆኑ ነበራ! ተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአባይ ላይ የሚያስተላልፋቸዉ ዉሳኔዎች ከአስተያየትና ምክር ሰጪነት አልፎ አስገዳጅ መሆን የሚችለዉ መንግስታቶቹ መስማማት፣የአፍሪካ ህብረትም ማስማማት አቅቶት ወደ ጦርነት ዉስጥ የገቡ እንደሆነ ብቻ ነዉ።እንዲያዉም እንደዚያም ሆኖ የእነዚህ መንግስታት ጦርነት ዉስጥ መግባት ለተባበሩት መንግስታት ጣልቃ መግባት በቂ ምክንያት አይሆንም።ምክንያት ሊሆን የሚችለዉ ጦርነቱ ከአካባቢ ጦርነት አልፎ የዓለምን ሰላምና ጸጥታ የሚነሳ ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነዉ።

እሳካሁን እንዳየነዉ አረቦችም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸዉና   እንደማይችሉም ነዉ።ይህም በመሆኑ አባይ ለድርድር መቅረብ አልነበረበትም።ግን ቀርቧል ወደፊት  እንጂ ወደ ኃላ ማሰብ አይኖርብንም።አገራችን ኢትዮጵያም ሁኔታዉ አስገድዷት ሊሆን ይችላል።ከስትራቴጂያዊ ጠላቶቻ ጋር ድርድር ይዛለች።ድርድሩ ፍሬያማ እንዲሆን መካሄድ ያለበት ግን አባይን እንደ ጋራ ሀብት ቆጥሮ የጋራ ሀብትን በጋራ እንጠቀም ሳይሆን የኢትዮጵያ የግል ሀብት የሆነው አባይን እንዴት በጋራ እንጠቀም የሚለው ነዉ።የግል ንብረትን በጋራ መጠቀም እና የጋራ ንብረትን በጋራ መጠቀም መካከል ብዙ ልዩነት አለ።እኛም እንደነሱ ፍትሃዊ አጠቃቀም፣የጋራ አጠቃቀም የምንል ከሆነ በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን ህጋዊ መብቱ የጋራ ሆነ ማለት ነዉ።ህጋዊ መብቱ የግል መሆኑ ቀርቶ የጋራ መሆኑን የምንቀበል ከሆነ ጥቅሙም የጋራ መሆኑን ልንቀበል ነዉ።አረቦች የሚፈልጉት እና የሚሉት ይህንን ነዉ።በአጭሩ ሀብቱ የኛ ከሆነ መብቱም የኛ ነዉ። ሀብቱ የጋራ ከሆነ መብቱም የጋራ ነዉ።

የአንድ አገር የተፈጥሮ ሀብት የዚያዉ አገር ሀብት እንጂ የጋራ ሀብት አለመሆኑ የዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረተ ሃሳብ ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ሰላምን በዓለም ላይ ማስፈን በመሆኑ በመንግስታት መካከል በድንበር አቋራጭ ወንዞች ለሚነሱ አለመግባባቶች መንግስታት ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱ የሚመክር በመሆኑ ምንም እንኳ Abay is a matter which is essentially within the domestic jurisdiction of Ethiopian State ኢትዮጵያ ለድርድር ቀርባለች።ጠላቶቻችን እየኮሰኮሱ ሰላማችንን ይነሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ ሰላም ወዳድ አገር ናት።ፍቅር ናት ማንንም ጎድታ አታዉቅም ።አሁንም መጉዳት አትፈልግም።የተባበሩት መንግስታት ተባበሩ ስላለ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከታችኞች የአባይ ተፋሰስ ጎረቤት አገሮች ጋር ለጋራ ልማት በመጠቀም አባይን እነሱን በማይጎዳ ሁኔታ እየተጠቀመች ልማቷን ማፋጠን ትችላለች። ከሌሎች ጋር መተባበር የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረተ ሀሳብ ነውና፡፡ ኢትዮጵያ በቅድሚያ በራሷ ህግ እንጂ በዓለም ዓቀፍ ህግ አትተዳደርም። ኢትዮጵያ በፈቃድዋ ተስማምታ ላላጸደቀችዉ ህግ የማክበርም የመፈጸምም ግዴታ የለባትም።ኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፍ ህግ አክባሪ አገር ናት ።ማናቸዉም ተስማምታ የፈረመቻቸዉን ዉሎች እና ስምምነቶች በመፈጸም ግዴታዋን የምትወጣ አገር ናት።

የድንበር አቋራጭ ወንዞች ህግ እንደ ጠፈርና የአካባቢ ጥበቃ ህጎች አዲስ ዓለም ዓቀፍ ህግ ነዉ።በድንበር  አቋራጭ ወንዞች ችግር ያላቸዉ አገሮች ተወያይተዉ ተስማምተዉ የሚያሳልፋቸዉ ህጋዊ ዉሳኔዎች አሉ።እነሱ ተስማምተዉ ያሳለፉት ህግ ከተስማማን መቀበል አሊያም ያለመቀበል ሙሉ መብታችን ነዉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ላይ ያለዉ አቋም ችግሩን ተስማምታችሁ ፍቱ የሚል አጠቃላይ ህግ ነዉ። የወንዞች ፍሰት እንደአገሮች ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ የችግሩ አፈታትም እንደ አገሮች ይለያያል።አንዳንዶች እንደ አባይ ከአንድ አገር ተነስተዉ በቀጥታ ወደ ሌሎች አገሮች የሚፈሱ ሳይሆን በሁለትና በሶስት አገሮች መካከል የሚፈሱ ናቸዉ።የጋራ ወንዝ ስለሆነ በአጠቃቀሙ ላይ አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። መንግስታት ተወያይተዉ ችግሩን ይፈታሉ። አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚፈስ ጅረት እንጂ በኢትዮጵያ እና በእነዚህ አገሮች መካከል የሚፈስ ወንዝ አይደለም። ያ ቢሆን ነበር የጋራ ሀብትነት ፣ፍትሃዊ አጠቃቀም የሚለዉ አባባል  አግባብ ያለዉ አነጋገር ነዉ ብለን እንቀበለዉ የነበረዉ።ያ ቢሆን ነበር በዉኃ አሞላሉ ላይ ጥያቄ ቢያቀርቡ መብታቸዉ ነዉ ብለን እንቀበል የነበረዉ።ዉሃችሁን ከልሰጣችሁን ግድቡን እኛ ሳንፈቅድ ከሞላችሁ ጦርነት እንከፍታለ! አያ ባያ ይላሉ ስዊድኖች ነገር ሳይጥማቸዉ ሲቀር። ያም ሆነ ይህ አባይ የጋራ ሳይሆን የኢትዮጵያ መሆኑን ከተስማማን ኢትዮጵያ በዚህ ድርድር በድፍረት ሃሳብዋን ማቅረብ ያለባት ግብጽና ሱዳንን የሚጎዳዉ ግድቡ ሳይሆን የዉሃዉን ፍሰት የሚቀንሱ ፣

1.የጣና ሐይቅ በእምቦጭ አረም መሞላት

2.የገባር ወንዞች በደለል መሞላት

3.የዛፎች አለመኖርና አለመትከል የዉሃ ትነቱ መጨመር

ኢትዮጵያ እነዚህን ነገሮች መቋቋም ስለተሳናት በዉሃዉ መጠቀም የሚፈልጉ አገሮችና አስታርቃለሁ የሚሉ  መንግስቶችም ሆኑ እንደዓለም ባንክ የመሳሰሉ ድርጅቶች በዚህ እንዲተባበሩ ማስረዳት ነዉ።

ግብጽና ሱዳን በዚህ እንደማይስማሙ ግልፅ ነው፡፡ የአለም ባንክ በማን እንደሚመራና የአለም ባንክ የስራ ቦታዎችም በአረቦች መሞላቱን ስለምናወቅ  በዚህ እንደማይስማሙ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ይሁንናም የአባይ መገደብ ልማቴን ያጓድላል የሚሉ  አገሮች ፍሰቱን እንዳይጎድል ከላይ ያነሳናቸውን መሰረታዊ  ሀሳቦችንና  ሌሎችም የኢትዬጵያ ተደራዳሪዎች ያቀረቧቸውን  የድርድር ሀሳቦች  መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ግን ይህንን ሀሳብ ናቅ  አድርገው ሌላ አማራጭ በመውሰድ አሁን እንደያዙት በተፅኖና በማስፈራራት ከዚያም አልፎ ችግሩን በጦርነት እንፈታዋለን የሚሉ ከሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አስታራቂነት የሚካሄደውን ድርድር ይቆምና ፍልሚያው የጦርነት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጦርነቱ ያስፈራል እኔ ፈሪ ነኝ ፈርቻለሁ፡፡ ያስፈራል ምክንያቱም አገራችን ኢትዮጵያ እንደአሁን የሀይማኖትና የጎሳ ልዩነት ፈጥራ የተከፋፈለችበትና የተናቆረችበት ጊዜ የለም ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ደክሞ ብሄራዊነት የሰፈነበት ጊዜ ነው፡፡ የነበሩንና ያሉን የጋራ እሴቶቻችን እያዳበርን ባሉን ልዩነቶች ላይ ከመወያየት ይልቅ ያሉን እሴቶች እየሸረሸርን ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ባለችበት በቅድሚያ የውስጥ አንድነቷን ሳትፈጥር አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል እንደሚባለው ይህንን የጃርት ትውልድ ይዛ ጦርነት ውስጥ ብትገባ ትሸነፋለች ብዬ እፈራለሁ፡፡ የጉልበት ገሚሱ ምላስ ነው እንደሚባለው የድሮ ዝነዋን እያወራች እንዲሁ ታስፈራራ፣ አንት ፈሳም መጣሁልህ ትበል እንጂ ጦርነቱ ውስጥ መግባት የለባትም እላለሁ፡፡

እኔ የፈሪ ፈሪ ነኝ፤ እኔ ኢህአዲግን እፈራለሁ ኢሕአዲግ ልምድ ያለው ድርጅት ነው የመፈራረም ልምድ የፍርሀት ፍርሀቴ ኢሕአዴግ ጋብቻ ለመፈፀም ወደ መዘጋጃ ቤት ለመፈራረም እንደሚቸኩሉ ፍቅረኛሞች ለመፈራረም የሚቸኩል ድርጅት በመሆኑ አሁንም ተፈራርሞ እንዳይመጣ እየፈራሁ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የቀዳማይ ወያኔ" እውነተኛ ታሪክና ሊላይ ኃይለ ማርያም እያስተጋባው ያለው የአባቱ የአርበኛነት ታሪክ ሲፈተሽ! [ክፍል ፩] - አቻምየለህ ታምሩ

እኔ አልፈራም በርከፈት ነኝ፡፡ በርከፈት ማለት በጉራጊኛ ደፋር/ጎበዝ ጀግና እንደማለት ነው፡፡ በልጅነቴ የአካባቢውን ነዋሪዎችን ከብት እየበላ ያስቸገረን ጅብ በጦር ወግቼ በመግደሌ የሀገሬ ሽማግሌዎች የሰጡኝ ስም ነው፡፡ እናም እና ለሀገሬ ለኢትዮጵያ እናቴ ……ደግሞስ እኛ ጉራጌዎች፣ የደቡብ ህዝቦች በኢትዮጵያ አንድነትና በህዝቧ ላይ ችግር የለንም፡፡ እኔ ሀገሬ አትዮጵያ ትሸነፋለች ብዬ አልፈራም፡፡ነብር ቢያንቀላፋ ዝንጀሮ ጎበኘው ሆነ እና ነው እንጂ የትውልድ ጉልበቱ ህብረቱ’የህዝብ ሀብቱ አንድነቱ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ካበረ ማንንም ማሸነፍ ይችላልና አልፈራም፡፡ ይሁንና ያም ሆነ ይህ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሳያማክርና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋራ በጥልቀት ሳይመክር ኤርትራንና ባድመን አስረክቦ እንደመጣ ዛሬም በድጋሚ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰራ ትልቅ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለማስገንዘብ ነው፡፡ ውስጣዊ ጥያቄ ውጫዊ ጥያቄ አድርጎ ከተፈራረሙ በኋላ መመለሻ የለውምና ነው፡፡ ኤርትራንና ባድመ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የአለም አቀፍ ሕግ ፈረምክ ታሰርክ ነው፡፡ ያውም የእድሜልክ እስራት፡፡ ጠላቶቻችን ይህንን በቅጡ ስለሚረዱ ነው እንድንፈርም የሚገፋፉንና የሚያጣድፉን፡፡

አገር በብድርና እርዳታ ይቀየር ይመስል የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን በእነሱ እርዳታ እንድንቀይር የሚያባብሉንና የሚደልሉን፡፡ይወቁት በራሳችን ጥረት የተፈጥሮ ሀብታችንን ተጠቅመን አገራችንን ማሳደግ እንጂ በእነሱ ባደጉ አገሮች እርዳታ ኢትዮጵያ አትለወጥም፡፡ እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ትቀየራለች፡፡ እርግጠኛ ነኝ አገራችን ኢትዮጵያ ያደጉ አገሮች የደረሱበትን የእድገት ደረጃ ትደርሳለች፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች ጊዜያዊ የእድገት ችግሮች ናቸው፡፡ ሉአላዊ የኢትዮጵያ መንግስት ሲኖር ነው ችግሮቹ እንደፈርጃቸው መፈታት የሚችሉት፡፡ ይህንን ሉአላዊነት ማክበርና ማስከበር የሁሉም ኢትዮጵያኖች ሀላፊነትና ተግባር መሆን አለበት፡፡ ተደራዳሮዎቻችን እስካሁን ያሳዩት የመደራደር ብቃትና ኢትዮጵያዊ ቆራጥነታቸው  የሚደነቅ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የበለጠ መጠናከር አለበት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎናቸው መቆም አለበት፡፡

ኢትዮጵያ  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት  መስራች አገር በመሁኗ ድርጅቱም በመዲናዋ አቋቁማ የአህጉሩን ችግሮች ለመፍታት  በግንባር ቀደም የምትንቀሳቀስ  አገር በመሆኗ ለድርድር አልቀርብም አላለችም እንጅ Nile is a matter which is essentially in the domestic jurisdiction of Ethiopia state እስከሆነ ድረስ ጭራሹን  ከመጀመሪያው  ለድርድር መቅረብ ባልተገባት ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ይሁን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአንድን አገር የውስጥ ጥያቄዎች የጉዳዩ ባለቤት እስካላቀረበው ድረስ በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት አጀንዳቸው ውስጥ አስገብተው መወያየት አይችሉም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ከላይ  በጠቀስናቸው ምክንያቶች ኢትዬጵያ  የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት  ሽምግልና ተቀብላ ውይይቱን እንደቀጠለችበት ትገኛለች ግን ከአፍሪካ ሕብረት ሽምግልነ ባሻገር  የሌሎች አውሮፓ አገሮች ታዛቢነትም ሆነ አስታራቂነት አልተቀበለችም ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡

ግን እዚህ ላይ የድርድሩን አጠቃላይ ሁኔታ  በሚመለከት መነሳት ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡  ኢትዬጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ከታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጋራ በጋራ ለመጠቀም ፈቃደኛ እየሆነችና ለጋራ እድገት ተነሳሽነቷን እያሳየች የተቃራኒ ጎራዎች ድርድሩን በሰላም ከመፍታ ይልቅ በወሰን ግጭት አሳበው ኢትዬጵያን እየወጉ እስከሆነ ድረስና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የተከፈተብንን ጦርነት ማስቆም ካልቻለ የድርድሩ መቀጠል ምን ፋይዳ አለው? ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ጦርነት ለመመከት ዝግጅት ማድረግ እንጂ በድርድሩ መቀጠሉ ምን ይጠቅመቀታል? እንዲየውም ኢትዬጵያ መደራደር በሌለባት የተፈጥሮ ሀብቷ ለድርድር ቀርባ ጦርነት ከከፈቱባት አረብ ሀገሮች ጋር ድርድሩን ማቆም እንጂ መቀጠል ይኖርባታል?

በመሰረቱ ግብፅና ሱዳን የውሀም ይሁን የሌሎች የውስጥ ችግሮቻቸውን መፍታት ያለባቸው እነሱ ራሳቸው እንጂ ኢትዬጵያ ልትሆን አትችልም፡፡ የእነሱን የተፈጥሮ ሀብት መጠየቅም መካፈልም እንደማንችል ሁሉ የእኛንም የተፈጥሮ ሀብት መጠየቅም መካፈልም አይችሉም፡፡ የሱዳን የነዳጅ ሀብት የሱዳን እንደሆነ ሁሉ አባይም የኢትየየጵያ ነው፡፡የቤንዚን ችግር ለኢትዬጵያ እንደሆነ ሁሉ የውሀ ችግርም ለሱዳንና ለግብፅ ነው፡፡ የነዳጅ ችግራችንን  በግዥ አንደምንወጣው ሁሉ የውሀ ችግራቸውም  ከፈለጉ በግዥ ይወጡት፡፡

ኢትዬጵያ የውሀ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የኢነርጂ ክምችትም በአግባቡ ትጠቀም አትጠቀም የመስኖ ውሀዋና የመብራት ስርጭትዋ ለሁሉም ግዛቶችዋ ታድርስ አታድርስ የእኛ የኢትዬጵያ መንግስት ችግር እንጂ የማንም መንግስት ችግሮች እንዳልሆኑ ሁሉ የሱዳንና የግብፅ የኢነርጅም ይሁን ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ችግሮች የኢትዬጵያ ችግሮች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለእኔ ብሎ ለምን በረሀው አያንጨረጭራቸውም! አንድ አስቂኝ እውነት ላጫውታችሁ አባ  ከቅዳሴ መልስ የተለመደው ስብከታቸውን ማሰተማር ይጀምራሉ ሰው ጥግ ይዞ ልብ ብሎ ያዳምጣቸዋል አባ ስብከታቸውን በመቀጠል እየደጋገሙ ሁሉም እንደየስራው ፍርዱን ያገኛል ጥሩ የሰራ ወደ መንግሰተሰማያት መጥፎ የሰራ ወደ ሲኦል  ይወርዳል፡፡

መጥፎ የሰራ ገሀነም እሳት ውስጥ ይቃጠላል! ይቃጠላል! አሉ፤ አንዱ ይነሳና አሁን አሁን እየደጋገመ በማይረባ ጥያቄ አባን ያዋክባቸዋል አዎ ልጄ ለሁሉም እንደስራው ነው፤ ሁሉም የሰራውን ያገኛል ብዬሀለሁ የሉታል፤ አሁንም መልሶ ይጠይቃቸዋል እንደስራው ነው ይሉታል፤ አባ ከአልጋ ላይ ወድቄአለሁና እፀድቃለሁ ወይንስ እኮነናለሁ ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ልጄ እንደዚህ አይነቱን ጥያቄ አይጠየቅም በእንደዚህ አይነቱ መኮነን ካለማ ………አሁንም የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅ ብሎ ይነሳና አባ ዶሮ ቂጧን ወደ ገሀነም እሳት አድርጋ ኩሷን ብትጠል ትቃጠላለች? አባ በጣም ይናደዱና ለእኔ ብሎ ለምን አያንጨረጭሳትም፤ ለምን አይጠብሳትም፤ ብለው መለሱ ይባላል፡፡ አባ መምህር ስለሆኑ ንዴታቸውን ዋጥ አድርገው ዶሮዋን ለምን አያንጨረጭሳትም አሉ እንጂ በዚያ ንዴታቸው ጠያቂውንም ያንጨርጭስህ ሳይሉት አይቀርም ነበር፡፡ አሁን እኔም የምለው ለምን አያንጨረጭሳቸውም ነዋ! እናንተም ማለት ያለባችሁ እንደዚያ ነዋ! መንግስታችንም ማለት ያለበት እንደዚያ ነዋ! የሱዳንና የግብፅ የውሀ ችግር የኢትዮጵያ ችግር አይደለም የከርሰምድር ውሀ ካላቸው የከርሰምድሩን አሊያም ከባህሩ ይሳቡ አሊያም አባ ዶሮዋን ያንጨርጭሳት እንዳሉት በረሀው ቢፈልግ ያንጨርጭሳቸው’ያቃጥላቸው ያንድዳቸው፡፡ ያቃጥላቸው አያቃጥላቸው የሞራል ጥያቄ ነው፡፡ ጥሩ ነው መጥፎ ነው እንደማለት ነው ሞራል በሕብረተሰቡ ውስጥ ይለያያል ሞራል መደባዊ ነው ለአንዱ ጥሩ የሆነው ለሌለው መጥፎ ሊሆን ይችላልና ይሁንናም አሁን የምናወራው ሞራል ሳይሆን ሕግና ፖለቲካ ነው፡፡ የአለምአቀፍ ሕግ፡፡

የእያንዳንዱ አገር የተፈጥሮ ሀብት ምን እንደሚመስልና እያንዳንዱ ምንግስት የተፈጥሮ ሀብቱን በምን መልክ እንደሚጠቀምና የውስጥና የውጭ የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ ችግሮቹን እንደሚፈታ መመሪያ አይሰጥም አይችልምም ልክ እንደዚሁ በመንግስቶች መካከል ለሚነሱ ውዝግቦች ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ይመክራል እንጂ የአንድን አገር ሀብት የመደልደልና የማካፈል ስልጣን የለውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም እንደዚሁ፡፡

አንባቢዎቼ! እስካሁን ስንወያይ የነበረዉ እናንተም እንደምትረዱት አባይ ከዓለም ዓቀፍ ህግ አንጻር ምን መሆን አለበት? የሚለዉ ነበር አሁን ደግሞ ከፖለቲካ አንጻር ምን እንደሚመስል እንይ። ፖለቲካ በሰዎች’በብሄሮች’ በሕዝቦችና በመንግስታት መካከል ያለ ግንኙነት ነው፡፡ ግለሰቦች ከግለሰቦች ይገናኛሉ ይጫወታሉ ብሄረሰቦች ከብሄረሰቦች ተገናኝተው ስለ ባህላቸው አካባቢያቸውና ክልላቸው ውይይትቶችን ያካሄዳሉ፡፡ የፐለቲካ ድርጅቶችም እንደዚሁ የፐለቲካና የኢኮኖሚ የቅርብና የሩቅ አላማዎችና እስራተጂዎች ይነድፋሉ ለፖለቲካ ስልጣን ይታገላሉ፡፡ ከእነዚህ ከላይ ካነሳናቸው ኸይሎች ሁሉ የሚበልጠውና በአገር አቀፍም በዓለም አቀፍም ደረጃ ተሰሚነት ያለው የመንግስት ፖለቲካ ነው፡፡አገሩንና ሕዝቡን ወክሎ ከለሌሎች ምንግስቶችና አለም አቀፍድርጅቶች ግንኙነት ፈጣሪው ሉዓላዊ መንግስት ነወ፡፡ እንግዲህ ትልቁ ፖለቲካ የመንግስት ፖለቲካ ከሆነና የአለም አቀፍ ግንኙነቶች በቅድሚያና በዋናነት በመንግስት የሚካሄድ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ከሌሎች መንግስታት ወይም በአለም አቀፍ ግንኙነቱ አባይን በሚመለከት ምን ያድርግ? የፖለቲካ ጨዋታው ምን ይሁን? ኢትዮጵያ ትቅደም ሳይሆን ትደግ ትምንደግ ከሚሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችስ ምን ይጠበቃል? የሚለውንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ግድ ይላል፡፡

በዚህ በተወሳሰበና በጎበጠ ዓለም ሳይጎብጡ ቀጥ ብሎ መሄድ አይቻልም ።የሊቢያ መሪ የነበረዉን ኮሎኔል ጋዳፊን አንዴ አንድ ጋዜጠኛ እንዴት እንደዚህ አንዴ የዋህ፣አንዴ ብልጥ፣አንዴ አዋቂ፣አንዴ ጅል፣ ሁሉንም መሆን የምትችል መሪ ነህ? እንዴት እንደዚህ መሆን ቻልህ?ብሎ ቢጠይቀዉ የመለሰዉ መልስ እንደዚያም ሆኜ አልቻልኳቸዉም የሚል ነበር። እንዳለውም የኮሎኔል ጋዳፊ ሁኔታ በሚያልቅ ሁኔታ አለቀ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እናም የዓለም ዓቀፍ ህግ በሁለቱ ጎራዎች በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም የኃይል ሚዛን ተወጥኖ የተዋቀረ ነዉ።ዓለም በእነዚህ ሁለት ፖለቲካ ሲስተሞች ተከፍላ ሚዛኑ ወዲያ እና ወዲህ እያጋደለ ኖሮ ዛሬ ዓለም ካለችበት የዕድገት ደረጃ አንጻር ስናይ ካፒታሊዝም ሚዛኑን የደፋ ይመስላል።በሲቭየት ህብረት መሪነትና በሌሎች ሶሻሊስት አገሮች ይመራ የነበረዉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዛሬ በአሜሪካና ሌሎች የከበርቴ አገሮች የሚመራ ሆናል።ይህም በመሆኑ ዓለም ሚዛኑን አጥቶ እነሱ በፈለጉት ሁኔታ እያሽከረከሩት ነዉ።በዚህ ሁኔታ ስለ ዓለም ህግና ፍትህ ከሚወራ ስለዓለም ፖለቲካና ስለ አምባገነኖች ማዉራት ይቀላል።ዓለም በዓለም ዓቀፍ ህግ ሳይሆን በአምባገነኖች ፖለቲካ የምትተዳደር መሆኑን ለመግለጽ የሁለት ሉዓላዊ አገር መሪዎች ሳዳም ሁሴንና ኮሎኔል ጋዳፊን እንዴት በአሰቃቂ እና በአሳፋሪ ሁኔታ እንደገደሏቸዉና አገሮቻቸዉ ኢራቅ እና ሊቢያ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማየቱ በቂ ነዉ።የጸጥታዉ ምክር ቤት ያስተላለፈዉ ዉሳኔ ከምንም ሳይቆጠር የሰዉ አገር ወሮ የተቀመጠ እስራኤልን መጥቀሱ ሌላዉ ማስረጃ ነዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጎጃም ቢወለድም በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው? - የአቻምየለህ ታምሩ ምላሽ

አገራችን ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮች ወደደረሱበት የዕድገት ደረጃ ደርሳ የምትፈራ አገር ሆና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ማስከበር እስከምትችል ድረስ አባይ የግል ሀብታችንም ቢሆን መደራደር አለብን።ከአገር ጥቅምና ከግል ጥቅም የትኛዉ መቅደም እንዳለበት የማናዉቅ እኛ ኢትዮጵያኖች ነን እንጂ የአደጉ አገሮች አገር ከሌለ የፖለቲካ ስልጣንም እንደሌለ ስለሚገነዘቡ በአገር ጥያቄ ላይ ሁልጊዜም ምን ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ። ባራክ ኦባማ ዴሞክራቱ መጣ ሄደ፣ዶናልድ ትራምፕ ሪፓብሊካኑ መጣ ሄደ ከሩሲያ ጋር የሚኖራቸዉ ግንኙነት ከሞላ ጎደል አንድ ዓይነት ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ መጣ ሄደ የአሜሪካ እና የግብጽ ግንኙነት በዚያዉ በነበረበት የሚቀጥል እንጂ ትራምፕ ስለተቀየረ አሜሪካ በግብጽ ላይ ያለዉን ፖለቲካ ይቀይራል ማለት አይደለም።አሜሪካ የግብጽ ወዳጅ የሆነችዉን ያህል የኢትዮጵያ ወዳጅ አይደለችም።አሜሪካ ከተለያዩ መንግስታት ጋር ያላት የማቅረብና የማግለል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጥቅም አንጻር የምታደርጋቸዉ ግንኙነቶች ናቸዉ።አሜሪካ ከግብጽ ጋር ያላት የቀረበ ግንኙነትም በዚሁ የተመሰረተ ነዉ።ኢትዮጵያ ይህን አዉቃ የእዉር ቀበጥ ከመሪዉ ጋር ይጣላል እንደሚባለዉ እንዳይሆን አሜሪካንን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መያዝ ይጠበቅበታል።

የአባይ ጥያቄ ከአፍሪካ ህብረት አልፎ የትም ስለማይሄድ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘዉን ዲፕሎማሲ አጠነክሮ መቀጠል ይኖርበታል።ግድቡን እንሞላዋለን እንለቀዋለን ካስፈራሩን ጭራሹኑ እንዘጋዋለን እያሉ ያዝ ለቀቅ ሳብ ረገብ ማድረግ ነዉ። ጠላት ቢያባብሉት ወዳጅ አይሆንም ይላል የሀገሬ ሰው  አገራችንን በተለያዩ  ዘዴዎች ደካማ ለማድረግ የሚሰሩ የቅረብና የሩቅ ጠላቶች ተነስተውብናል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ውጊያ የጀመሩን የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ብቻ ይመስሉናል እንጅ ከጀርባቸው ሌሎች ኃይሎች አሉ የወጊዎችም የአስወጊዎችም ሕብረት ማፍረስ የሚቻለው በእኛ በኢትዮጵያውያኖች አንድነትና ሕብረት ነው፡፡ ጠላቶቻችንን ማሸነፍ የምንችለው እንዲህ እንደአሁን ተዝረክርከን ሳይሆን ተደራጅተን ነው፡፡ አባይ የሁላችንም ነው መንግስት ዘረኛ ሊሆን ይችላል አባይ ግን ዘርና ጎሳ  የሚለይ ዘረኛ   አይደለም ስለሆነም በአባይ ላይ መተባበር የሁላችንም ተግባር መሆን አለበት፡፡

እንግዲህ ይህንን እንዲህ ካልን ዘንዳ ወደ ተግባር ስንሻገር የድርጅት አስፈላጊነት አጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ድርጅት ስጡንና ጠቅላላ ሩሲያን እንገለባብጠዋለን እንዳለው ትልቁ የሩሲያ መሪ እኛም ጥሩ ድርጅት ከፈጠርን ኢትዮጵያን እንቀይራታለን፡፡ በመደራጀትና በማደረጃት ካመንን የትም ተበታትኖ የቀረበውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊትን በማሰባሰብ መጀመር አለበት እላለሁ፡፡ ጠላቶቻችን ከወሬ፣ ከፕሮፖጋንዳና ከቃላት ጦርነት አልፈው የውጊያ ጦርነት የመሚከፍቱብን ከሆነ የሚሊታሪ ተቋማችንን በሁሉም መልኩ ከአሁኑኑ ማጠናከር መጀመሩ ጊዜ የማይሰጥ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጀግኖች ጀግና የተባለ እንደ እኔ ጀኔራል ተስፋ ሀብተማሪያም የመሳሰሉትን ያፈራች የጀግኖች አገር ናት፡፡ኢትዮጵያ የሚሊታሪ ተቋሟ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተቋሞችዋ መጠናከር አለባቸው፡፡ ሰላም በሌለበት ጠንካራ መንግስትና አገር መፍጠር አይቻልም ሰላም ለመፍጠር መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከማንም ጋራ ተፋልማ ለመውጣት ዋናው ውስጣዊ አንድነቷ ዝግጅቷና ጥንካሬዋ ይሁን እንጅ ውጫዊ ድጋፍም ያስፈልጋታል፡፡ ከጥንትም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራትና አሁንም ያላት፣ የኢትዮጵያ ትልቅ ወዳጅ አገር ትልቋ ሩሲያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል፡፡

የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገሮች በአውሮፓ በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ እነማን ናቸው?

የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ስራቸው ምን ይሆን?

የአባይ ጥያቄ የኛ የዓለም ዓቀፍ ህግ አዋቂዎች ጥያቄ ነዉ፣የኢንጅነሮች ጥያቄ ነዉ፣የኢኮኖሚስቶች ጥያቄ ነዉ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች ጥያቄ ነዉ።የአሁኑ ኮሚቴ እነዚህን ሁሉ ያዋቀረ እንዳልሆነ በቀላሉ መገመት ይቻላል።ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የተራቀቁ ምሁሮች አላት።መንግስት እነዚህን ማሰባሰብ ይጠበቅበታል። እኔ የማውቃቸው ምርጥ ናቸው የምላቸውን ልጠቁም፤ በአለምአቀፍ ህግ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሀይለማሪያም፣ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ፣ ጓድ ባይሳ ዋቆያና የምርጦች ምርጥ አህመድ ዱአሌ አብሲ አለ በኢኮኖሚክስ ዶ/ር ተካልኝ ጎዳና፣ ዶ/ር አስፋው ኩምሳ፣ ዶ/ር ሰሎሞን ደስታ፣ ዶ/ር ትርፉ ማሞ፣ ዶ/ር ታደሰ ዘሪሁን፣ ዶ/ር ሙሉጌታ ይልማ፣ ምርጡ ታደሰ ገ/ኪዳን፣ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ቢረዳንና የኢኮኖሚስቶቹ ቁንጮ ዶ/ር ላቀው አለሙን እጠቅሳለሁ፤ ብርሀነ መዋ፣ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ፣ አንዳርጋቸው አሰግድ፣ ስዩም ሙሉጌታ፣ ኮሎኔል ጌታቸው ዋቅጅራና ፖለቲካ ሉቁ ጓድ አበራ የማነአብ የሌሉበት ፖለቲካ? በእንጅነሪንግ መስክም ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ኢንጀነር ተስፋዮ ዳማና ኢንጅነር ግርማ አላሮን መጠቆም ይቻላላል፡፡

በአባይ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካ ጥያቄዎች ከላይ የጠቀስኳቸው ምሁሮች ጥልቀት ያላቸው ናቸው፡፡ እኔ ያልጠቀስኳቸው ሌሎች እውቅ ምሁራን እንዳሉ ትንሽም አልጠራጠርም፡፡ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የወጡ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ሕይወት ያላቸው ምሁራኖችን የምታሰባስብ መሆን አለባት ዶ/ር አብይ ራሱንም አገራችንም ማዳን የሚችለው ይህን ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ግብፅ ስለአባይ የሚፅፉና የሚመራመሩ የተለያዩ ምሁሮችን ያሰባሰበ ራሱን የቻለ የአባይ ድርጅት አቋቁማ መንቀሳቀስ ከጀመረችበት ብዙ አመቶች ሆኗታል፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግንም በማዳበር ከአፍሪካ ሦስት አገሮች መካከል ከናይጀሪያና አልጀሪያ ጀምሮ ሶስተኛዋ አገር ናት፡፡ የሎቢ ስራዋን አጣጥፋለች፡፡

መደምደሚያ

የተፈጥሮ ሀብታችን የሆነው አባይ ከኢትዮጵያ በበለጠ የጎረቤት ሀገሮችን ሱዳንና ግብጽን ለዘመናት ሲያገለግል ኖሯል፡፡ ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ኢትዮጵያንም ጠቅሞ እነሱንም የጋራ ተጠቃሚዎች አድርጓቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የጋራ ሀብት አይደለም፡፡ አባይ የኢትዮጵያ የግል የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ ይህ መሰመር አለበት፡፡ ይህም በመሆኑ ውሃችንን ገድበን መስኖ መስራት እና የመብራት ኃይል ማመንጨት ሙሉ መብታችን ነው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች በግድቡ አሞላል ላይ አምባጓሮ የሚከፍቱት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ያወጣውን ህግ አትከተልም ሳይሆን ጭራሹኑ አባይ የጋራ ሀብታችን በመሆኑ ሁሉም ነገር በጋራ መወሰን አለብን ስለሚሉ ነው፡፡ አስተሳሰባቸው ውሃ አይዝም፡፡ የሚበጃቸው አባይ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑን ተቀብለው ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምተው ለጋራ እድገት በጋራ መቆም ነው፡፡ የታችኛ ተፋሰስ ሀገሮች በተፃራሪው አሁን የያዙት ፖለቲካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ አድንድነት ድርጅት የአንድን ሀገር የተፈጥሮ ሀብት የማከፋፈል መብት የተሰጣቸው ይመስል ጉዳዩን አንዴ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሌላ ጊዜ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲያቀርቡ ይታያል፡፡

መፍትሔው ግን ሦስቱም ሀገሮች ተስማምተው የጋራ መፍትሔ መሻት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያቀርበውን የመተባበር መንፈስ በቀናነት መመልከት ነው፡፡

በዚህ ድርድር የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የመደራደሪያ ነጥብ አድርገው ማቅረብ አለባቸው ከምላቸው ሐሳቦች አንዱ የአባይ ተጠቃሚ ሀገሮች የአባይን ድርሻ ለማግኘት አባይን በመንከባከብ የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል የሚለው ነው፡፡ ጥቅሙ የጋራ እስከሆነ ሁሉ ጉዳቱም የጋራ መሆን አለበት፡፡ ያም ሆነ ይህ በዚህ በተንሸዋረረ ዓለም ትክክለኛ ፍርድ አገኛለሁ ብሎ ከሌላው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሉት ከአፍሪካ ህብረት መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያሰሩልንን የተንኮል ሰንሰለት በጣጥሰን መውጣት የምንችለው ጠንካራ ሆነን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬ ወሳኝ ነው፡፡ አገራዊ አንድነት እና ጥንካሬ አንፃራዊ በሆነ መዋቅራዊ ለውጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ ምን ዓይነት የማህበራዊ ተቋም ለውጦች? ምን ዓይነት የፖለቲካ ተቋም ለውጦች? ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ተቋም ለውጦች?

በመጨረሻም በዉጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያዉያን በደንብ ተደራጅተን አሁን በየቦታዉ እንደምናደርገዉ የሎቢ ስራዎችን ሳናቋርጥ ማካሄድ ይጠበቅብናል።

 

አመሰግናለሁ!

ኃያለማርያም ደንቡ
Tel. 0920-24331
Email – [email protected]

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.