/

ሕዝብና ምርጫ – አገሬ አዲስ    

1

የካቲት 2 ቀን 2013 ዓም(10-02-2021) ምርጫ የሚፈልጉትን ከማይፈልጉት ነገር ለይተው የሚወስኑበት መግለጫ መንገድ ነው።ከሁሉም በፊት ግን መራጭና ተመራጭ ነገር መኖር አለበት፤ባይኖርም ለመፍጠር ችሎታና ፍላጎት ሊኖር ይገባል። የሚመረጠው ከብዛት ካሉት እንጂ በነጠላው ካለ ወይም ከቆመ አካል አይደለም።እንዲያ ከሆነ  በግዴታ እንጂ  መርጠው የሚቀበሉት አይሆንም።የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳት ለኑሯቸው ወይም ለህይወታቸው አመችና ተስማሚ፣ለደህንነታቸው ዋስትና የሚሰጣቸውን አካባቢና ሁኔታ መምረጣቸው ተፈጥሮ የለገሳቸው መብትና ችሎታ ነው።

በተለይም የሰው ልጅ ለአካላዊ፣መንፈሳዊና ቁሳዊ ግብአት ወይም ይዞታ የሚስማማውን የመምረጡ  ፍላጎት አብሮት የኖረ ልማዱ ነው።መምረጥ የማይችለው ነገር ወይም ከምርጫው ውጭ የሚያገኘው ቢኖር ከማንና ዬት ቦታ መወለዱን ነው። ያም ቢሆን አሁን በዘመናችን የሚሆነውን ስናይ የሰው ልጅ ዬትና መቼ እንደሚወለድ በወላጆቹ ውሳኔና ምርጫ እንደሚሆን እያዬን ነው።በተለይም ኢትዮጵያውያን ወላጆች  የሚወልዱት ልጅ በተሻለ መንገድ እንዲያድግ፣ኑሮው የተሟላ እንዲሆን ከመፈለጋቸው የተነሳ ከአገራቸው ውጭ አመችና ብዙ ዕድሎች ባሉበት አገር በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ መውለድን ይመርጣሉ።

ምርጫ ሁለገብነት ቢኖረውም በዚህ ጽሁፍ የሚቀርበው የአንድን አገርና ሕዝብ እጣፈንታ በሚመለከተው የሥርዓት  የምርጫ ሂደት ዙሪያ ነው።

በዓለም ላይ የሰው ልጅ በጋራና በቡድን በተጓዘበት የታሪክ ዘመናት የደረሰባቸው የኑሮ ደረጃዎችና የአስተሳሰብ ለውጦች ኑሮውን ለመምራትም ሆነ ፍላጎቶቹን ለማርካት የሚረዱትን አማራጮች እንደፈጠረለትና ያንንም ተገንዝቦ  የመምረጥ ችሎታ እንዳዳበረ አይካድም።በዘመናት ጉዞው እድገትና ለውጡም የተለያዬ በመሆኑ የምርጫው አይነትና ውጤት እንደ ወቅቱ የተለዬ ነው።

የምርጫ ታሪካዊ አመጣጥ

ታሪክ ከመዘገባቸው ጥንታዊ የምርጫ አካሄዶች መካከል በጥንታዊ ሕንድ ቬዲክት ዘመን በተባለው ከብረት ዘመን (Iron Age)ማለትም በ600 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት  የተከናወነ ሲሆን ይህም ራጃ የተባለውን ጦረኛ አለቃ ለማድረግ የሚካሄድ ምርጫ ነበር።ይህም ምርጫ ከትውልድ ወደ ትውልድ ፣ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ሹመት ነበር።ምርጫው ሕዝብ የተሳተፈበት ሳይሆን በጉልበተኞች መካከል ነበር። በአሁኑ ባንግላዴሽ በ750-770 ዓም በባላባቶች ምርጫ ንጉስ ጎፓላ የሥልጣኑ ባለቤት ሆኖ ነበር።ምርጫ በድምጽና በእጅ ምልክት በመስጠት የሚገለጽ ሲሆን በአሁኑ ታሚል ናዱ በቾላ ስርዎ መንግሥት በ920 ዓም የነበረው የምርጫ ሂደት በዘንባባ ቅጠል ላይ የተመራጩ ስም ተጽፎ ወይም ምልክት ሰፍሮበት በሸክላ ድስት ወይም ገንቦ ውስጥ ከገባ በዃላ አንድ ወጣት ልጅ ከገንቦው በእጁ እያወጣ በቅደም ተከተል ለሚፈለገው የሥልጣን ቦታ ምደባ ይደረግ ነበር። እጣ ያልወጣላቸው ቅር እንዳይላቸውና ግርግር እንዳይፈጥሩም በቅደም ተከተል የመጀመሪያ ተመራጮቹ እረዳትና ምክትል እንዲሆኑ ዕድል ነበራቸው።ይህ አይነቱ የምርጫ ስርዓት ስያሜ ኩዳቮላይ(Kudavolai system)ይባል ነበር።

በምርጫ የሥልጣኑ ባለቤት መሆን በህንድ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአሁኑ የአውሮፓ ክፍለዓለም  ከጥንታዊት ግሪክና ሮም ንጉሳዊ አገዛዝ  እስከመካከለኛው ዘመን ድረስ የተከናወነ ሲሆን በሮማ ንጉሳዊ ምርጫ ወይም (Imperial election)በቤተመቅደሱና ቤተክህነቱም ዙሪያ( papal election) የሚባሉ ምርጫዎች ይካሄዱ ነበር። ከላይ እንደተመለከተው ባለሥልጣናቱን ለመምረጥ የሚደረገው ምርጫ በላይኛው መደብ አባላት መካከል ቢሆንም የምርጫ ስርዓትን በተመለከተ የመጀመሪያው ምርጫ የተከናወነው በግሪክ ስፓርታ በተባለው ግዛት በ754 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር።በዚሁ ጥንታዊ ግሪክ ከ247 ዓመት በዃላ በ500ከክርስቶስ ልደት በፊት በአቴና የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ ምርጫ ተካሄደ።ከሌላው ጊዜ የተሻለ ቢሆንም የለዬለትና የጸዳ ምርጫ አልነበረም።

በዓለም ላይ የነበሩት ሥርዓቶች ሃይልና ጉልበት ያለው የሥልጣኑ ባለቤት እዬሆነ ያሻውን ሲያደርግና ሲወስን የነበረበት ወቅት ሲሆን መራጩም፣አስመራጩም፣ተመራጩም የዚያው ቡድን አባል ብቻ ነበር።

እድገትና ስልጣኔ  ሲመጣ የህብረተሰቡን አስተያዬትና ፍላጎት እንደቀዬረው ሁሉ ሕዝብ ለሚኖርበት አገርና ለኑሮው የሚያመች ስርዓት የመዘርጋቱ ፍላጎቱ እያደገ መጣ። የምሁራንና የፈላስፋዎችም ቁጥር እዬጨመረ ሲመጣ አዲስ አመለካከትና የሥርዓት ፍልስፍናዎች ብቅ ብቅ አሉ። በነበረው የመቀጠል ዕድሉ እዬቀነሰ መጣ። በሥልጣን ላይ የተቀመጡት የሕዝቡን ፍላጎትና አካሄድ በማጤን የጥገና ለውጥ ለማድረግ ሁኔታው አስገደዳቸው።ይህንን የህብረተሰብ ለውጥ ተከትሎ የመጀመሪያው የምርጫ ደንብና ስርዓት በአውሮፓ ውስጥ የተካሄደው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ነበር።በተከታዮቹ ዘመናት የምርጫ አሠራር የተለያዩ መልኮች ነበሩት።

እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በዚህ የምርጫ ሂደት የሚሳተፈው ሁሉም ዜጋ ሳይሆን የተወሰኑት የማህበረሰብ ክፍሎች አባላት ነበሩ።መደብን የተመለከተ ሲሆን ሃብት ያላቸውና ግብርና ቀረጥ የሚከፍሉት ብቻ የመምረጥና የመመረጥ መብት ነበራቸው። በተከታዩም እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ለመምረጥ ገንዘብ መክፈል ግዴታ ነበር፤ያልከፈለ አይመርጥም ማለት ነው።ይህ አሠራር እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በአርጀንቲና፣በብራዚል፣በካናዳ፣በቺሌ፣በኮስታሪካ፣በኢኳዶር፣በሜክሲኮ፣በፔሩ፣በኡራጉዋይና በቬኑዙዌላ ሲተገበር ቆይቷል።

በሌላም የምርጫ ሂደት የትምህርት ደረጃን የተመለከተ እንደነበርና  ለመምረጥ ፈተና ማለፍ ግዴታ እንደነበር የታሪክ ማስረጃ ያመለክታል።ትምህርትና እውቀት የሌላቸው እንዲሁም ፊደል ያልቆጠሩ ዜጎች የመምረጥ መብት እንዳይኖራቸው ካገዱት አገሮች መካከል ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ቺሌ፣ኤኳዶርና ፔሩ ይገኙበታል።እነዚህ አገሮች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች መዳፍ ስር የቆዩ በመሆናቸው የሚከተሉት መመሪያ ሁሉ የዚያው ነጸብራቅ እንደነበረ በግልጽ ይታያል።

ዘረኛና ጎሰኛ የምርጫ ስርዓት፣ ይህን በተመለከተ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት ሰሜን አሜሪካ፣ሮዴዝያ(ዚምባብዌ)ና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።በነዚህ አገሮች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የጥቁር ሕዝብ ከማንኛውም የምርጫ ተሳትፎ የተከለከለ ነበር።አውስትራሊያና ካናዳም ከዚያ ኢፍትሃዊ አድራጎት አላመለጡም።በቀይ ኢንድያንስና በአቦርጂኒስ ተወላጆች ላይ የነበረው ተጽእኖ ዘመን ተሻጋሪ ነበር፤እስከአሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም።

ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የምርጫ ስርዓት፣ ይህ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች በኩል የሚንጸባረቅ የመብት ግድፈት ሥልጣኑን በተቆጣጠረው የእምነት ተቋም የሚፈጸም በደል ሲሆን አሁንም ድረስ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ጥላውን እንደጣለ አይካድም፤ በአይርላንድ የሚታዬው ክፍፍልና ቀውስ የዚሁ ነጸብራቅ ነው። በተመሳሳይም በሮማንያና በሌሎቹ የባልካን አገሮች ክርስቲያን ያልሆነ ነዋሪ ከመምረጥም ባሻገር የዜግነት መብቱ የተገፈፈ ነበር።ለምሳሌም ይሁዳውያን እስከ 1923 ዓም ድረስ የዜግነት እውቅና የላቸውም ነበር።በአንዳንድ እስላማዊ መንግሥት በሰፈነባቸው አገሮች ለሌላው እምነት ተከታዮች የሚኖረው መብትና እውቅና እንዲሁ የተዛባ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ጥሪ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እንመካከር !

ሌላው የምርጫ መብት ደግሞ ጾታን የለዬ ነበር።ለዘመናት በተካሄዱት የምርጫ ታሪኮች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መምረጥ የሚችሉት ወንዶች ብቻ ነበሩ።የሴቶች የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የታወቀ አልነበረም። በ1840 ዓም በሃዋይ የሴቶች ድምጽ የመስጠት መብት ከመታወቁ በተረፈ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የሴቶች የመምረጥ መብት የታወቀው ከመቶ ዓመት ወዲህ ነው።ከዚያ በፊት ሴት ልጅ ለቤት ውስጥ ሥራና በሚስትነት ለማገልገል እንጂ እንደዜጋ በአገሯም ሆነ በራሷ ህይወት እጣ ፈንታ ላይ የመወሰን መብት አልነበራትም።ይህ አስተሳሰብ አሁንም ዃላ ቀርና ኢዴሞክራሲያዊ በሆኑ ስርዓቶች መዳፍ ሥር በወደቁት አገሮች የሚታይ ኢሰብአዊ አድራጎት ነው።በነዚህ አገሮች ሴቶች በድርብ ጭቆና ማለትም በጾታቸውና በሃይማኖታቸው ይጨቆናሉ ማለት ነው።

ከሁለተኛው ዓለም ጮርነት በዃላ የተባበሩት መንግሥታት ሲቋቋም የሕዝብን ድምጽና የመምረጥ መብት በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ ተገደደ።ስኬታማም እንዲሆን ደንብና ሕግ አወጣ።

ዓለም አቀፍ የምርጫ ስርዓት ድንጋጌ፣

የተባበሩት መንግሥታት እንደተቋቋመ በ1948 ዓም የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን በመሰዬም ዓለም አቀፍ ሕግ አጸደቀ።በዚህ ሕግ በአንቀጽ 21 ላይ የሚከተለውን መመሪያ አሰፈረ።

1 ማንኛውም ዜጋ በአገሩ የመንግሥት ተቋም የመሳተፍ መብት እንዳለው

2 ወኪሎቹን በነጻና በቀጥታ የመምረጥ መብቱ መከበር እንዳለበት

3 የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተግባር የሕዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ የተከተለ መሆን እንደሚገባው፣ይህም የሕዝብ ውሳኔ በዬጊዜው በሚካሄድ ሃቀኛና አስተማማኝ ፣ሁሉንም ያሳተፈ ፣ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ የሚረጋገጥበት መሆን እንዳለበት አስቀምጧል።

በተጨማሪም የምርጫውን ሂደትና ጸባይ፣ፍትሃዊነቱንም በሚመለከት አባሪ ደንብና ሕግጋትን አውጥቷል።

1 ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ምርጫዎች የሚካሄዱበትን ስርዓት መዘርጋትና ማመቻቸት፤ለመራጩ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን ማመቻቸትና ለምርጫ የሚያገለግሉ ቁሶችን ማሟላት።የመራጩን ደህንነት ማስከበር።በሕጉ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውጭ ማንም የማይገለልበትና ወገንተኛ ያልሆነ የምርጫ ሂደትን ማረጋገጥ።

2 በምርጫ ወቅት የመምረጥ መብት በሕግ ሊነፈጋቸው ከሚችሉት ውስጥ ዕድሜው ለምርጫ ያልደረሰ፣የአይምሮ እክል ያለበት፣በወንጀል ተፈርዶበት በእስራት ላይ ያለ  ካልሆነ በስተቀር ሁሉም የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል።

3 ብዙሃኑ የሚሳተፉበትን፣ሃሳብ የሚሰነዝሩበትን ዕድልና አጋጣሚ እንዲሁም መድረክ መፍጠርና ማመቻቸት(ስብሰባ፣ሰላማዊ ሰልፍ፣የመሳሰሉትን)አለመከልከልና አለማገድ።እንዲሁም የምርጫ ውጤት አንጸባራቂ ሊሆኑ የሚችሉ የተጭበረበሩ አሠራሮችን አለመከተል።ቅድመ ምርጫ የድጋፍ ሰልፎችንም አለማዘጋጀት።በተጨማሪም ለተወዳዳሪዎች እኩል የገንዘብና የሚዲያ አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ።

4 በተወሰነ የጊዜ ገደብና መመሪያ መሠረት ምርጫው እንዲካሄድ ማድረግ

5 ምርጫውን የሚመራው አካል ወይም ተቋም ከማንኛውም የመንግሥት ተጽእኖ ነጻና ገለልተኛ መሆን ይኖርበታል።በተለይም የምርጫ ተቋሙ አመራር ከዚህ የጸዳ ሊሆን ይገባዋል።

6 ምርጫው መደበኛ ሕግና ስርዓትን የተከተለ ሆኖ የድምጽ አሰጣጡ ላለመጭበርበሩ ትክክለኛ ቆጠራና ውጤቱ በታዛቢዎች የተረጋገጠ መሆን አለበት።ይህንንም ሕዝቡ በቀጥታ ሂደቱን እንዲከታተለው የሚያስችል መንገድ መዘርጋቱ ጥርጣሬ እንዳይኖር ይረዳል።

7 በመጨረሻም የምርጫ ሕጉን በተግባር መዋሉን የሚከታተልና የሚያረጋግጥ ገለልተኛ አካል መኖር ምርጫውን ተከትሎ ሊነሱ የሚችሉ አለመግባባቶች ለማሶገድ ይረዳል።ለዚህ ተግባር ከፍትሕ ተቋምና በማህበረሰቡ አሜኔታ ካላቸው ነጻ ታዛቢዎች የተውጣጡ  ሊሆኑ ይችላሉ።

የምርጫ አዘጋጅ ወይም ቦርድ አባላትን በተመለከተ

1 ለሥራው ሙያዊ ብቃት ያለው፣በሥልጣን ላይ ካለውም ሆነ ከተወዳዳሪው ፓርቲ ተጽእኖ የጸዳ

2 በሁሉም ዘንድ ነጻና ገለልተኛ መሆኑ የታመነበትና መምራት መቻሉ  የተረጋገጠለት

3 የምርጫ እስፈጻሚው ወይም ቦርዱ ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት ለምርጫው  አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ መሟላቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

የምርጫ ስነምግባር፣

ለምርጫ የሚቀርብም ሆነ ደጋፊ የሚከተሉትን ደንቦች ማክበር ይጠበቅበታል።

1 የምርጫ ቦርዱን መመሪያ አክብሮ መከተል

2 አመጽና ዛቻ፣ማስፈራራትና ማሸማቀቅን ማሶገድ

3 የምርጫ ቅስቀሳ ሕግና ስርዓትን ማክበር

4 በሥልጣን ላይ ያለው አካል ሃይል እንዳይጠቀም መከላከል

5 የምርጫው ቅስቀሳ ገደብ(Election silence) ምርጫው ከሚካሄድበት ዕለት ቢያንስ ከ48 ሰዓት በፊት ቢቆም ሕዝቡ በረጋና በሰከነ መንፈስ ካለማንም ጫጫታና ወከባ አስቦና አሰላስሎ ድምጹን ለሚፈልገው ለመስጠት ይረዳዋል።

6 የምርጫውን ውጤት አክብሮ መቀበል፤ጥርጣሬ ቢኖር በሕጋዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ማመልከት።

ከሁሉም በፊት ምርጫ ሲታሰብ እመረጣለሁ የሚለው እጩ ዓላማውን በግልጽ ማስቀመጥና ለሕዝብ ማስረዳት እንደሚኖርበት፣መራጩም የሚመርጠውንና ለምንስ እንደሚመርጠው በቅጡ መረዳት እንደሚኖርበት፣የምርጫ ድምጹን ለወገንተኝነት እንዳይጠቀምበትና የምርጫ መብቱን እርካሽ እንዳያደርገው፣ከመጸጸትና ከህሊና ወቀሳም ለመዳን መጠንቀቅ እንዳለበትና የሚሰጠው ድምጽ አገርና ሕዝብን በሚመለከተው ትልቅ ጉዳይ ላይ መሆኑን በቅድሚያ ሊገነዘበው ይገባል ይላል።

አንዱ የድምጽ መስጠት የምርጫ  አካል ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ (Referendem) የሚባለው ነው።

በዚህ ሕዝባዊ ውሳኔ ስር የሚጠቃለሉት መንግሥት አዲስ ሕግ ሲያወጣ በመደገፍና በመቃወም ጎራ የለዬ ጭቅጭቅ ሲፈጠር፣የአንድ ከባቢ ሕዝብ ወይም ነዋሪ የሚፈልገው አስተዳደር እንዲመሰረት ሲፈልግ፣ባለሥልጣን  ወይም የወጣ መመሪያ  እንዲነሳለት ሲሻ በሕዝቡ (ድምጸ) ውሳኔ ችግሩ  የሚፈታ ይሆናል።ያም ቢሆን ሕግና ስነስርዓትን የተከተለ መሆን ይገባዋል።በሌላው ወይም በቀረው ብዙሃን ወይም በአገር ላይ አደጋ የሚያስከትል ከሆነ ግን መንግሥት ተገቢ እርምጃ ሊወስድ ይችላል።

ለምሳሌም የአንድ ከባቢ ነዋሪ ሕዝብ በአካባቢው ሕገወጥ ተግባርን የመብት ጥያቄ አድርጎ ቢነሳ፣ወይም  ከሌላው የተለዬ እምነትና ማንነት ያለው ሰው በከባቢዬ መኖር አይገባውም በሚል አቋም ሌላውን ለመጉዳት ቢነሳ መንግሥት እርምጃ ሊወስድና  የሌሎቹን ደህንነት በሕጉ መሰረት ሊያስከብር ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Hiber Radio: የአቶ ግርማ ሰይፉ ንግግር የአንድነት አቋም አይደለም ሲሉ አቶ በላይ ፈቃዱ ተናገሩ * ከለንደን ሶሪያ ሄዶ አሸባሪዎችን የተቀላቀለ አንድ ሀበሻ ተገደለ

 

ኢትዮጵያና ምርጫ

ለብዙ ሽህ ዓመታት ስርዓት ዘርግታ የኖረችው አገራችን የተጓዘችበት መንገድ ከጥንታዊ አገሮች የተለዬ አልነበረም።ባለፈችበት ዘውዳዊ ስርዓት ሕዝቡ መሪዎቹን የመረጠበት ወቅት አልነበረም።ምርጫና ሹም ሽሩ የሚከናወነው በስልጣኑ ዙሪያ በነበሩት መሪዎች ማለትም በቤተመንግሥቱ አካባቢ ነበር።በዘር ከአባት ወደ ልጅ በውርስ የሚተላለፍ  ወይም በመገለባበጥ የሚደረግ የሥልጣን ዝውውር እንጂ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት የወጣ መሪና መንግሥት አልነበረም። ሕዝቡ የመጣውን የመቀበል ግዴታ እንጂ የመምረጥ መብት አልነበረውም።ሕዝባዊ ምርጫና መራጭ ሳይተዋወቁ  እስከ ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ የሥልጣን የመጀመሪያ ጊዜ ድረስ ቆይቷል።

ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ በአልጋወራሽነት ሥልጣናቸው ወደ አውሮፓ ለጉብኝት በመሄድ ሁኔታውን ከተመለከቱ በዃላ በአገራቸው  ለውጥ መካሄድ እንዳለበት ተገንዝበው ቀድሞ ያልነበሩ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ወሰኑ።ከነዚህም ለውጦች መካከል በትምህርትና በአስተዳደሩ ዘርፍ የነበረውን የተመለከተ ነበር።

በቅርበት ታሪኩን የተከታተሉት ጋዜጠኛና ደራሲ ከዚያም በዲፕሎማት ሥራ ለረጅም ዓመት አገራቸውን ያገለገሉት አቶ ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ሃይለሥላሴ መንግሥት”በሚል እርእስ በጻፉት መጽሃፍ ውስጥ ይህንን አስፍረዋል።

ምንም እንኳን የካህናቱና የመሳፍንቱ ተቃውሞ ቢበረታባቸውም ሃሳባቸውን የሚደግፉ በትምህርትና በአስተሳሰባቸው ሕዝባዊነት ያላቸው በዘመኑ ተራማጅ ተብለው የሚታዩት የወሎ ገዥ እራስ እምሩ ሃይለሥላሴ፣ የጽሕፈት ሚኒስቴሩ ጸሃፊ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ፣ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ፣ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያትና የጦር ምኒስትሩ ፊታውራሪ ብሩ ወልደገብርኤል፣ መሳፍንትና መኳንንት በመኖራቸው ያሰቡትን ከማድረግ  አላገዳቸውም።እነዚሁ የተራማጅነት ሃሳብ ያላቸው በኮሚቴ መልክ  አገሪቱ የምትመራበትን ሕገመንግሥት አርቅቀው አቀረቡ።በይዘቱ ያልተስማሙትና ጭራሽም ለውጥ አያስፈልግም ከሚሉት መሳፍንት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ተደረገ።በመጨረሻውም በራስ ካሳ የሚመራውን የተቃዋሚ መሳፍንቱን አቋም በሚያለዝብ መልክ ተሰናድቶ ለንጉሱ አቀረቡ።ለሕገ መንግሥቱ መርቀቅ ዋና መነሻ የነበረው  የሕዝብ ተወካዮችን የመምረጡና የሚሰበሰቡበት ፓርላማን የማቋቋም ውሳኔ ነበር።

የሕዝብ ተወካዮች ሆነው የሚወከሉት በሕዝቡ ምርጫ ሳይሆን  በመሳፍንቱ ፈቃድና የመሬት ባለቤት የሆኑ ባላባቶች ቢሆኑም ከነበረው ስርዓት ጋር ሲታይ ተራማጅና ዘመናዊ ነው ማለት ይቻላል።ንጉሰ ነገሥቱ ከመሳፍንቱ ጋር የነበራቸውን ውጣ ውረድ በተራማጆቹ ክንፍ እርዳታ ከተወጡ በዃላ የረቀቀውን ሕገ መንግሥት ዘውድ በጫኑ በዘጠነኛው ወር በሃምሌ 23 1923 ዓም በፊርማቸው አጽድቀው ይፋ አደረጉ።ከአራት ወር በዃላም ዘውድ በጫኑ በአንድ ዓመት በጥቅምት 23 ቀን 1924 ዓም የመጀመሪያውን የሕዝብ ምክር ቤት ከፈቱ።ይህም እርምጃ አገሪቱ ስትተዳደር የነበረበትን ለዘመናት የቆዬ ፍትሓ ነገሥት(የነገሥታት ሕግ)የተባለውን ከጥቅም ውጭ አደረገው። ከምክር ቤቱ ጎን ለጎንም የመሳፍንቱን ፍላጎት ለማርካት ሲባል የዘውድ ምክርቤትን(ሕግ መወሰኛን)መሰረቱ።ይህ እንደ እንግሊዞቹ የህዝብ ምክር ቤት (House of common)የመሳፍንቱ(house of lords)የሚባሉትን ተከትሎ የመጣ ይመስላል።

በተራማጆቹ እረቆ በወጣው ሕገመንግሥት  ውስጥ ከአንቀጽ 1-28 ድረስ ከተዘረዘሩት የሕዝብ መብቶች ውስጥ  የሚከተሉት አንቀጾች ይገኙበታል።

1 ማናቸውም የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነ በንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ የጦር አለቃ ለመሆንና በጠቅላላውም በመንግሥት ሥራዎች ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ሊቀበል ይችላል።

2 ማናቸውም የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነ ከአንዱ ስፍራ ወደሌላው ስፍራ በነጻነት እዬተዘዋወረ ለመኖር ይችላል።

3 ማናቸውም የኢትዮጵያ ተወላጅ በሕግ መሰረት ይያዛል፣ይፈረድበታል፣ይታሰራል እንጂ ያለሕግ ለመያዝም፣ሊፈረድበትም፣ሊታሰርም አይችልም።

4 ማናቸውም የኢትዮጵያ ተወላጅ ከሕግ ውጭ ቤቱና ዕቃዎቹ አይበረበሩበትም።

5 ማናቸውም የኢትዮጵያ ተወላጅ ከሕግ ውጭ ከማንም ሰው ጋር የሚጻጻፈው ወረቀትና ደብዳቤ አይመረመርበትም።

6 ማንኛውም የኢትዮጵያ ተወላጅ በሕግ እንደተጻፈው ለሕዝብ ጥቅም ያስፈልጋል ከሚልበት ጊዜ በቀር በእጁ ያለውን ንብረቱን ማንም ሊወሰድበት አይችልም።

ይህንንና ሌሎቹንም የሕግ አንቀጾች ለማስከበር፣የንጉሠነገሥቱንም ፍላጎት ተቀብሎ የሚያጸድቅ ፓርላማ ተቋቁሞ እስከ 1966 ዓም ድረስ በሥራው ላይ ቆዬ።በተደረጉት ተከታታይ ምርጫዎች ምርጫውን የሚቆጣጠረው የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ሲሆን ሶስት ሰዎች ያሉበት የምርጫ ቦርድም ነበረው።ይህም ማለት ምርጫው በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንደነበር ያሳያል። የምርጫ ሂደቱ ባይለወጥም የተመራጮቹ የመደብ አመጣጥ ግን እዬተለወጠ መጥቶ ነበር።ከባላባቱና ከመሬት ባለሃብቶች በተጨማሪ ቁጥራቸው ቢያንስም የተማሩና ከሕዝቡ ውስጥ የወጡ ተወካዮች በፓርላማው ውስጥ ለመግባት ችለው ነበር።ግን ሕጉን ለማሻሻል፣የሕዝቡን ኑሮና የፖለቲካ ጉዞ፣የሥርዓቱን መሻሻል በሚመለከተው ዙሪያ የሠሩት ሥራ አልነበረም።አብዛኛው የሚያገኘውን ደመወዝ ብቻ እንደትልቅ ግብ ይቆጥረው ነበር።በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ግን የማይገባው ቃል አልነበረም።ከሰማይ ዳቦ አዘንባለሁ ከማለት የደረሰ ባዶ ተስፋ ይነገር ነበር።

ይህ የለውጥ ጅማሮ በቀጣይነትና በትክክለኛው መንገድ ቢተረጎም ኖሮ አገራችን አሁን ካለችበት ምስቅልቅል ሁኔታ ላይ አትገኝም ነበር። ይህ ሕግ ከወጣበት ከመቶ ዓመት በዃላ አሁን የሚሆነውን ሁሉ ስናዬው የዃሊት እንደሄድን ልንገነዘብ እንችላለን።ከመቶ ዓመት በፊት በሕግ የተደነገገው አሁን ላይ እዬተጣሰ ፣ሕግ አልባ የመሆኑ ነገር በስፋት ሲታይ ተፈሪ ማረኝ! ያሰኛል።

ምንም እንኳን የንጉሠነገሥቱ እርምጃ ከሌሎቹ ነገሥታት የተለዬና ዘመናዊ ቢሆንም ለመሠረታዊ ለውጥ አላበቃም።ለትውልዱ የሚመጥን የተለያዩ ሥርዓት አመለካከቶችን የሚያንጸባርቁ የሕዝቡን መብት የሚያስከብሩ ጥያቄውንም የሚመልሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ለመደራጀትና ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ሕግና ነጻነት አልነበረም።የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እያሽቆለቆለ ሲመጣ፣ድህነት ፣እርሃብና ስደት፣የኑሮ ውድነት ሲከሰት ተቃውሞ ከዳር እስከዳር በመነሳቱ ለንጉሠነገሥቱ መንግሥት ውድቀት ምክንያት ሆነ።

ከዘውዳዊ ስርዓት በዃላ የመጣው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን ቡድንም የባሰ ሆነና አገሪቱ ከድጡ ወደማጡ ተሻገረች።አነሰ ሲሉት ተቀነሰ እንዲሉ በንጉሱ ጊዜ የነበረውም ፓርላማ ታገደ።ጁንታዎች አድራጊ ፈጣሪ ሆኑ። በብሄር እኩልነት ስም የተገንጣይ ቡድኖች እንደአሸን ፈሉ፤በትጥቅ ትግል አገሪቱና ሕዝቡ ታመሱ።የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥትም ሲንገዳገድ ቆይቶ ከ17 ዓመት የሥልጣን ዘመን በዃላ ተበታተነ።መሪ የነበረው መንግሥቱ ሃይለማሪያምም በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ ውስጥ ያልነበረ አሳፋሪ ክህደትና ቅሌት ፈጸመ፤ከባዕዳን ጋር ተመሳጥሮ ወታደሩን በጦር ሜዳ በትኖ ጥሎ ፈረጠጠ።አገሪቱም በተገንጣይና አስገንጣይ የጎሳ ድርጅቶች መዳፍ ላይ ወደቀች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለቪኦኤ ቃለምልልስ ሰጡ | ስለአንዳርጋቸው ጽጌ፣ ስለኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ፣ ስለሚያደርጉት ጥንቃቄ ተናገሩ

በቦታው የተተካው  የኢሕአዴግ ስርዓት የኢትዮጵያን ታሪክና አገራዊ አንድነት ብሎም ልዑላዊነት እውቅና የሰጠና ለማስከበርም የተነሳ ባለመሆኑ መነሻና መድረሻውን የጎሳ ፖለቲካ አድርጎ ሕዝቡን ለመለያዬት ሌት ተቀን ሠርቶ፣ በሕግ ደንግጎ አሁን ለደረሰው አገራዊ ውድቀት ዳረገን። እንኳንስ ለሕዝባዊ ምርጫ ቀርቶ ሕዝብ ብሶቱን ለመግለጽ የሚችልበት መንገድ ተነፈገው። ለስሙ ፓርላማና ሕግ አለ ቢባልም ሕጉ ለራሱ አገዛዝ የሚያመች ሆኖ በራሱ የተቀረጸ፣በፓርላማውም  የሚሰገሰጉት በጎሳ አውጫጭኝና ኮታ በመሆኑ  ወሳኙና አድራጊ ፈጣሪው የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ከሌሎቹ የበለጠ ሃይል ያለው ህወሃት የተባለው ሕገወጡ የትግራይ ነጻ አውጭ ቡድን ሆነ።ለስሙ የምርጫ ቦርድ ቢኖርም የህወሃት ዱላ በመሆን ከማገልገል በዘለለ እውነተኛ ምርጫ የሚያስከብር ተቋም አልነበረም። በመጨረሻውም ይህ ቡድን በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው በደል ከቀን ወደ ቀን እዬጨመረ በመምጣቱ  በሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት በራሱም ውስጥ ሽኩቻ ተነስቶ  የመወገድ ዕድል ገጠመው።በቦታው የተተካው ግን የራሱ ተባባሪና አካል የነበረው ኦነግ የተባለው የኦሮሞ ድርጅት ውልድ የሆነው ኦህዴድ የተባለው በመሆኑ ሲሆን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሥልጣኑን ይዞ ስም እዬቀያዬረ የህወሃት/ኢሕአዴግን ብልጽግና የሚል የዳቦ ስም አውጥቶ ሌሎቹን ጎሰኛ ድርጅቶች አሰልፎ በተመሳሳይ መንገድ እዬተጓዘ ይገኛል።

አሁንም የጎሰኛ ስርዓት የኢሕአዴግ ቅጥያ በሆነው ብልጽግና ዘመን የሰው ልጅ ዜጋ በማንነቱ፣ በቋንቋው፣ በጎሳው፣በእምነቱ እዬተፈረጀ መከራ የሚያይበት እንጂ መብቱ የተከበረበት አይደለም።ይባስ ብሎም የሰው ልጅ ከሚበላበት ወቅት ላይ ተደርሷል።, ኢትዮጵያን ለመበታተን ከህወሃት በከፋና በታቀደ መልክ  በመሰራት ላይ ነው።የጎሳ መተካካት እንደ ጥበብና ችሎታ ብሎም መብት ተቆጥሮ ባለተረኝነት ነግሶ ሕገወጥ ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቶ ይገኛል።የገንዘብና የመሬት ዘረፋው ተስፋፍቷል፣ጎሳ ተኮሩ ጭፍጨፋና ማፈናቀሉ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም።በጎሳ መተካካት መርሆ የሰፈነው ስርዓት ከራሱ ጎሳ ውጭ ያሉትን በተለይም አገራዊ አመለካከት ያላቸውን በማጥቃቱ ሥራ ተሰማርቶ እራሱን ለማጠናከር ብዙ ሙከራዎችን አድርጓል፣በማድረግም ላይ ነው።በምርጫ ቦርድ በ,ባለው ፈረሱ በኩል ለአገር አንድነትና ለእኩልነት የቆሙትን  ድርጅቶች ከምርጫው ውድድር በስበብ ባስባቡ እያገደ ለጫፋሪዎቹ ብቻ እውቅና ሰጥቷል። የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ትውልዱን ተስፋ ቢስ ከማድረጉም በላይ ለወንጀል ሥራዎች ዳርጎታል።የሴት ልጅ ክብር ተገፏል፣ሕጻናት እዬተሰረቁ ኩላሊታቸው እዬወጣ በየጉሮኖው ተገለው ይጣላሉ።  ሕዝቡንና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማጭበርበር ብዙ ቢታክትም ሃቁን ሊሸፍነው አልቻለም።እራሱን ሕጋዊ ለማድረግና ዕድሜውን ለማርዘም  ምርጫ ለማካሄድ ሽርጉድ በማለት ላይ ነው።ምርጫው ፍትሃዊና የስርዓት ለውጥ የሚያመጣ ላለመሆኑ ብዙ ማረጋገጫዎች ይታያሉ።የምርጫው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ከምርጫው በፊት መናገር ይቻላል።ለዚያም ማመላከቻው

1 ምርጫው በጎሰኛ ድርጅቶች መዳፍ ስር መውደቁ፣ከዜግነት በላይ የጎሳ መብትን ቅድሚያ በመስጠቱ፣

2 የምርጫ ቦርድ ተብዬው የቀድሞው ተቀጥያ ሲሆን ለተረኞቹ ባደሩ፤ቅጥረኞች መመራቱ፣የመንግሥት ዱላ ሆኖ የማገልገሉ ባሕል አለመለወጡ፣

2 ተወዳዳሪዎቹ በነጻ በፈለጉበት ቦታ  የመንቀሳስና የመሰብሰብ መብት በመነፈጋቸው፣

3  ለምርጫ የሚያበቃ ሰላምና መረጋጋት አለመኖሩ

ከነዚህ ባሻገር በጎሳና በዘር እንዲሁም  በሃይማኖት ትርምስ ውስጥ በተዘፈቀ አገር የሚካሄድ ምርጫ ውጤቱ የበለጠ ቀውስ እንደሚሆን አያጠራጥርም።ይህንን አደጋ ለመከላከል በቅድሚያ በጎሳና በሃይማኖት ተዋረድ የመደራጀትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግን  በሕግ ማገድ ይገባል። በአገራዊ ማለትም በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የመቆምም እንደ ግዴታ ሊቀመጥ ይገባል።የአገርን አንድነት የሚዳፈረው፣ልዩነትና ግጭት የፈጠረው ሕገ መንግሥት  መለወጥ ይኖርበታል። ምርጫው የቡድን ማንነትንና መብትን ለማስከበር ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ መብት በሚያስከብረው በፖለቲካ አስተሳሰብና ፍልስፍና አኳያ ፣የአገርን አንድነትና ልዑላዊነት፣የሕዝብን ሰላምና አብሮነት በሚያረጋግጥ መርሆ ስር ለተሻለ ስርዓት የሚያበቃ  ፉክክር እንዲሆን ማድረጉ ከምርጫው በፊት ሊተገበር ይገባል።ይህ ባልተሟላበት ወደ ምርጫ መግባቱ ምን ተይዞ ጉዞ ከመሆኑም በላይ ለከባድ አደጋና አገራዊ ቀውስ ፈቃደኛ መሆን ነው።ምርጫው ቢካሄድም ውጤቱ  አሁን የሚታዬውን የአንድ ጎሳ የበላይነትን  ሕጋዊ ከማድረግ ሌላ የሚሰጠው ጥቅም የለም።ገና ከጅምሩ ተቃዋሚን ማሳደድ፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና መግደል እለታዊ ትዕይንት ሆኗል።ሁኔታው ከቀጠለ ያሰጋል።በምርጫውም ሰሞን ይሁን ከዚያ በፊትና በዃላ ሊከሰቱ የሚችሉት አደጋዎች ለባሰ የጎሰኞች የድንበርና የመሬት ውዝግብ በር ከመክፈቱም ባሻገር የአገሪቱን መኖር አጠራጣሪ ያደርገዋል።

አሁን ያለውን ውስጣዊ ትርምስ በማዬት የውጭ ሃይሎችም በኢትዮጵያ ላይ ከመረባረባቸውም በላይ ሱዳኖች ድንበር ጥሰው መሬቷን ይዘዋል።ሌሎቹም የየድርሻቸውን ለመቀራመት አሰፍስፈው ይገኛሉ።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች የጎሰኞች አጃቢ ሆነው  ለምርጫ መራኮታቸውን ትተው በቅድሚያ የአገሪቱን ህልውና ለማስከበር በአንድ ላይ መቆም ይኖርባቸዋል።አገር ሳይኖር ሥልጣን አይታሰብም።ይደርሰናል ብለው ከሚጠብቁት የሥልጣን ትርፍራፊ ይልቅ ከታሪክ ወቀሳ የሚድኑበትን መንገድ ሊከተሉ ይገባል።

ከሁሉም በፊት  አገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይገባል።በአሁኑ ሁኔታ ለምርጫ ከመሮጥ ይልቅ የሕገ መንግሥት ለውጥና ከጎሳ እይታ የተላቀቀ ብሔራዊ የሽግግር ወይም የቀውጢ ቀን መንግሥት መፍጠር ለዘላቂው ውጤትና የጋራ ድል ዋስትና ነው።

አገሬ አዲስ

 

1 Comment

 1. የምናነግስ በምርጫ
  ለነገሩን ሊጥሉልን ቅርጫ

  የምግብ ዋጋ ንሮ
  መርሮታል የሀገሬ ሰው ኑሮ

  ዘይት በቁራጭ የማሽላ እንጀራ
  ሆንዋል ምግቡ እድለኛ ታዳጊ አማራ

  ለአብዛኛው የባህላዊ ወጥማ ድሮ ቀረ
  ከርሞ ውሀ በጠብታ-ዘይት እንደሞያ ከተከበረ

  ለአፍንጫ መአዛ ብቻ ሆነዋል ሽሮ እና በርበሬ
  ሽንኩርት እና ቲማቲምም አይቀመሱም ልክ እንደ ሥጋ የበሬ

  አዲስ አበቤ ዘይድዋል ለማስታገስ የዘንድሮውን ረሀብ
  የመኪና ጭስ አየር ወደ ሆድ ምጎ በመሳብ

  የውሀ በጠብታ-ዘይት ወጥ የለመደ ሆድ
  በባዶ ተነፍቶ ጾሙንም ማደር ይለምድ

  አረብ ሀገር ሄደች እና ምግብ የማትበላዋ የጉለሌዋ የቤት እመቤት
  የመኪና ጭስ በኦክሲጅን ሆኖ ተገኘ እንዲህ ያፋፋት

  የአረብን ንፁህ አየር ምጋ ስትስብ
  ለቀቀባት ግሉኮስ ያልቻለው ረሀብ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.