/

የራያ ህዝብና  ብሄረሰባዊ  ማንነቱ

4

ተጻፈ በአማረ ምስጋን ትኩዬ(የህግ ባለሞያ)

ኩታበር

መግቢያ

ራያ  ከዘመነ  ኢ.ህኢ.ዴ.ግ  በፊት  በደርግም  ሆነ  በንጉሱ  ዘመነ    መንግስት  እንዲሁም  በጎንደርያን  አገዛዝም  ይሁን    በዘመነ-መሳፍንት  ወቅት   በሰሜን   ምስራቅ  ኢትዮጵያ  በወሎ  ክፍለ  ሀገር  ውስጥ  በአውራጃነት  የሚገኝ  እጅግ   በጣም  ለምና  በከርሰምድር  ውሃ  የበለጸገ   በአመዛኙ  በተንጣለለ   ሜዳ  ላይ  የሚገኝ   አካባቢ  ነው፡፡

ይህ  ቦታ  እንደማንኛውም  የኢትየጵያ  ስመጥር  አውራጃዎች   የራሱ  የሆነ  የታወቀ  ወሰን  ያለውና  አይነግቡ  የሆነ  የህዝቦች  ሁለንተናዊ  ክዋኔ  የሚካሄድበት  ስፍራ ነው፡፡  አንዳንዶች የራያ  የአስተዳደር ወሰን  በስተሰሜን  በኩል   ማይጨውን  ያካልላል   ቢሉም  አብዛሀኛው  ሰው  ግን  በደቡብ  ከአላ-ወንዝ  በሰሜን  ደግሞ እስከ  ኤቦ  ወንዝ  ይረግጣል  ይላሉ፡፡  ይህም  ማለት ራያ  በስተደቡብ   ከየጁ   በስተሰሜን  ደግሞ  ከወጀራት  ጋር   ይዋሰናል  ማለት  ነው፡፡   በውስጡም  ራያ ቆቦ፣ ራያ  አላማጣ፣ራያ ኦፍላ (ኮረም) ፣  ራያ  አዘቦ (መሆኒ)፣  ራያ  ጨረጨርና  ሌሎች  ስመጥር  ቦታዎች   ይገኛሉ፡፡

ይህ አውራጃና  በውስጡ  የሚኖሩ  ህዝቦች  ከጥንት  እስከ  ዘመነ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ  ድረስ  በከፊልም  ሆነ   በሙሉ  በትግራይ  ገዥዎች   ወይም  በትግራይ ክልል  አስተዳደር  ስር  ተዳድረው  አያውቁም፡፡  ይህን  ማረጋገጥ የምንችለው ቀደም  ሲል በጎንደሪያን  ዘመነ  መንግስት   ንጉስ አንጋሽና  አውራጅ  የነበረው  የትግራዩ ሚካኤል  ስሁልና  የኢትዮጵያ  ንጉሰ  ነገስት  የሆኑት  አጼ ዩሀንስ 4ኛ ይገለገሉበት   የነበረውና  የትግራይን  ወሰን ያረጋገጡበት  የነበረው  “መጽሀፈ  አክሱም” የትግራይ  አስተዳደር  ደቡባዊ  ወሰን  ተምቤን  እና   አምባላጌ እንደሆነ  በካርታ  ጭምር  ስለሚገለጽና   በአንድም  ታሪካዊ  ካርታ ላይ  ራያ   የትግራይ   ግዛት  አካል  ሆኖ  የማይገኝ  ስለሆነ  ነው፡፡  ( አቻምየለህ  ታምሩ፡- የወልቃይት ጉዳይ ገጽ 350 እና 352 ፡ 2012ዓ.ም  የታተመ)

ይልቁንም ራያ  ከ16ኛውና  17ኛው  ከፍለ ዘመን  የኦሮሞ ህዝብ  እንቅስቃሴ   እንዲሁም   ከሌሎች  ታሪካዊ  ትስስሮች ጋር  ከወሎ  ክፍለ ሀገር   የተገናኘና  የተሳሰረ   በክፍለ  ሀገሩ  ውስጥ  ዋነኛና  ተጽእኖ  ፈጣሪ  አውራጃና ወረዳ  የነበረ ነው፡፡

የወሎ  ክፍለ  ሀገር  በራያ  በኩል  ከትግራይ  ጋር  ይዋሰናል  እንጅ  በአንዱም  የታሪካችን   ክፍል  ትግራይ   በወጀራት  በኩል እንጅ በራያ  በኩል  ከወሎ ( ቤተ አምሀራ)  ጋር  ተዋስኖ  አያውቅም፡፡

በውስጡ  የሚኖሩ  ህዝቦችም  የርስበርስ  ግንኙነታቸው  የጠነከረና   የመደብ  ጭቆናን  በመቃወም  እንደ  ጎጃምና የባሌ  ገበሬዎች  ሁሉ  የራያ  ገበሬዎች   አመጽን  በቀዳማይ  ወያኔ በኩል  አስነስተው  ለፍትህና ለነጻነት   የሚታገሉ  አገር ወዳድና  ንቁ  ህዝቦች  ናቸው፡፡ በዚህም  ትግላቸው   መደባዊ  ጭቆናን  ታገሉ   እንጅ   የማንነት   ተጋድሎ   አላደረጉም፡፡ ይህንንም   የትግሉ መሪ   የነበሩት   የብላታ  ሀ/ማሪያም  ረዳ   ልጅ የሆነው    አቶ  ሊላይ ኃ/  ማሪያም  በቅርቡ  በፋና  ቴሌቭዥን   ቀርቦ   አስረድቶናል፡፡

ታዲያ  ራያን  በአንድ  የአስተዳደር ስር  አድርጎ  በአንድነት  ማስተዳደር  የስልጠናቸው  አደጋ  መሆኑን  የተረዱ  ቀዳማዊ  ሀይለስላሴ በአንድ ወቅት  ራያን  ለሁለት በመክፈል   ግማሹን  (ራያ አዘቦ)    ወደ  ትግራይ  ክፍለ  ሀገር  እንዲጠቃለል  አድርገውት  ነበር፡፡ ነገር  ግን  ይህ  የአስተዳደር   መደላደል  ከጅመሩ  ፖለቲካዊ  ስለነበርና   ለአማቾቻቸው   እጅ  መንሻ የሰጡት  ስለነበር  በህዝቡ  ተደጋጋሚ  አቤቱታና  ትግል ወደ  ትግራይ   የተካለለው  የራያ ክፍል ( ሰሜን  ራያ)  ወደ  ወሎ   ክፍለ  ሀገር  (  ደሴ)  እንዲመለስ  ተደርጓል፡፡ (ታሪክ አዋቂዎች የበለጠ ታስተካክሉልኛላችሁ)  በዚህ  ሁነት   የአገሬ  ሰው ተደስቶ፡-

መናገር ደግነው   መንገር  ለስላሴ (  ቀ.ሀ.ስ)

ራያና  ቆቦ   ገበረ  አሉ  ደሴ ፡፡ (አላማጣ በዘመኑ የራያና ቆቦ ማዕከል ነበረች) በማለት  ተቀኝቶ  ነበር፡፡

ከደርግ  ዘመን  መንግስት በኃላ ይህንን  መጥፎ  የታሪክ  ልምድ  ከራሱ  የግዛት  ማስፋፋትና የገዘፈች  ትግራይን  ከመገንጠል  አላማው ጋር በማቀናጀት ህወሀት / ኢህአዲግ ምንም  እንኳን  በ1968ዓ.ም ማንፊስቶው መሰረት  ሙሉውን  መውሰድ  ባይችልም  ዳግሞ  ራያን  ለሁለት ከፍሎ  ራያ አላማጣን  ፣ራያ ኦፍላን፣ ራያ አዘቦን እና  ሌሎች  የራያ  ቦታዎችን   በትግራይ  ክልል  አስተዳደር  ስር  በማድረግ   ይሄው ከ1983 እስከ 2013ዓ.ም   ድረስ  እያስተዳደረ  ይገኛል (ነበር)፡፡

ህወሀት ዳግሞ  ለ2ኛ  ጊዜ  ራያን  ለሁለት  ሲከፍል  በመጀመሪያ  ደረጃ   በ1968ቱ  የትግል ማንፌስቶ ጠላት  አድርጎ  የሳለውን  የአማራን ብሄረሰብ ለማዳከም  ነው፡፡  በመቀጠል  አማራውን   በማዳክም ሌሎች  ብሄረሰቦች  አማራን  በጠላትነት  ከተነሱበትና  እርስ  በርሳቸው  በመናከሳቸው ኢትዮጵያ ሀየባይ( ተቆታጣጣሪ)  በምታጣበት  ጊዜ  በግዛት  መጠኗ  የሰፋችና  ለም  የሆኑ  የራያ  የአፈርና  የጎንደር  መሬቶችን  የያዘች    ትግራይን (Republic  of  Tigray)   ለመገንጠል   ነበር፡፡

ይህንንም  የመገንጠል  ስራውን  በሚሰራበት ጊዜ  በእነዚህ  ቦታዎች ላይ  የሚኖሩ  ህዝቦች  የአንገነጠልምና  የኢትዮጵያዊነት  ስሜት እንዳያነሱበት  ላለፉት  ሶስት  አስርት  አመታት  በክልሉ ውስጥ  ለአማራም  ሆነ   ለሌሎች  ብሄረሰቦች  እውቅና  ባለመስጠትና  የራሳቸውን  ቋንቋ  ባህልና   ስነልቦና  እንዲጥሉና እንዳያስታውሱ  በማድረግ  አሀዳዊ  በሆነች  ትግራይ  በትግረኛና  በህወሀት  አመራሮች  ፍዳቸውን  ሲያበላቸው  ኖሯል፡፡  በአካባቢዎቹ  የሚኖሩ  ወጣቶችና  ጎበዛዝት  ቀያቸውን  ጥለው  እንዲሰደዱ  አደርጓል፡፡  በእነሱም ፋንታ የራሱን ሰዎች ከአድዋና  ከአዲግራት እያመጣ  ክልላዊ  የሰፈራ  ስራ  ሲሰራ ኖረ፡፡  የአካባቢውንም  ነዋሪዎች  በስርአተ  ት/ት  ውስጥ  በተቃኘ  ፕሮግራምና  በአስተዳደራዊ  ሰንሰለት   ትግረኛ ቋንቋን  በግድ  እንዲለማመዱ  ፣የአፍ  መፍቻ  ቋንቋቸውን  በትግረኛ  እንዲተኩና  በልምምድ ሂደት  የአማርኛና  የትግረኛ ቅይጥ የሆነ  ቋንቋ  እንዲናገሩና  በእውኑም ተጋሩ ነን  እንዴ? የሚል የማንነት  ብዥታ  እንዲፈጠርባቸው  አደረገ፡፡

ይህንንም የማንነት  ረገጣ ( internal colony በሉት) ተከትሎ  በጎንደር  በኩል   በወልቃይትና  ሁመራ  የሚኖሩ  አማሮች ስረ መሰረታቸውን  አጥንተው  የአማራነት  ማንነታችን  ይመለስ በማለት  የማንነት  ጥያቄ  ሲያነሱ  በራያ  በኩል  ያሉት ግን  ይህንን  የውስጣዊ  አግላይ  ጭቆና  የወለደውን  የቋንቋ  ባህሪና  የማንነት   ብዥታ  ተቀብለው  እኛ  ራያ  ነን  የራያነት  ማንነታችን  ይመለስ  በማለት  የማንነት  ጥያቄ  አንስተው  በሂደት ላይ  ይገኛሉ፡፡

የወልቃይቴዎች ጥያቄ ትክክለኛና  ይመለስልኝ  የሚባለው  የተቀማ  ማንነት   በመሆኑ  በአማራ  ህዝብም  ሆነ  በቀሪው  የኢትዮጵያ  ህዝብ  ተቃውሞ አልገጠመውም፡፡  ነገር  ግን  በራያ   በኩል የተነሳው  የራያነት  የማንነት  ጥያቄ ራያንና ህዝቡን  ዳግም  ለሁለት   በመክፈል  በወያኔ  አገዛዝ  የታለመውን  አማራንና  ኢትዮጵያን  የማዳከም እሳቤ  የሚያስቀጥል  ሆኖ  በመገኘቱ፤  እንዲሁም  ይህ  የማንነት  ጥያቄ  በዚህ  የራያ  ክፍል  ውስጥ  የሚገኙ  ወገኖቹን  ለዳግም  ጭቆና የሚዳርግ በመሆኑ በአማራ  ህዝብ ተቃውሞ ሲገጥመው በሌሎች  ኢትዮጵያዊያን ዘንድም እምብዛም  ተቀባይነትን አላገኘም፡፡    ጥያቄውም   እንግዳ  ሁኖ  ስለተገኘ  ብዙዎች   በጉዳዩ  ላይ  ግልጽ  አይደሉም ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹አሁን ወንድማችን ጀዋር በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፤ መንግስት የሚያደርግለት ጥበቃም ይቀጥላል›› - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

እኔም  ይህ  የራያነት  የማንነት  ጥያቄ  ከጅምሩ ህጸጽ ያለበት (ever defective) ሆኖ  ስላገኘሁትና  እመልሰዋለሁ  ብሎ  የተነሳው ማንነት  ጭቆናን፣  አግላይነትን  ፣ነጣጣይነትን እንዲሁም  አናሳነትን ይዞ  የሚመጣ  በመሆኑ ይህ  ችግሩ ተወግዶ ሁለንተናዊ  አንድነትና  ነጻነትን በሚያመጣ  መልኩ  ትግሉ  እንዲካሄድ  ይህንን  ጽሁፍ ላጋራችሁ ችያለሁ፡፡

 1. ራያና የስያሜው  ምንነት

ራያ ምንም  እንኳን  በራያ  ማንነት  አስመላሽ  ኮሚቴዎችና  በራ.ዴ.ፓ( ራያ ራዩማ  ዲሞክራሲዊ  ፓርቲ)  አመራሮች የማንነት  ወይም  የብሄረሰብ  ስም  ነው በመባል   ጥቅም  ላይ  እየዋለ  ቢገኝም  ትክክለኛ  አገባቡ ግን  የቦታ   /የአውራጃ/ወረዳ/ ስም ነው፡፡

የቃሉን  ትርጉም  የተመለከትን  እንደሆነ ቃሉ  የኦሮምኛ ቃል  ሲሆን  የአማርኛ  አቻ  ትርጉሙ “ሰራዊት”  ማለት ነው፡፡ ይህን  ስያሜውን  ደግሞ  በ16ኛውና  በ17ኛው ክ/ዘመን  ወደ ሰሜን   ምስራቅ  ኢትዮጵያ (ወሎ)  ተንቀሳቅሶ  የነበረው የኦሮሞ  ህዝብ  እንደማንኛውም  የወሎ  አካባቢዎች እንደወጣለት /እንደቀየረለት  ይታመናል፡፡ ይህ  የኦሮሞ  ህዝብም  የራያን  ሜዳ  ራያ  ሲል   የሰየመው    ልክ  ለየጁና  ለአምባሰል  በሰጠው   የስያሜ  አግባብ  እንጅ    በተለየ ብሄረሰባዊነት  አግባብ  አይደለም።

ምናልባት    ጥንት  በነበረው  የኦሮሞ ህዝብ   እንቅስቃሴ  ራያ  የሚባለው  ንዑስ  ጎሳ በወሎ ጎሳ ውስጥ  የሚገኝ ጎሳ ነው የሚባል ከሆነ   የራያ  ጎሳነት  የሚሰራው  የኦሮሞን  ጥንተ-ታሪክ  በምናጠናበት  ጊዜ   ለኦሮሞ  ህዝብ እንጅ  ከጥንት  እስከ  ዛሬ  በቦታው   ላይ  ለሚኖሩ  ለአማራ  ፣አገውና  ለሌሎች   ህዝቦች  አያገለግልም፡፡

ስለሆነም የላስታና  የራያ  ሰው  “ራያ”  የሚለው  ስም  ለዚያ  በታላቁ  የምስራቅ   አፍሪካ  ስምጥ ሸለቆ  ውስጥ  ለሚገኘውና ለተናፋቂው   ስፍራ  መጠሪያ  መሆኑን  አውቆ ላስቴው፡-

 • የተጫነችውን አትበላም  አህያ፣

የነስበር  አገር  እንዴት ነው  ራያ፡፡  በማለት ናፍቆቱን  ሲገልጽ የራያው ሰው   ደግሞ  ያገሩን  ቆንጆ

 • እንደራያ ሜዳ  ወለል  ያለው  ገላሽ፣

ሃብታም  በገንዘቡ  ድሃ  ባይኑ በላሽ፡፡

 • እንደ ራያ ሜዳ  ለጥ ያለው  ወገቧ

መቼ  ያስታውቃል ራቧ ጥጋቧ፡፡

በማለት  ቁንጅዋንና ለግላጋነቷን  ይገልጽበታል፡፡

በነዚህና  በሌሎች  ስነ-ቃልም  ሆነ  አፈ-ታሪካዊ  ሀልወቱ ራያ  የራያ  አውራጃ/ወረዳዎች/ ስም  እንጅ  በውስጡ  ለሚገኙ  ለአማራ  ፣ለአገው፣ለአፋር፣ ለኦሮሞና፣ ለትግሬ  እንዲሁም   ለነዚህ  ውህድ  ህዝቦች  ብሄረሰባዊ  ማንነት ስም  ሆኖ  አይነገርም ፡፡ አይደለም ፡፡

ይሁን  እንኳን  ከተባለ   እነዚህን  ህዝቦች  ራያ  ላይ  የሚገልጻቸው  ኢትዮጵያዊነት  እንጅ  ራያነት  አይደለም፡፡

 1. ራያና አቅኝዎቹ  ( ምንጭ  ሙሄ  ሂድያ እና ሞላ  ከበደ ጎሽ ራያ ቆቦ 03  ቀበሌ )

እዚህ  ላይ  አንባቢዎች  እንድትረዱልኝ  የምፈልገው ነገር  ራያ እንደ ማንኛውም  የኢትዮጵያ  ክፍል  ጥንት  በደን የተሸፈነ ጫካ  የነበረና  አሁን  ላይ   ለምቶና ቀንቶ  የሰዎች  መኖሪያ  የሆነ  ስፍራ  መሆኑን  ነው፡፡  ይህንን  መሰረት  አድርገው ጥንት ኦሮሞዎች ቦታውን ለከብት ግጦሽና ለአደን ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በ17ኛው ክ/ዘመን  አጋማሽ  ግን  ከዚህ  በታች  አቅኝዎች በማለት  የምጠቅሳቸው  7  አባቶች  (ባላባቶች) ከላስታና ከደጋው የራያ  ክፍል ተነስተው ራያን  ለእርሻና  ለመኖርያነት  አቅንተው ይሄው  ዛሬ  ለኛ  ለልጆቻቸው  መኖሪያ  አድርገውታል፡፡

በዚህም  መሰረት  የራያ  የሽምግልና  ስርአትና  ባህላዊ  አስተዳደር   ከወንዝ  ወንዝ  (ከቦታ  ቦታ)  እነዚህ  አቅኝዎች  ባስቀመጡት  ስርአት  ስለሚተዳደር  ራያና  ማህበረሰቡ  በሰባት (7)  አባት  ይተዳደራል ይባላል፡፡   እንደ አባቶቻችን   አፈ ታሪክ   እነዚህ  የአካባቢ  አቅኝዎች  ራያን  በወንዝ  ፣በተራራና  በመንገድ  በመከፋፈል አቅንተውታል፡፡

በመሆኑም ከየጁ፡ ከደቡብ  ወደ ሰሜን በሆነ  አቅጣጫ ስንጓዝ፤

1ኛ) ስንየ  ቢገድ  የሚባለው  አባት  በዋናነት ቃሊም  በመባል  የሚታወቀውንና  ከዶሮ  ግብር  እስከ  አላውሃ የሚገኘውን  ስፍራ    ያቀና ሲሆን፤

2ኛ  ከፍሎ  ደግሞ ጉራ  ወርቄ  የሚባለውንና  ከከረም /ዳና/  እስከ  ጎሊና (አራዱም)   የሚገኘውን  አገር  አቅንቷል፡፡

3ኛ  ከነዚህ  በመቀጠል  የምናገኘው  ክንፎ የሚባለውን  አባት  ሲሆን   ተራራማውን  ምእራብ  የራያ  ክፍል  ከሳንቃ  እስከ  ተኩልሽ (መቅደላ)  ያቀና ነው፡፡

4ኛ. ዘወልድ የሚባለው  አባት  ያቀናው  የራያ ክፍል ደግሞ ከሁሉም የአካባቢ አቅኝዎች ግዛት የሰፋና የተንሰራፋ/የተለቀ/ ሲሆን አባታችን ዘወልድ የቄስ የኋላ ምንይልክ እና የራስ በትሮን ልጅ የሆነችው የመስቀሌ በትሮን ልጅ ሲሆን በትውልዱም ጎንደሬ ነው። በኋላም በአጼ ፋሲለደስ ዘመነ-መንግስት የላስታ ቡግና ገዥ ሆኖ ተሹሟል ፡፡ይህንንም ቦታ ማዕከል በማድረግ ከላስታዎች ጋር በመጋባት ተኩለሽን/መቅደላን/ ጨምሮ ራያን /ቆቦ/ ከሆርማት እስከ ጎቡ ወንዝ ድረስ አቅንቷል ፡፡

እንደሌሎች አካባቢዎች  ሁሉ  በዚሁ ቦታ  እኔን  ጨምሮ  የእርሱ የልጅ ልጆች  የሆኑ  ህዝቦች   እንድንኖር  አድርጓል፡፡

5ኛ. መዛርድ  የሚባለው  አባት  ከዋጃ  እስከ በላይ  ተድላ  ሲያቀና፤6ኛ ገረመድን( ገረብ)  ደግሞ  ከመዛርድ ጋር  ተዳክቶ አላማጣን  ማእከል  ባደረገ ከአሮሮሻ ወንዝ እስከ  በርጨጭ ወንዝ ( በርተህላይ)  ያለውን ስፍራ አቅንቷል፡፡

7ኛ.  በመጨረሻም  ተድላ የሚባለው አባታችን  ከአፋር ጋር  በመዳከት  ምስራቃዊ የራያ  ክፍልን  (ራያ አዘቦን) ያቀና  ሲሆን  ከበላይተድላ  እስከ ኩኩፍቶ  የሚያጠቃልል  ነው፡፡

ይህ  አፈታሪክ  በቀጣይ  የሚጠና  መሆኑ  እንደተጠበቀ  ሆኖ   እነዚህ  አቅኝዎች  ያቀኑት  ቦታ  ከሞላጎደል  አሁናዊ  የራያን የግዛት  ወሰን    የሚሸፍን  ነው፡፡   እንግዲህ  እነዚህ  አባቶች  አሁን  ላይ  በብሄረሰባዊ  ማንነቱ  አማራ  ነው  ከምንለው  ከክርስቲያን /high land kingdom/ የወጡና  የተሾሙ  ሆነው  ሳለና እንዲሁም  አሁን  ከእነርሱ  የሚወለደው  የራያ  ህዝብ  በቦታው  ሰፍቶና  በዝቶ  እየኖረ  ሳለ ለዚህ  ህዝብ  ከአማራነት ውጭ  ሌላ  አዲስ  ብሄረሰባዊ   ማንነት  ልንሰጠው አይገባም  ማለት ነው፡፡  ራያም  በዚህ  የታሪክ  ውልደቱ  የአካባቢ  ስም  እንጅ  የማንነት  ስም  አይሆንም፡፡

 1. ራያና  የህዝቡ  አሰፋፈር

ከላይ  ለመግለጽ  እንደሞከርኩት  ቀደምት  አባቶቻችን  ራያን  በአካባቢ ገዥነትና  አቅኝነት  አለሙት እንጅ   በጎሳ  መሪነት  ወሰናቸውን    አልገደቡትም ፡፡  ከዚህም  የተነሳ  ልጃቸው  የሆነው  የራያ  ህዝብ  የቁጥር ልዩነት  ቢኖረውም  አብረውት ከሚኖሩት  ከአፋር  ፣ ከአገው፣ከትግሬና  ከኦሮሞ ህዝቦች  ጋር  ከአንዱ ወሰን  ወደ ሌላው ግዛት በድንበር  ሳይወሰን  ለመኖሪያ  በተስማማውና ቤት ንብረት በመሰረተበት ቦታ የመኖሪያ ቀየውን   አድርጎ  በነጻነትና  የኔ ባይነት ስሜት ከጥንት እስከ  ዛሬ እየኖረ  ይገኛል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ዛሬም እንደ ትላንቱ አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል!" አብን

ነገር ግን  ይህንን  ወንድማማችነትና  የእርስ  በርስ  መስተጋብር   ወደጎን  በመተው  ህወሀት /ኢህአዴግ ልቡ  እንደፈቀደና የግዛት   ማስፋፋት   ፍላጎቱ እንደመራው  ከ1983ዓ.ም  ጀምሮ  ላለፉት 30  አመታት   ምንም  አይነት  ህገ-መንግስታዊም ሆነ ፖለቲካዊ የልዩነት  መስፈርት  ሳያገኝ  አንድ  የሆነውን  የራያን   ህዝብ   በወስፌ  እንደሚከፍል የሴት ጸጉር  ለሁለት  ከፍሎ  የማንነት  ጭቆና  ሲያደርስበት  ኖሯል፡፡  ይህንንም  በደል  የፈጸመበት  ጥንተ  ጠላቴ  አማራ  ነው በማለት  ሲሆን ራያነት    ጠላቱ ሆኖ  አያውቅም፡፡

ይህንንም  የምንረዳው  ትህነግ

“አረሱት  የሁመራን  መሬት  ያውም  የኛን እጣ  ፣

እነሱ  ምን  ያርጉ  ከኛ ሰው  ሲታጣ ” (ከሚለው  ሞጋቹ  የፋሲል  ደመወዝ  ዘፈን   እኩል )

 “አላማጣ ውየ  ዞብል  አቀናለሁ( ሰሜን ወሎ)  ፣

አታርጊኝ  ጣል  ጣል  አያል ሰው  አውቃለሁ”

በሚለው  በራዮች  ነባር  ባህላዊ  ስነ-ቃል   ሲበረግግና  ሲፈራ  ስናገኘው  ነው፡፡

እንደዚህ  የሚሆንበት  ምክንያትም   በህገ-መንግስቱና  በሌሎች ህጎች  ለብሄረሰቦች  እኩልነት   የቆመ  በመምሰል    ቢደነግግም  በተግባር  ግን  የሌሎች ብሄረሰቦችን  /አማራ/ መኖሪያ መሬትን  በሀይል  ቀምቶ  መያዙን   ስለሚያውቅና   እነዚህን  ስንኞች ተከትለው  አማራዎች ማንነታችንንና ግዛታችንን  በማለት ጥያቄ  እንዳያነሱበት ስለሚፈራ  ነው፡፡

 1. የራያ ህዝብና የራያ  ማንነት  አስመላሾች    መሰረት   ያደረጓቸው  ህገመንግስታዊ  የማንነት  መስፈርቶች  ያላቸው  ግንኑነት

በስራ  ላይ  ያለው  የኢፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግስት  በአንቀጽ 39 (5) ላይ  አንድ  የተወሰነ  ማህበረሰብ  የብሄር /የብሄረሰብነት/  እውቅና  እንዲያገኝና  መንግስታዊ  ውክልና  እንዲኖረው   ማህበረሰቡ  ተመሳሳይ  ባህል /ልምድ/ ያለው  ፣ የጋራ  መግባቢያ  ቋንቋ  ያለው፣ የጋራ  የተዛመደ  ህልውና  አለኝ  ብሎ  የሚያምን ፣ የስነልቦና  አንድነት  ያለውና  በአብዛሀኛው  በተያያዘ/  ኩታገጠም  በሆነ    መልከአምድር  የሚኖር  መሆን  እንዳለበት  ይደነግጋል፡፡

ራ.ዴ.ፓ እና  የራያ ማንነት አስመላሽ  ኮሚቴም  እነዚህን  ህገመንግስታዊ    መስፈርቶች መሰረት  በማድረግ  በሰሜን  ራያ(ከዋጃ እስከ ወጀራት) የራያነት ብሄረሰባዊ ማንነት ጥያቄ በማንሳት ከመንግስት ምላሽ ለማግኘት   በመጠባበቅ  ላይ  ይገኛሉ ፡፡

እኔም  ሰሜን   ራያ  ከህገ-መንግስቱ  በፊት  የተወሰደ  መሆኑን  ጠብቄ የሰሜን  ራያ  ህዝብ  እነዚህን ህገ-መንግስታዊ የማንነት   ቅድመ  ሁኔታዎች  መሰረት  አድርጎ  ራሱን  የቻለ  የተለየ  ህዝብ  ነው  ወይስ  ከወሎ  ህዝብና  ከአማራ  ህዝብ  ጋር  አንድ  ህዝብ  ነው የሚለውን  ነጥብ  ካለው  ነባራዊ  ሁኔታና  ካደኩበት  ማህበረሰብ  አንጻር  እቃኛለሁ፡፡

እንግዲህ  ህገ-መንግስቱ  አንድን  ህዝብ  ከማህበረሰብነት    ከፍ  አድርጎ  የተለየና    ራሱን የቻለ ብሄረሰብ አድርጎ እውቅና ለመስጠት ይህ ብሄረሰብ  የራሱ  የሆነ የጋራ  መግባቢያ  ቋንቋ  ያለው ፣ ተመሳሳይ  ባህል  ያለው  ፣የስነ-ልቦና  አንድነት  ያለው  የጋራ  ህልውና  አለኝ  ብሎ የሚምን  እና   ኩታገጠም  በሆነ ስፍራ  የሚኖር  መሆን  እንዳለበት  በአስገዳጅነት   ይደነግጋል፡፡

ታዲያ  የራያ-ራዩማን (ከቆቦ እስከ ወጀራት)  ጠቅላላ    የሰሜን    ራያን ህዝብ    ደግሞ  በተለየ  ሁኔታ   ከነዚህ ነጥቦች  ጋር  አገናዝበን  ያየነው  እንደሆነ  የማንነት  ጥያቄ  የተነሳባቸው  የራያ  ዋጃ፣ ራያ አላማጣ፣ራያባላ፣ ራያ ጨርጨር፣ ራያ  ኮረም፣ ራያ  ጥሙጋ  እንዲሁም   ሌሎች  የራያ  ቦታዎች  የአማረኛ  ቋንቋ  ተናጋሪዎች  እንጅ  የራይኛ ( የራያ  ትግረኛ) ቋንቋ  ተናጋሪዎች  አይደሉም፡፡  አማረኛንም  ልክ  እንደራያ  ቆቦ  ሰው  እና    እንደላስታዎች  አድርገው   አያወሩትም/አይናገሩትም/  የሚባል  ከሆነ  ደግሞ  ለአመታት በህወሀት የተደረገባቸው ጭቆና እንደተጠበቀ ሆኖ ከትግራይ ህዝብ  ጋር  ባላቸው  ሁለንተናዊ  መስተጋብር   ኮ/ል  ደመቀ  ዘውዱ  በሚናገረው  ዘየ  መናገራቸው እንጅ  የተለየ ቋንቋ  መፍጠራቸው  አይደለም ፡፡  በነዚህ  በጠቀስኳቸው ቦታዎች  ከአማረኛ ውጭ  ይህንን (ራይኛ)  የማይሰሙና  የማያውቁ  ብዙ    እናት ፣ አባት  ወንድምና  እህቶቻችን  አሉ፡፡   እንደሚባለው  በእነዚህ  ቦታዎች  ላይ  ራያነት  ከራይኛ  ጋር  ብሄረሰባዊ  እውቅና  ይሰጠው ቢባል  እነዚህ  ነባር  የአገሬው  ነዋሪዎች  ድጋሜ  በማያውቁት  ቋንቋ እንዲማሩ ፣እንዲዳኙና  እንዲተዳደሩ  በመፍቀድ  በውስጣዊ  ጭቆና  እንዲማቅቁ  ከማድረግ  ውጭ  ሌላ  ፋይዳ  የለውም፡፡  በዚህ  አድራጎታችንም  አንድ  ነው  የምንለውን  ራያ  ራዩማን  እንደ  አስካሁኑ  ለሁለት  ከፍለን ዳግም  ለስነልቦና ረሃብ  መዳረጋችን  ነው፡፡መሆኒ  አካባቢ  ይነገራል  የሚባለው  የራይኛ  ቋንቋም (የራያ ትግርኛ ቁርጥ  አማርኛ) አማርኛን ከመናገርና  ከመስማት  የማያግድ  መሆኑ  እንደተጠበቀ ሆኖ  በስፋት  ይነገርባቸዋል በሚባሉ  ቦታዎች  ላይ  የአስተዳደር  እውቅና  ከመስጠት ውጭ ራያን  ለሁለት  መክፈል   ለራያነት  መፍትሄ  አይሆንም፡፡

ከዚህ በመቀጠል  የራያን  ህዝብ  ስነ-ልቦናዊ  አንድነትና   የህልውና መሰረት  የተመለከትን  እንደሆነ  ራያዎች  ልክ  እንደየጁዎች ፣ አምባሰሎችና  ጎንደሮች   አገራቸውን  እንደቤታቸው  የሚያዩ(  ሌሎች  ይጣላሉ አላልኩም)  የአገራቸውን  ክፉና  መልካም   ታሪክ  እንደታሪክ  ተቀብለው  የራሳቸውን  ታሪክ  ለመጻፍ የሚንደረደሩ  ጀግናን  በጀግንነቱ  እንጅ  በዘር  ከረጢቱ  የማይመዝኑ፡ ጀግናን  የራሳቸው   አድርገውና   ራሳቸው  እንደርሱ   እንዲሆንላቸው  የሚተጉ  ባጠቃላይ  ለአገራቸው ኢትዮጵያና  ለብሄረሰቦቿ  ጤነኛ  አመለካከት  ያላቸው፡  እንደ  ዘመነኞቹ  የብልጽግና አመራሮች(ከአማራ ብልጽግና ውጭ)  ስልጣን  አገኘን  ብለው  ሌሎችን በማንነታቸው  ምክንያት    እውቅና  የሚነፍጉና  የሚጨቁኑ  አይደሉም፡፡

ይህም  የሚሳየው  ራያዎች  ከአማሮች  ጋር  በስነልቦና  የተሳሰሩ   የነሱ  ህልውና  የሚረጋገጠው  የጎንደሬዎች  ህልውና  ሲጠበቅ   በመሆኑ  ከሸዋዎችና  ከወሎየዎች  ሲለዩ   ለአጥቂዎቻቸው ተጋላጭ  እንደሚሆኑ ነው ፡፡ በዚህም  ወንድምነታቸውና  የስነልቦና  አንድነታቸው “ራያን  ሲያስለው  ጎንደርን  ያስነጥሰዋል ” “ራያ  ሲነካ   ጎንደርን  ያስለቅሰዋል ” ፡፡ ሁለቱም   ህዝቦች  አንዱ  ለሌላው  ደጁን  ሆነው  ክፉና  ደጉን  በጋራ   እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡

ራያ ከነዚህ ህዝቦች  ጋር  ብቻ  ሳይሆን  በሚኖርበት  የአካባቢ  ሁኔታ  በሰጠው  እድል  መሰረት   በዙሪው  ከሚገኙት  ከአፋር  ጋር  ተካይሳ  /ጓደኛ/  ነው፡፡   ከአገው  ጋር  ወንድም  ነው፡፡ ከኦሮሞም  ጋር  ዘመድና   አብሮ ኗሪ  ነው፡፡  ከትግሬም  ጋር  የተዋለደና  በክፉ  ቀን  ደራሽ ነው፡፡  በመሆኑም ራያን  ከዚህ   ሁለንተናዊ ትስስር  ነጥሎ  ለብቻው  በብሄረሰብነት  በማዋቀር በልዩ ዞን አጥሮ  ማስቀመጥ አሳውን  ከባህር  እንደማውጣትና  ትልቁን  ዛፍ ዙሪያ-ገባ  ስሩን  ቆራርጦ  እንደማድረቅ  ይቆጠራል፡፡  በዚህ ምክንያትም    የማንነት  ጥያቄው  የህዝቡን  ነባራዊ  ሁኔታ   ያላገናዘበና  ዘመን  አመጣሽ  ጥያቄ  ይሆናል፡፡

የራያን  ህዝብ   በተለይም የማንነት  ጥያቄ  የተነሳበትን    ህዝብ  ጅኦግራፊዊ  አቀማመጥ  የተመለከትን  እንደሆነ  ከራያ ቆቦ፣ ከየጁና  ከላስታ  እንዲሁም  ከአገዎች  ጋር  እንደ  ሰው  ልጅ  አካል  ክፍሎች   ተጎራርሶና ተሰካክቶ የሚገኝ  እንጅ  የተለየ  የቦታ  አቀማመጥ  የለውም፡፡

ባህላዊ  ክዋኔውንና  ሱታፌዎቹን  ከተመለከትን  ደግሞ  ካለው  የቦታ  አቀማመጥና  የአየር  ንብረት  ሁኔታ  አንጻር ድግና  ጎንቢሶ ይለብሳል እንጅ  በአቅራቢው ካሉት  ከየጁዎችና  ከላስታዎች  እንዲሁም  ከወሎየዎችና  ከጎጃሜዎች  ጋር (ጥቃቅን  አካባቢዊ  ክዋኔዎች  እንደተጠበቁ ሆነው) ተመሳሳይ  የሰርግ ፣የሽምግልና፣ የሀዘን፣የደስታ፣ የአስተራረስ  ፣የአመጋገብ፣የአዋዋብና ሌሎች አይነተ-ብዙ  ባህሎች አሉት ፡፡  አንድ  የራያ  ልጅም  ለየጁዎችም  ሆነ  ለላስታዎች   የሰርግ  ሚዜ  ቢሆን  ምንም  አይነት የሚገጥመው እንግዳ  ባህል  (culture shock) የለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Mauris id orci non erat porta

ስለሆነም  ራ.ዴ.ፓና  የራያ  ማንነት  አስመላሽ  ኮሚቴዎች  መሰረት  ያደረጉበት  የሀገራችን  ህገመንግስታዊ   የማንነት  ብያኔ  የዘር፣ የቋንቋ  ፣የባህልና  የስነልቦና  አንድነትን  የሚጠይቅ  ስለሆነና  ራያ  ደግሞ    ለብቻው  ይህንን  መስፈርት   የማያሟላ  መሆኑ  እንደተጠበቀ  ሆኖ  ባለው  አካባቢያዊ  የአየር ንብረትና  የቦታ  አቀማመጥ   እንዲሁም  ከሌሎች  ብረሰቦች  ጋር    ባለው የቆየ  ትስስርና  የአሰፋፈር    ወሰንተኝነት  ለየት ያለ   የአለባበስ  የአጨፋፈር  የአዋዋብና የአነጋገር  ዘየ መያዙ    ራሱን    የቻለ  ብሄረሰብ  አያስብለውም፡፡ ከትልቁ   የአማራ  ብሄረሰባዊ  ማንነት ውጭም የተለየ ማንነት  አያሰጠውም ፡፡ በዚህ  የአኗኗር ገጽታው  ደግሞ ራያነት ልክ  እንደላስቴነትና  የጁነት  አካባያዊ  ማንነት ነው ፡፡ የአለማጣ  መሆኒ  ባላና  ኮረም  ሰዎች  ከቆቦ  ሰዎች  ጋር  ተመሳሳይ  የሆነ  የአለባበስ  የአኗኗርና የአጨፋፈር ባህል  አላቸው፡፡

 1. ራያና  ስነ-ቃላዊ  ህልውናው

ታሪክ የጊዜና  የሁኔታ  መደላደልን  ሲያገኝ   በጽሁፍ የሚተላለፍ  መሆኑ  እንደተጠበቀ ሁኖ  ይህን  እድል  ሳያገኝ  ሲቀርና  ነገሮች  ያልተመዘገቡ ሆነው በሚገኝበት  ጊዜ  የህዝቡን   አኗኗር ፣ አጠቃላይ  ሁኔታና  የአስተዳደር  ስርአት በስነቃል እና  በአፈታሪክ ከትውልድ ወደትውልድ ያስተላልፋል ፡፡ እኔም በዚህ የስነ-ቃል ታሪካዊ ፋይዳና  የነገሮችን  ጥንተ ማንነት  የመግለጽ   አቅሙ  የተነሳ ስነ-ቃልን  የራያነት  ብሄረሰባዊ ማንነት  የተነሳባቸው  የሰሜን   ራያ  ማለትም የራያ  ዋጃ ፣ ራያ   አላማጣ፣  ራያ  ባላ ፣ ራያ አዘቦ /መሆኒ/ ፣ ራያ  ኮረም  ፣ራያ  ጨረጨርና  የመሳሰሉት  ቦታዎችና  ህዝቦች  ብሄረሰባዊ  ማንነታቸው ራያዊ ነው ወይስ  አማራነት   ለሚለው   መደምደሚያ  ተጠቅሜበታለሁ፡፡  እነዚህ   ስነቃሎችም  እንደ ንዋይ  ደበበና ጅማ  ከማዶ ሆነው  ስለራያና  ስለራያዎች  የተቀነቀኑ  ሳይሆን   ራያዎችና  ወሎየዎች  በአካባቢያቸው  እየኖሩ  ከእግር  እስከራሳቸው  እየዳሰሱ  የዘፈኗቸውና  ያዜሟቸው  ናቸው፡፡

እነዚህ  የራያ  አካባቢዎች  በትውልድ ፣ በቋንቋ ፣ በባህልና  በስነልቦናዊ  አንድነት  ከራያ ቆቦና  ከወሎ  ህዝብ  ጋር  የተቆራኙ ናቸው፡፡  ከራያነት (አሁን  ከሚሉት)   ጋር  ደግሞ  ምንም  አይነት  ታሪክ  የላቸውም፡፡  የእነዚህም  አካባቢዎች  ስነ-ቃላዊ  ሀለዎት  ከአማራዎችና  ወሎየዎች  እንዲሁም  ከአማረኛ  ጋር  እንጅ    ከራያኛ  ጋር  አይደለም፡፡  በዚህም  መሰረት  የራያ  ልጆች  ለእነዚህ  አካባቢዎችና በነዚህ  አካባቢዎች ላላቸው  ሁለንተናዊ  መስተጋብር እንደሚከተለው  በአማረኛቸው  ተቀኝተዋል ፡፡

ለመለሎዋ ኮረዳ ፡-

 • እንደራያ ሜዳ  ለጥ  ያለው  ወገቧ፣

መቼ  ያስታውቃል    ራቧ  ጥጋቧ፡፡

 • አላማጣ ውየ ዞብል  አቀናለሁ ፣

አታርጊኝ  ጣል ጣል  አያል  ሰው  አውቃለሁ፡፡

 • አላማጣ ውዬ መልሼ  አለማጣ

ከበሽታየ ላይ  በሽታ  ላመጣ፡፡

 • ዋጃ ገበያ  ላይ  ቁጭ  ብየ  እንደለማኝ፣

ወይ  እሷን  አላገኝ  ወይ  ገበያ አልቀናኝ፡፡

 • ሳስባት አድሬ  ሲነጋ  መሆኒ፣

ሲሸተኝ  አደር  የድርምሟ ( ሹርባ) ቁኒ፡፡

 

 • እሪኩም እሪኩም….. እሪበል  ኮረም፣

አርብ አርብ  ይሸበራል  ኢየሩሳሌም፡፡

አሁን  ላይ  ደግሞ  አለማጣ  ላይ  ተቀምጠን “ራያ  አይደለም ምድሩ  ሰማዩም  የኛ ነው ” እያልን   ትግሬ  አስተናጋጃችንን ፡-

 • በአማረኛ አናግሪኝ  አናግርሻለሁ፣

የተውሶ  ምላስ (ትግረኛ)  ከየት  አመጣለሁ፡፡

( ጠበቃ መንግስቱ  ዘገየ) ወ.ዘ.ተ

እያልንና እየተባለ    ራያዎች (  ወሎየዎች / አማራዎች)  በአካባቢዎቹ ላይ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሀለዎታችንን ገልጸንባቸዋል ፡፡ ስለሆነም ራያ  ከአማራዎችና  ከአማርኛ  ጋር  እንጅ  አሁን  ከሚቀነቀነው  ንኡስ  ራያዊ  ማንነት  ጋር  ስነቃላዊ  ሃለዎት  የለውም፡፡

ማጠቃለያ

ራያ   የአካባቢ ስም  መሆኑ  እንደተጠበቀ  ሆኖ  በታሪክም ሆነ  በአሁናዊ  ግኝቱ   የወሎና  የአማራ  ህዝብ  ውብ እና  ደማቅ  አካል  ነው ፡፡  በመሆኑም  ከ1983ዓ.ም  ወዲህ የተደረጉ   አካባቢያዊና  ስነህዝባዊ (Demografy) ለውጦችን  ተከትለው  የራያ  ማንነት  አስመላሽ  ኮሚቴዎች  ህወሀት  ግዛቱን  ለማስፋፋትና  አማራን ለማሳነስ  እንዲሁም እነሱን  ለመጨቆንና    ትግሬ  ለማድረግ  የሄደበትን  ከቅኝ ተገዥነት  ጋር  እኩል  ውጤት  ያለውን  የውስጥ  ጭቆና( internal  domination) የወለደውን   ቁንጽል  አተያይ  መሰረት  አድርገው  የራያነት  ብሄረሰባዊ  ማንነትና  የልዩ ዞንነት  ጥያቄ  ማንሳታቸው  ተገቢ  አይደለም፡፡

የዚህ  ጥያቄ  ተገቢ  አለመሆን  የሚረጋገጠው  ደግሞ  ከአላ  እስከ ኤቦ ወንዝ  ድረስ  የተነጠፈውን  አባቶቻችን  ዝንታለም  አንድነቱን  የሚመሰክሩለትን  ራያ  ራዩማን  ለሁለት  የሚከፍልና  አንድ  በሆነ ህዝብ  በእናትና  በልጅ ፣በአክስትና  በአጎት  ፣በእህትና  በወንድም   መካከል  የበርሊንን ግንብ    ያክል  ልዩነት ፣ መራራቅንና  መለያየትን የሚፈጥር ስለሆነ  ነው፡፡

ከዚህ  በተጨማሪ ጥያቄውና  ጠያቂወቹ  የግንቦት 20  ፍሬዎች   ስለሆኑ   በእነዚህ  የራያ  አካባቢዎች  የሚገኙትን  እህት  ወንድሞቻችን  ልክ   እንደ ህወሀት  ትግርኛ  እስከ አሁን  በማያውቁትና   በማይችሉት  (ራይኛ)  ቋንቋ  ዳግሞ  እንዲጨቆኑና   እንዲሰቃዩ  ከማድረጉ  በላይ  አዲስ የማንነት  ቀውስ  ውስጥ  የሚከታቸው ነው፡፡

ይህ    አዲስ  የማንነት  ጭቆና  ደግሞ  እስከ  አሁን  ድረስ  ከነበረው  የህወሀት   ጭቆና  እጅግ  የከፋና  የበረታ  ነው፡፡ ምክንቱም ላለፉት 30 አመታት ከዛሬ  ነገ  ከወሎየዎችና  ከራያ ቆቦ  ዘመዶቻችን  ጋር  እንገናኛለን በማለት  በተስፋ ሲታገሉ   የነበረና ማንነታቸውን  ጠብቀው  እንዲኖሩ   ስላደረጋቸው   ሲሆን፡  አሁን  ላይ  ግን  ከኛ  ከለይዋቸው  ምንም  ተስፋ  ስለሌላቸውና  በአገራቸው  ውስጥ ባይተዋር  እንዲሆኑ  ስለሚያደርግ  ነው፡፡

ስለሆነም ራያነት ህወሀት  የጫነባቸውን  አዲስ  የትግሬነት   ማንነት  በመቃወምና    በህወሀት የሀሰት ትርክት  መሰረት አማራነትን  በመፍራት  እንዲሁም  በዘመን  ሂደት  የገጠማቸውን   ውህድ  ማንነት  ለመሸፈን  የፈጠሩት  አዲስ  ማንነት  ስለሆንና  አባቶቻችን  የራያ  ገበሬዎች  አመጽን  የቀሰቀሱት  መደባዊ  ጭቆናን  ለመታገል  እንጅ    ለማንነት ትግል  ስላልሆነ፤  ከዚህም  በላይ ከህወሀት   አገዛዝ  ነጻ  ለመውጣት  ከወሎየዎች  ጋር  ለመገናኘት   እስከ  አሁን   የፈሰሰው  የወንድሞቻችን  ደም  ከንቱ  እንዳይቀር  ራዴፓዎችና  የራያ  ማንነት  አስመላሽ   ስብስቦች  የራያ  ብሄረሰብነትና  የልዩ  ዞንነት  ጥያቄያቸውን  በድጋሜ   አጢነው  የራያን  ህዝብ  አንድነት  በሚመልስ መልኩ ትግል   ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እኛም ወገኖቻችንን ለዳግም ጭቆና ሊዳርጉ የሚያኮበኩቡ አካላትን አጥብቀን ልንታገል ይገባል እላለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!

 

4 Comments

 1. ትግሬ፣አማራ፣ራያ፣ኦሮሞ፣የሚል የዘር ቆጠራ ለኢትዮጵያ ደሀ ገበሬ ምን ይፈይድለታል? አንድ ዳቦና አንዲት ጣሳ ወሃ ሆኖ ነፍሱን ሊያቆይለት ይችላል? ህዝቡ በረሃብ እየተገረፈ፣በወባና ንዳድ እየተቃጠለ ሲስቃይ፣እናንተ የቦታና የመንደር ስም እየጠቀሳችሁ ሽንጥሽ ዳሌሽ፣በሚል አጉል የመንደር አለሌ ዘፈንና ተረት ውስጥ መዘፈቃችሁ እጅግ ያሳዝናል። እስቲ መጀመሪያ መሰረታዊ የስው ልጅ ፍላጎቶች ምግብ፣መጠለያ፣ጤና ለህዝቡ መድረሱን አረጋግጠን የአረቄ ቢት ጨዋታው ከዚያ ቀጥሎ እንደርስበታለን። ሀገሩ ለእስተዳርና ለአገልግሎት በሚያመቸ መልክ ፣በጥናት ላይ በተመስረተ መልክ ፣ተደራጅቶ፣ ህዝቡ በአንድ መንግስት ስር ሆኖ ግብሩን እየከፈለ ቢተዳደር ምን ችግር አለው?ዋናው የመንግስት አስተዳደርና እስራር ግልፅና ከሌብነት የፅዳ መሆን መቻሉ ነውና ከመቀሌ እስከ፣ሞያሌ፣ከጋምቤላ እስከ ቶጎጫሌ ፣ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረት አፍርቶ ቤት መስርቶ በእኩልነት በህግ እስካደረ ድረስ፣ምን ችግር አለው?

 2. ለራያ ወንድሞቻችንን እንድረስላቸዉ አብይ የትግሬዎችን ግዛት ለማግኘት እጅ መንሻ ሊያደርጋቸዉ ነዉ። እናንተም በርትታችሁ ታገሉ ጀግናዉ የወሎ ህዝብ ማንነትህ ከተቀማ ምን ቀረህ?

 3. ይስተካከልልኝ
  ለራያ ወንድሞቻችንን እንድረስላቸዉ አብይ የትግሬዎችን ድጋፍ ለማግኘት እጅ መንሻ ሊያደርጋቸዉ ነዉ። እናንተም በርትታችሁ ታገሉ ጀግናዉ የወሎ ህዝብ ማንነትህ ከተቀማ ምን ቀረህ?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.