የራሱን ሽንፈት የተነበየ በዓለማችን የመጀመሪያው ሰው – ይሄይስ አእምሮ

1

ይሄይስ አእምሮ (yiheyisaemro@gmail.com)

ሰዎች ስለሰዎች የእውነትም ይሁን የሀሰት ትንቢትን ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶችም ስለራሳቸው የወደፊት ሁኔታ ምናልባትም ስለአሟሟታቸው የሚተነብዩ አይኖሩም አይባልም፡፡ የራሱን አሸናፊነት እንጂ ሽንፈቱንና ውድቀቱን የተነበየ ግን በበኩሌ አንድ ሰው ብቻ አውቃለሁ፡፡ እርሱም የኦሮሚያው ምክትል ጠ/ሚኒስትር  አቢይ አህመድ አሊ ነው፡፡

ወደሥልጣን እንደመጣ ህዝብን ያስገረመ አንድ ጥሩ ነገር ተናገረ፡፡ “መግደል መሸነፍ ነው” አለና አዳሜን በአግራሞት አስደመመ፡፡ “እንዲህ ያለ መሪ ከኢሕአዲግ ጉያ መውጣቱ የእግዜር ተዓምር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም” ብለን ሁላችን ማለት ቢቸግርም ቢያንስ አብዛኞቻችን በደስታ ጮቤ ረገጥን (ኧረ እንዲያውም “በሱ የመጣ ባይኔ መጣ” ያልንም ነበርን)፡፡ አጅሬ አቢይ የተናገረው ትንቢት ወደራሱ መዞሩን ለመረዳት ግን እንደወያኔ ዘመን 27 ዓመት መጠበቅ ሳይኖርብን ከሦስት ዓመታትም እጅግ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ገሃድ እውነቱ ወጣ፡፡

አንድ የፐርሽያ ንጉሥ ነው አሉ፡፡ ከጎረቤት መንግሥት ጋር ይጣላል፡፡ ከጠቢባን ነቢያቱ መካከል በጣም ዝነኛ የሆነውን አንዱን ይጠራና “ከአንድ መንግሥት ጋር  ጦርነት መግጠም አስቤያለሁና ምን ይታይሃል? አሸንፍ ይሆን”? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ነቢዩም “ንጉሥ ሆይ! አንድ ታላቅና ስመጥር መንግሥት እንደሚያጠፉ ይታየኛል!” ሲል ይነግረዋል፡፡ በዚህ ትንቢት ልቡ እንደኦህዲድ/ኦነጉ አቢይ አህመድ ያበጠው ንጉሥ “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” ብሎ በደርጉ አማርኛ ባለ በሌለ ኃይሉ ያን የጎረቤት መንግሥት ሊወር ይነሳል፡፡ ግን ብዙም ሳይፋለም የራሱ መንግሥት እንኩትኩቱ ይወጣና ንጉሡ እግር አውጭኙን ሸሽቶ አንዱ ሸጥ ውስጥ ይወተፋል፡፡ ዙፋኑና ክብሩም ከነቤተ መንግሥቱ በባላጋራው የጎረቤት ንጉሥ ይወረሳል፡፡ ይህ የተሸነፈ ንጉሥ እንደምንም ብሎ ያን ነቢይ ያገኘውና “ታላቅ መንግሥት ትጥላለህ አላልከኝምን? ምነው ጉድ ሠራኸኝ!” ብሎ በቁጭት ይጠይቀዋል፡፡ ነቢዩም የዋዛ አልነበረምና “ታዲያ ምን አጠፋሁ? ይሄውና የራስዎን ገናና መንግሥት ለሽንፈት አልዳረጉምን?” ይለዋል፡፡ እውነት ነው፡፡

አንዳንድ ትንቢት ቀጥተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ትንቢት ደግሞ የግልብጥ ነው – በአተረጓጎም ስህተት ወደባለቤቱ ይዞራል፡፡ ፈረንጆቹ Self Fulfilling Prophecy የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ በላይኛው አንቀጽ የተገለጸው ሞኝ ንጉሥ ያደረገውን ትንቢት-ነክ ሕፀፅ ዓይነት፡፡

ነገር አሳመርኩ ብሎ ራሱም በቅጡ ያልገባውን “መግደል መሸነፍ ነው” ብሎ የተናገረው  አቢይ አህመድ ተሸንፏል፡፡ ንግግሪቱ እርግጥ ነው ወርቅ ናት፤  ምንም እንከን አይወጣላትም፡፡ ችግሩ አተገባበሩ ላይ ነው፡፡ መናገር ደግሞ እንደማድረግ አይቀልም፡፡ ከነተረቱ “ለአፍ አቀበት የለውም” ይባላል፡፡ አቢይ ተቀባይነትን ለማግኘት ያኔ ያልዘባረቀው ነገር አልነበረም፡፡ ይሁንና ልጁ በማስመሰል እንጂ በጥበብ ባለመብሰሉ እየሆነና እያደረገ ያለውን ሁሉ ከመሆንና ከማድረግ የሚያግደው ምድራዊ ኃይል እስካሁን ሊገኝ አልቻለም፡፡ አሳዛኝ ሀገራዊ ክስተት፡፡

ለማንኛውም አማራ የሚባል ዘውግ አለ ካላችሁ አማራ በሞቱ አሸናፊ ነው፤ ይህን ቋሚ እውነት መረዳት አስፈላጊ ነው – ሟች ምን ጊዜም አሸናፊ ነው – የዕዳ ቅራቅምቦውን ለገዳይ አስረክቦ ይህችን በወንጀለኞችና በኃጢኣተኞች የቆሸሸች ምድር ትቶ ወደቀጣዩ ዓለም ያልፋልና፡፡ እየሞተ የሚያሸንፍ ሕዝብ እንደ አማራ አላየሁም፡፡ አማራ ከሥልጣንም፣ ከሀብትም፣ ከሀገርም ከወጣና ከተሰደደ በትንሹ 30 ዓመት ይሆነዋል – ወደ ውጭ የተሰደደውን ትተን በሀገር ውስጥ ያለው አማራ ራሱ በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር ነው፡፡ በአክራሪዎች አስተሳሰብና እምነት አማራ የኢትዮጵያ አንደኛው ባለቤት አይደለም – ለመገደልና ለመፈናቀል ብቻ የተፈጠረ የነሱ መጫወቻ አሻንጉሊት መስሎ ሳይታያው አልቀረም፡፡ አሸነፍነው ያሉ የሁለት ነገዶች አክራሪ አባላት እየተፈራረቁ ይህን ከምኑም የሌለበትን አማራ እጃቸው በገባ ዱላ ሁሉ እንደ አህያ ይነርቱታል፡፡ እርሱም እነሱን ደስ ይበላቸው ከሚል አዘኔታ ይመስላል ዝም ብሎ ይቀጠቀጥላቸዋል፡፡ እነሱም አማራን በመግደልና በማሰቃየት እንዲሁም በማደህየት የሚረኩ አይመስሉም፡፡ የነሱ ችግር ሥነ ልቦናዊ ነው፡፡ የአማራው ደግሞ እጅግ የተለጠጠ ሆደ ሰፊነት፡፡ ሆደ ሰፊነቱሞ የአማራን ጠላቶች እርር-ቅጥል ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ አማራ ወደአማራነት ለመውረድ አለመቻሉ ይብሱን ያንገበግባቸዋል፡፡ የሞቱ መንስኤም አማራው አማራ ሆኖ እንደነሱ በመጥበብ በዘረኝነት የድንቁርና ካባ ተጀቡኖ አካኪ ዘራፍ አለማለቱ ነው፡፡ ዘረኝነት እንደሚያሳውር አብዛኛው አማራ ይረዳልና ወደዚያ አረንቋ አይገባላቸውም – የተወሰነ አዝማሚያ ቢታይም ቁጭት-ወለድና ጊዜያዊም ነው፡፡ አማራው የመረጠው የትግል ሥልት ታዲያ እየሞቱ ማሸነፍን፣ እየተሰቃዩ ጠላትን ማሰቃየትን ሆነ፡፡ ይህ የትግል ሥልት መጨረሻው ለሁሉም ግልጽ ባይሆንም ለአሁኑ ግን ፍቱን የማጥቂያ ዘዴ ይመስላል፡፡ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥረው በአማራ የሚበሳጩ ካሉ፣ ሀብትና ሥልጣንን ሁሉ በእጃቸው አስገብተው ሳለ ስለ አማራ በተሰበከላቸው የሀሰት ትርክት ሳቢያ በጥላቻ ተውጠው እንቅልፍ የሚነሳቸውና የነሱን መኖር እንኳን የማያውቀውን፣ ከአድማስ ማዶ ሀገር እንዳለ የማይረዳውን ምስኪን አማራ በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ የሚረኩ የ8ኛው ሽህ ጭራቆች ከተፈጠሩ ጥፋቱ የአማራ ሣይሆን የአልጠግብ ባዮቹ የአክራሪ ኦሮሞዎችና እነሱን የፈጠሩት ሰሜነኞች ነው፡፡ በተበላሸ አእምሮ አገር አይተዳደርምና ፈጣሪ ይሁነን፡፡

አቢይ አህመድና ሽመልስ አብዲሣ ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ የሚገድሉት ሽንፈታቸውን ለመሸፈን ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ሰው ሌላውን ሰው የሚገድለው በሆነ ትልቅ ጉዳይ ሲጣላ ነው፡፡ በንግግር የማይፈታ ችግር ገጠመኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ባላጋራየ ነው ያለውን በተመቸው መንገድ ይገድላል፡፡ መግደል በምንም መልኩ ትክክል ባይሆንም ግድያው ግን ምክንያታዊ ነው፡፡ አንድን ሕጻን ወይም አንዲትን ሴት አማራነቷዋን እንኳን ሳታውቅ ሕጻናቱንም ሴቲቱንም አማራ ናቸው ብሎ መግደል ግን ከመሸነፍም በላይ ነው፡፡ ይህ ስም የለሽ ዕኩይ ድርጊት ኅሊናን የመሳትም ውጤት ነው፡፡ ኅሊናውን የሳተ ሰው ደግሞ እንኳንስ ሀገርን ቤተሰቡንም መምራት አይችልም፡፡ መግባት ያለበት የአእምሮ ህሙማን የሚታከሙበት አማኑኤል ሆስፒታል ወይም ወደሱ ቅርንጫፎች ነው፡፡ በሉ እነዚህን ዕብዶች ከዚህም በላይ ብዙ ሳያጠፉን ወደ ጠበል ወይም ወደአእምሮ ህክምና ማዕከል ውሰዱልን፡፡ በነገራችን ላይ እነአቢይ በነሱ ቤት ጤነኞች ናቸው፤ በሽተኞቹ እኛ የምንቃወማቸው ነን፡፡ እንደንጉሡ የሚያጎነብሱ ቁጥራቸው የትዬለሌ መሆኑ ደግሞ ዕብዶቹን የልብ ልብ እየሰጠ ይበልጥ እንዲያብዱ ማድረጉ ልንቋቋመው ያልቻልነው ችግር ሆኗል፡፡ ይሄውና አለማየሁ ገ/ማርያም የተባለው ለሀገሩ ብዙ የደከመ ሰውዬ እንኳን  ከቢዮንሴ ቀጥሎ ለአቢይ አህመድ 46ኛው  ጽላት እንዲቀረጽለት ለፓትርያርክ ጽ/ቤት አመልክቷል እየተባለም አይደል? ከምር ግን መጪው ጊዜ ጨለማ ይመስላል፤ ዳርዳርታው አያምርም፡፡ ሦርያና ሩዋንዳ፣ የመንና ሶማሊያ ወደኢትዮጵያ ሰተት ብለው እየገቡ ነው፡፡ እነአቢይ ከዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕልቂት ምን እንደሚያርፉ ካለቅንላቸው በኋላ እንደዕድል ሆኖ የሚተርፍ ሰው መኖሩ አይቀርምና የሚያየው ይሆናል፡፡

 

1 Comment

  1. አብይ አብይ ብለን ላንቃችን እስኪታክተን ድረስ እየጮህን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ ዳያስፖራዎችም ሁላችንም ሰልፍ ወጥተው ፎቶውን በአይነት በአይነት በትልቁ እያሳተምን ተሸክመን አንግሰነው ይዘን በብዛት አብይ ያሻግረናል እያልን እየጮህን ከአለም ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ የአብይን ፎቶግራፍ ስናነግስ ሰኢሳት በዩትዩብ ታይተን ከነበረ አንድ ወር እንኳን አልሞላውም። አለማየሁም ሆኑ ቢያንሴ ሳይነግሱት እኛ አንግሰነው።

    ጃዋር የለ ፣ እስክንድር የለ ፣ ደብረፅዮን የለ ፣ ልደቱ የለ ፣ በቀለ ገርባ የለ ፣ ዳዉድ ኢብሳ የለ ፣ ይልቃል ጌትነት የለ… ፣ማንም በሌለበት ያለተቀናቃኝ ነግሶ (ብርሀኑ ነጋም በቋፍ ተንጠልጥሎ ቢበዛ ቢበዛ የአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሆን ነው)፤ ታድያ ማን ተቀናቅኖት አብይን ለንግስናውማ? እዛው እንደለመደባቸው ፖርላማው ካልተካው፤ ቦምብ አይነካው ፤ ጥይት አይጠጋው ፤ በአውስትራሊያ ሀገር ከብት የሚያግዱበት ሄሊኮፕተር መንጋውን አስደንብሮበት አይጨፈለቅ በኢሬቻው ላይ ።

    አብይ አህመድ ሲፈልግ ሲያሻው የኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ስብሰባን ላይ ያለ ፍቃድ አስቀድሞ ሳይናገር ቀጠሮ ሳይይዝ የቅዱስ ሲኖዶሶችን ስብሰባ በር አስበርግዶ ገብቶ ሲኖዶሱን ይደሰኩራል። ደግሞ ከፈለገም አብይ የተለያዩ ሀይማኖት መሪዎች በአንድ ላይ የሚያደርጉትን ስብሰባን ሲመራ እና እቅድ ነድፎ ሲያስተገብራቸው ይታያል። በሰሞኑ ደግሞ የሰሜን ካሊፎርኒድያን አሜሪካን እከባቢን የኦርቶዶክስ ጳጳስን፤ አብይ በሐሰት መስካሪ ከሳሽ ናቸው እያለ፤ ምዕመንኖቸውን እንዲያወግዙዋቸው ፤ ምዕመኖቻቸውም ካላወገዙዋችውም የሰሜን ካሊፎርኒያ አከባቢ ሀገረ ስብከቱን እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶሱም በአስቸኳይ እውቅና እንዲነሱዋቸው እያሳዘዘ ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.