ሕዝብ እንዲሰማህ ሰፊ አፍ ይኑርህ!

4

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

እንደሚታወቀው ለመስማት ተናጋሪና ሰሚ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ተመራምሮና መጻሕፍት አገላብጦ ሳይሆን ተባራሪ ዜናና አሉቧልታ በጀሮው ከጣራ እንደተቸከለ አንቴና እየቃረመ ያወቀ ለሚመስለው መንጋ ለመስማት እንደ ዲሽ የተንከረፈፈ ጆሮ ለመናገርም እንደ ሰማይ የተከፈተ አፍ ያስፈጋል፡፡ የፊደል ቆጣሪ ማይም እንደ ዝናብ አብራ በፈላባት ኢትዮጵያ ቀርቶ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች በሞሉበት አሜሪካና አውሮፓም ሰፊ አፍ ዘወትር ያሸንፋል፡፡ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ሰፊ አፍ አሸንፏል፤ እስከ ዳግም ምጣትም ሰፊ አፍ ያሸንፋል፤ ምንጊዜም ሰፊ አፍ ያሸንፋል፡፡

ጠቢቡ ሶቅራጥስ መርዝ እንዲጠጣ የተደረገው በድልዱም ገዥዎች ሰፊ አፍ ቅስቀሳ የተነዳ ሕዝብ “ሶቅራጥስ ይገደል” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነው፡፡ የአቴንስ ሕዝብ ይህ ጠቢብ እንዲሞት ድምፅ የሰጠው ብችኛ መተማመኛው ጀሮው ስለነበርና  በዘመኑ የነበሩት አረመኔና ዱልዱም ገዥዎች ዋና መሳርያም ሰፊ አፍ ስለነበረ ነው፡፡ የጠቢቡን ሐሳብ የፈሩት ዱልዱም ገዥዎች “ሶቅራጥስ ወጣቱን እያበላሸና አማልክቶችንም እየከዳ ነው” እያሉ እንደ ታምራት ላይኔና በረከት ስሞን ያሉ ካድሬዎች ሲሰብኩ መንጋው ጆሮውን እንደ ሰፌድ እየዘረጋ ሰማቸው፡፡ የሕዝቡን መታለል የተገነዘበው የገዥው ቡድንም ሶቅራጥስ ሔምሎክ ጠጥቶ እንዲሞት አደረገው፡፡

እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለውም እንደ ኢሀዴጎች ሕግን እያነበነቡ ከሕግ ግን አንዲቱንም በማይፈጥሙ ፈሪሳውያን ሰፊ አፍ የተሰበከ ጆሯማ መንጋ “ስቀለው! ስቀለው! ስቀለው!” የሚል ድምፅ ሶስቴ ስላሰማ ነው፡፡ ሰፊ አፊ እንደዚህ ነው! ጠቢቡንም መለኮትንም የማጥፋት ኃይል አለው! ተቀናቃኝ አፍ በልጓም ካልገታው ሰፊ አፍ እንኳንስ የሰውን ሐሳብ መንፈስ ቅዱስንም የማጣጥፋት ጉልበት አለው፡፡ 

አውሮጳውያን አፍሪካን፣ ኤሽያንና ላቲን አሜሪካን ለክፍለ-ዘመናት የገዙት በጠመንጃ ሳይሆን በሰፊ አፍ ነው፡፡ ሕዝቡም የተገዛላቸውን ጉልበት ስለሌለው ሳይሆን ይተማመን የነበረው በጉልበቱ ሳይሆን በጆሮው ስለነበረ ነው፡፡ አውሮጳውያን “ልናሰለጥንህ ከመለኮት ተላክን!” እያሉ የማያምኑበትን መጽሐፍ ቅዱስ ተቀናቃኝ በሌለው ሰፊ አፋቸው ሲሰብኩት የመኪና የጎን መስታዎት በመሰለው ጆሮው እየጠቀለለ ከልቡና ከመንፈሱ አስገባው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን ኢሐዴግ የሚባለው ከሀዲ እስከመጣ ድረስ በአሮጳውያን በቀጥታንም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልተገዙት እንደ ዓባይ በርሃ የተከፈተውን የአውሮጳውያን አፍ የሚዘጉ እንደ መምህር አካለ ወልድ፣ አራት ዓይናው ጉሹ፣ አስረስ የኔሰው፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ ቀኝ ጌታ ፍታሄ ንጉሴና ሀዲስ አለማየሁ ያሉ አፈወርቆች ስለነበሯት ነው፡፡ ሰይጣን የከፈተውን የኢሀዴግ አፍ እሚዘጋው ለገሰ ያሰለጠነው የኢሀዴጉ ፓስተር ሳይሆን መለኮት የከፈተው የዮሐንስ አፈወርቅ አፍ ነው፡፡

ጨፍጫፊው ስታሊን በሩሲያ እንደ አምላክ ይታይ የነበረው ሬዲዮኑን፣ ጋዜጣውና ሌላውንም የሕዝብ መገናኛ ስለተቆጣጠረው ነበር፡፡ አረመኔው ሂትለርም ብዙ ተከታይ ያፈራውና አውሮጳን ያንበረከከው በጠምንጃው ሳይሆን በሰፊ አፉ ነበር፡፡

ሰይጣኑ ለገሰ ዜናዊ ኢትዮጵያን እየሸጠ ጃርት የጋጣት ድንች አስመስሎ በስልጣን የሰነበተው እንደ ዳሎል ጉድጓድ በጠለቀውና በሰፋው ይሉኝታ ቢስ አፉ ነበር፡፡ ለገሰ ተቀናቃኝ አፎችን ጥርቅም አርጎ የዘጋው ሕዝብ እርሱ እሚለውን ብቻ እንዲሰማና እንዲቀበለው ነበር፡፡ ለገሰ ባሪያዎቹ በተከሉለት ቴሌቪዥንና ሬዴዮ የሚለቀውን ውሸት ሃያ አምስት ዓመታት ስለሰማ ከልቡ “ባለራዕይ መሪ” እንደነበር ዛሬም የሚያስበውን ጎጋ ቤት ይቁጠረው፡፡ ለገሰ በሞተበት ወቅት ልጆቻቸው ሊጠይቁ የመጡ እናቶች “አቶ መለስ ስለ ልማት ተናግረው የማያባሩ ሩህሩህና ለሕዝብ አሳቢ መሪ ነበሩ” ብለው እንባ ያፈሰሱ አማራ እናቶች አይቻለሁ፡፡

ለገሰ እንደ ጠላት በሚቆጥራቸው አማሮች ሳይቀር “ባለ ራዕይ መሪ” እስከ መባል መድረሱ የሚያሳየው ሶቅራጥስን መርዝ ያስጠጣውና ክርስቶስን ያሰቀለው ሰፊ አፍ ሰይጣንንም የማንገስ ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው፡፡ ለገሰ ዜናዊ ሰይጣን በመለኮትን አምላኪው አማራ የላከው ሰይፍ እንደነበር ሥራው ምስክር ነው፡፡ ሥራው ቢመሰክርም ተቀናቃኝ ያልነበረው ሰፊ አፉ በአካልና በመንፈስ አኮስምኖ ሊያጠፋቸው በመጣው አማራ ሳይቀር ቅዱስ ሆኖ እንዲታይ አደረገው፡፡ የአውሮጳን ወገብ ሰብሮ የዘላለም ሕመምና ውርደት የሰጠው አማራ በለገሰ መሸወዱ የሚያሳየው ኔቶ እንኳን የአፍን አንድ አስረኛ ኃይል እንደሌለው ነው፡፡ ለገሰ አማራን የጎዳው ብአዴን በሚባል ማፈኛ አፍኖ ዲዳ በማድረግ ነው፡፡ የለገሰን ወንበር የወረሰው ፓስተርም አማራን መግዛት የሚሻው ይኸንኑ ማፈኛ ከድሮውም የበለጠ በማጥበቅ ነው፡፡ የአማራ ጉዳቱ እሚጠገነውና ከመጥፋትም እሚድነው ይኸንን ብአዴን የሚባል ማፈኛ ቦጭቆ ዲዳነቱ ሲቀርና ራሱ ስለ ራሱ መናገር ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ ያልታፈነ አፍ ሶስቴ “ስቀለው! ስቀለው! ስቀለው! ” እያለ የማሰቀልና የመግደል ኃይል እንዳለው ሁሉ ሶስቴ “አድነው! አድነው! አድነው!” ብሎ የማዳንና ዘርን የማትረፍ ኃይልም አለው፡፡

ለገሰ አማራን በብአዴን አፍኖ ሲጨረግድ በጆሮ ጠቢነት፣ በስልክ ጠላፊነትና በታማኝ “ኮሎኔልነት” ሲያገለግለው እንዳልኖረ ሁሉ ፓስተር አቢይ በአማሮች “ከሰማይ የወረደ መሲህና ወንዝ አሻጋሪው ሙሴ!” እስከ መባል የደረሰው በሕዝብ ደም ተሻግሮና በሰማእታት አጥንት ተንጠልጥሎ ከሃያ አመታት ባርነት ተላቆ አፉን ስላሰፋ ነው፡፡ ከወንጀለኞች ፊት እንደ ሊማሊሞ ገደል የተቦረገደ አፍ ሳይቀር ግዙፍ ኃይል አለው! የተቦረገደ አፍ ጆሮ እየጠባና ፖሊስ እያዘዘ ሕዝብ ያሰጨረገደውን የይድረስ ይድረስ ሎሌ ኮሎኔልም መሲህ አደረገው፡፡ 

አፍ ለጮሌው ብርሃኑ ነጋም ለሃምሳ ዓመታት የተጠቀመበት ትልቁ መሳርያው ነው፡፡ ብርሃኑ ነጋ አሻሮ ይዞ ወደ ቆሎ እየተጠጋ ቆሎውን ቀምቶ እየቃመ ባለቆሎን አሻሮ አስታቅፎ የሚሰድ ጩልሌ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይኸንን ጩልሌነቱን ያልተረዳ አቶ ኃይሉ ሻውልንና በግንቦት ሰባት ስም የተረሸኑትን ዜጎች ከሰማይ ቤት፣ የአርበኞች ግንባርን ሰራዊትን ወረታ፣ በእርሱ ስም ሽባ፣ ዓይነ-ስውርና ስልብ የሆኑትን የአማራ ልጆች ቤጌምድር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሸዋ ሄዶ መጠየቅ ነው፡፡ ብርሃኑ ነጋ አዲስ አበባ በቀይ ምንጣፍ በገባ በማግስቱ ለእነዚህ ሰማእታት ፍትህ ይጠይቃል ብለን ተስፋ ስናደርግ ከገዳያቸውና ከአሰቃያቸው ኢሀዴግ ጋር አስረሺ ምቺ የሚጨፍር ዓይን አውጣ ማገወልድ ሆኖ አገኘነው፡፡ 

ይኸንን ታሪክና ትውልድ የማይረሳው ክህደት የፈጠመው አብያው ብርሃኑ የወለደ አይጨክንም በሚል የጫት ቁማር ኢትዮጵያ እሚባል የመርካቶ ሙዚቃ ኢትዮጵያን አምጦ ወልዶ ባሳደገው በአማራ ጆሮ በሰፊ አፉ እያንባረቀ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እሚባለው የብርሃኑ የንግድ ሙዚቃ የማይጣፍጠው ቡድን ከደቡብ በቆንጨራ ሲያባርረው እየተመለሰ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ባህርዳርና ደብረ ማርቆስ እየተንከባለለ ይደንሳል፡፡ ወልዶ ያሳደጋት ኢትዮጵያ አንጀቱን እንደ ሰለሊት የምትበላው አማራም እንደ ውዷ እናቴ አንጀቱ እየተንሰፈሰፈ ያዳምጠዋል፡፡ ይህ ብርሃኑ እንደ ማይክል ጃክሰን እየተንከባለለ የሚደንስበት ሕዝብ ደሞ ብርሃኑ በአስራ ሰባት ዕድሜ ትግል ሲጀምር “ብሔራዊ ጨቋኝ” ሲል የኮነነውና ስልጣን ለመቆናጠጥ የፈለገ ጆቢራ ሁሉ ባጎረሰ የሚነከሰው መከረኛ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ብርሃኑ አሜሪካ በጠፈጠው ድርጅት ሥም ጥፍራቸው በጉጠት የወጣ፣ ህብለ-ሰረሰራቸው በጥይት ተቦድሶ ሽባ የሆኑና መፀዳዳት የተሳናቸው፣ ተሰልበው የመነኮሱና እንደ ሙጃ የተጨረገዱ ልጆች ወላጅ፣ ወንድምና እህት ነው፡፡ 

ብርሃኑ በድርጅቱ ሥም ለሞቱትና አካለ ስንኩላን ለሆኑት ፍትህ ይጠይቃል ብለን ስንጠብቀው ከገዳዮቻቸው ጋር በቁርባን ተጋብቶ “ጨቋኝ ብሔር” ባለው ሕዝብ ስም የወንበር ቅስቀሳ ሊያደርግ ልኻጩን ሲያዝረበርብ ተመለከትነው፡፡ በዚህ የስልጣን ቅስቀሳውም ጧት ጧት እንደ አሰፋ ማሩ፣ ፕሮፌሰር አስራትና ሳሙኤል አወቀ ያሉ ጀግኖችን ሥም እያነሳ ሕዝብ ሲያታል ያረፍዳል፡፡ ከሰዓትና ምሽት ደሞ እነዚህን ሰማእታት ከገደለው ኢሀዴግ ጋር  ሲሞዳሞድና እንደ ቀበጥ ልጃገረድ ሲወባራ ያመሻል፡፡ ይኸንን የመሰለ ዳግ ያጣ የፖለቲካ አመንዝራነት እየፈፀመም ሰፊ አፍ ስላለው ጆሮውን ተማምኖ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ይሰማዋል፡፡ ሰፊ አፍ በሬን መጥለፊያ መጫኛ ከያዘ አሳራጅና ካራ ከጨበጠ አራጅ ጋርም ያሳድራል፡፡ የሰፊ አፍ ኃይሉ ያስደንቃል!

እንደ ለገሰ፣ አቢይና ብርሃኑ ያሉ ዓይናውጣ ቅርድ አፎችን እየሰማ ሕዝብ ሶቅራጥስን ሲያስገድል የተመለከተውና ጆሮውን ብቻ በሚያምን ሕዝብ ተስፋ የቆረጠው ፕላቶ በሶፊስቶችና በደነዝ ገዥዎች የሚገዙትን ምሁራን ሲመክር “ከፖለቲካ ከሸሸህ በቀረጨጩ አይምሮዎች ትገዛለህ” ሲል መክሯል፡፡ 

እኔም እንደ አቅሜ አገራችን ካበረከተቻቸው ብቁ ጸሐፊዎች በተጨማሪ ከሶቅራጥስ በፊት የእነ ቴልስንና ፓይታጎረስን፤ በሶቅራጥስ ዘመንም የእነ ፕላቶንና አርስቶትልን፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የእነ ፍራንሲስ ቤኮንን፣ ትሆማስ ሆብስን፣ ሎክን፣ ስፓይኖዛን፣ ቮልቴርን፣ ዳቪድ ሆምን፣ ሮዙን፣ በርክሌየን፣ ኢማኖኤል ካንትን፣ ኒቼን፣ ሚልስን፣ ሄግልን፣ ማርክስና ሌሎችም ጨልፌ አንብቤ በዚህ መነፅር ዓለምን ሳጤናት ከጉልበተኞችና ከአፈ ሰፊዎች መዳፍ ወጥታ እንደማታውቅ፤ ወደፌትም ከጉልበተኞች ክንድና ከአፈ ሰፊዎች እጅ እንደማትወጣ ተገንዝቤአለሁ፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ ሰፊ አፍ እንኳን ጉልበትን መንፈስ ቅዱስንም አቅቶ ዓለምን ሲገዛ እንደሚኖር ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ እሚሰማ ከተገኘ ለሕዝብ በተለይም ልሳኑ ተዘግቶ ለእርድ ለተዘጋጀው አማራ “እንዳየኸው አፍህን ከዘጋህ ባለቤት እንደሌለው ጫካ የጨረገደህ መሲህ ነኝ! ፃድቅ ነኝ! ሙሴ ነኝ! ኢያሱ ነኝ” እያለ ሊሰብክህ ይመጣል!” ስል እመክራለሁ፡፡ “እንደ ስታሊን፣ ሂትለር፣ ለገሰ ዜናዊ፣ አቢይ አህመድ፣ ብርሃኑ ነጋና ሌሎችም ይሉኝታ ቢሶች ለመደመጥና ስልጣን ለመጨበት ከፈለክ እንደ ዓባይ ሸለቆ የተቦረገደ ሰፊ አፍ ይኑርህ!” ስልም አስጠነቅቃለሁ፡፡ 

ሰምታችሁ ይኸንን ምክር ለሕዝባችሁ ላደረሳችሁና ሕዝባችሁን ከመጥፋት ላዳናችሁ ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡  

የካቲት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.