ምነዋ ኢትዮጵያ ? -ፊልጶስ

2

እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ
እንደ ኤሳው ሆኑ ቡክርናቸውን ሸጡ
በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ – እንደ ሰማይ ከዋከብት
ምነዋ ኢትዮጵያ… በዛብሽ ጠላት?…

አፈርሽ ‘’ሰለሰ’’ ሜዳሽ ‘’አሜክላ’’ እሾክ አበቀለ
ተራራ ሸለቆሽ ‘’ጃርት’’ ተራባበት – ተራብቶም ፏለለ፤

ባላና ማገርሽ፣ ምሰሶሽ ተማሰ
ዞብ አምባሽ ተናደ፣ ወንዝሽ ደፈረሰ
ደም እንደ ጎርፍ ውሀ፣ በገላሽ ፈሰሰ
ውጭ ውስጥሽ ነቀዘ፣ ቤት አጉራሽ ፈረሰ
ምነዋ ኢትዮጵያ… ምፅአት ለአንች ደገስ?

የሚታመን ጠፋ፣ ለሰው ልጅ ያደረ
ውሸት ገኖ ናኘ፣ በቀየሽ ከበረ
ዘብጥያ ወረደ፣ እውነትም ታሰረ
ታሪክ ተረት – ተረት ብስራት ተበሰረ፤

የውርጃ ‘’አደፍ’’ ቅሪት – ጭንጋፍ አሳድገሽ
‘’ቃልቻ ዘር – ጎጥን’’ ደም ተጠማልሽ
ጉድ ውልዶ ‘’አነበረ’’ ጊዜ ማህፀንሽ
ምነዋ እናት ምድር… ያልታየ ታየብሽ?

በቆብ ደፊ ‘’ሻሻም – ቀሳሽ መሳይ ኮከብ ቆጣሪ ‘’
በቀን ሰባኪ፣ ማታ ጎፈሬ አበጣሪ
በደብተራ፣ ረጅም ተላባሽ፣ ካባ ተሞሻሪ
በዘንግ ተውረግራጊ – ወገብ አሳሪ፤

ማህደረ ቅርስ ‘’ፅባወተ – መምበርሽ’’ ታምሶ
በዛር ፈረስ ደመ ነውጠኛ፣ መቅደስሽ ‘ረክሶ፤

የዓምላክ ጻድቅ – ሰማአታትሽ ማደሪያ
ተቸበቸበቸበ ወ’ቶ ባደባባይ ደርቶ በገብያ
ታበዩ በእግዚአብሔር ምነዋ ኢትዮጵያ…?

አንድ ቀን ለተለበሰ ‘’ጥቁር ካባ’’ ለተደፋ ‘’ጥቁር ቆብ’’ በሚሉ ከ’ኔ ወዲያ የለም፣ ልሂቅ – አዋቂ ለሀገር የሚያስብ በሚመስላቸው እነሱ ብቻ የሆኑ ህዝብ፤ እየተራበ ያጠገባቸውን – እየታረዘ ያለበሳቸውን ሳይማር ያስትማራቸውን – ሳይከፍሉት የከፍላቸውን እየናቁት ያከበራቸውን – እየሞተ ያኖራቸውን በረሱት – በከዱት የገዛ ማንነት ወገናቸውን፤ በ’ነ ከረባት ….. ማ’ረጋቸው

በ’ነ ሆድ ….. አምላካቸው፤
በነሰለጠን ባይ ደንቁረው አደንቋሪ፣ ውስጠ ‘’አንኮላዎች’
ያልሆኑትን ለመሆን፣ በመስሎ አዳሪ፣ ህሊና ቢስ ሸፍጠኞች

በጥራዝ ነጠቅ ‘’ርዕዬት አለም’’ ሰባኪዎች
ያዩትን ያላዩትን ናፋቂ፣ በብልጭልጭ ኰተት ጎታች፣ ተሸካሚዎች
የሀገር ርዕይ በሌላቸው – በቅዥታም ተቀጥላ ጅራቶች፤

ተገዘገዝሽ!… ተቦረቦርሽ!… ተከፋፈልሽ!…
እንደ ቅርጫ ስጋ ገነጣጠሉሽ – ቸበቸቡሽ!

ምነዋ ኢትዮጵያ …?

ምነዋ ኢትዮጵያ …?

ባጠባሽ ተነከስሽ – ባጎረስሽ ተበላሽ

አመድ አፋሽ ሆነ የዚህ ዘመን እጅሽ።

 

ወግ ነው ሲዳሩ እንዲሉ ‘’ተማሪ’’ ነኝ በሚሉ

ይይዙትን አ’ተው ይጨብጡትን በዋለሉ

በመማሪያ የብዕር ደም ብልቃጥ፣ ውሀ በሞሉ፤

በኮሌጅ – ዩኒቨርስቲው በየትምህርት ቤት

የሚማሩት የሚያገኙት፣ የእውቀታቸው አይነት

የአድማሳቸው ልዕልና፣ የ’ርካታቸው ጥማት

የወጣትነት ህይወታቸው፣ የጥበባቸው እድገት፤

አባትን ሳያውቁ አያትን መጠየቅ

ሱሪ በአንገት ማጥለቅ – በጎጥ እድር መድረቅ፤

ዲስኮ …ጫት …ሀሽሽ ‘’ፓሪ’’ መንጎድ

ምነዋ እናት ሀገር …. ምነው ጠፋ ትውልድ።

እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ

እንደ ኤሳው ሆኑ ቡኩርናቸውን ሸጡ

በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ።

እንደ ባህር አሸዋ – እንደ ሰማይ ከዋከብት

ምነዋ ኢትዮጵያ… በዛብሽ ጠላት?…

 

ባህር-ወደብሽን፣ ልጆችሽን አ’ተሽ

ዙሪያሽ እሾህ ሆኖ፣ በጠላት ተከበሽ፤

እንድነት ተረስቶ፣ መደማመጥ ጠፍቶ

የባዕዳን መሳሪያ፣ አገልዩ በዝቶ፤

ርሀብ – እርዛት፣ ሰቆቃና ስደት

ስም መጠሪያሽ ሲሆን፣ አንች ባለሽበት፤

እርስ-በርስ መባላት፣ ትውልድን ሲጨርስ

የፍትህ ያለህ ባይ፣ ዓለምን ሲያዳርስ

እኛ ማለት ቀርቶ ‘’እኔ ብቻ’’ ሲነግስ፤

ወገኑን – ወገኑ ገሎ ሲፎክር

ሀውልት ሲገነባ፣ በአንች ምድር አፈር

ምፃ’ተኛ ሲኮን በገዛ ሀገር፤

ትንሳኤሽ ደረስ ብለን ስናናፍቅ

ጥላ ሲሆንብን ፣ ስቀርበው ሲርቅ፤

ጥቂቶች ሲስቁ፣ ብዙሀን ሲያለቅስ

ኃጢአት ተትረፍር፣ፎ ፅዋው ሞልቶ ሲፍስ

ዘመን አልፎ ዘመን- ዛሬም ደም ስናፈስ

ምነዋ ኢትዮጵያ…?

ምነዋ እናት ምድር… ዝም አለ የአ’ች ነፍስ?

 

ፍርድ ስጭ ዝም አትበይ፣ ተይ አትታበይ

ዋጋ ይከፈለው፣ በዳይ – ተባዳይ

ይቅርም አባብይን ወደፊት እ’ድናይ።…

 

የነፃ ህዝብ መልኩ ሰንደቅ አላማቸው

ባላደራ እናት ነሽ ቅርስ ያ’ርነታቸው።

 

አለሁ ካልሽ አለው በይ መስክሪ በራስሽ

ከአንገቱ ተቃንቶ ማየት የሚሽ ይይሽ።…

ታላቅ እንደነበርሽ፣ ታላቅ ትሆኛለሽ

ኑሪ ለዘላ’ለም ፣ ዓለም ኢትዮጵያ ነሽ።

—–//—— ፊልጶስ

e-mail: philiposmw@gmail.com

***ይህ ”ምነዋ ኢትዮጵያ ” የተሰኘ ግጥም የጻፍኩት ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን በአንድ ወቅት ለብዙሃን መገናኛ ቀርቦ ሲዘዋወር ነበር። አሁን እንዳንድ ጓደኞቸ እንደገና እንዳቀርበው ስለጠየቁኝና እኔም ስለአምንኩበት፣ መጠነኛ ማስተካከያ አድርጌ ለእንባቢዎች አቅርቢያለሁ።****

2 Comments

 1. እኛ ቀርቶ እኔ ሆነ ሲባል በተደጋጋሚ እሰማለሁ
  የቀረበት ምክንያት ምን ይሆን ብሎ የፈተሸን እንዴም አላየሁ

  በክፍል ውስጥ ያለ ዝሆን ሆኖብናል
  እኛ ስንል ሰነፍ ፖርሳይት ስለምንባል
  እኔ ስንል አግላይ ራስ ወዳድ ስለምንባል

  እኔ ብለን ሆዳችንን የብቻ መብላት ካስተማርን እየቆጥበን በኔባጀት ከከረምን አንራብም
  በእኛ ባጀት ግን በአንዴ አሙዋጠን በልመና መለማመጥ ነው በጥማት እና በልመና ልንከርም

  እዲሱ ትውልድ የቤቱን በርም አይከፍትም ለወለደችው እናቱ ዘንድሮ
  እንደቻይና ወይም ፣ እይጥም ፣ ጊንጥም ስለሚቀቅል ሳያስቀርም በረሮ

  ትዳርም እንደቀልድ ይገነባል እና እንደቀልድ ይፈርሳል
  የወንደላጤ ባለትዳር እና የሴተላጤ ባለትዳር በርክተዋል

  ወላጅ አሳዳጊ እየሆኑ ለእራሳቸው አንድ ፍሬ ዘልለው ያልጠገቡ ስነስርዐት የሌለው ታዳጊ
  በብቸኝነት በእኔ ኑሮ ስነስርዐት ቢያደርግ ባያደርግ የለበት ወቃሽ ቃል ሰንጣቂ

 2. ማለፊያ ነው ወገኔ። ችግሩ እኮ ምነው ብለው የጠየቁትም ለምን ተብለው የሚጠየቁ እየሆነ ነው። ላስረዳ። ነበር፤ የእስር ቤቱ ሃበሳ፤ ምስክርነት፤ ያ ትውልድ፤ ክህደት በደም መሬት የተሰኙትን መጽሃፍ ስታገላብጥ የምታየው አንድ የጋራ የሆነ ነገር አለ። ይህ ባህሪ ዛሬም በምድሪቱ ላይ አለ። ያም አትፈርስም እያሉ አፍራሽ ሥራ የሚሰሩ መብዛታቸው ነው። ያዘው ጥለፈው፤ ግደለው አጥፋው የሚለው ያ እይታ ወደፊት እንዳንራመድ ቀፍዶ ከያዙን እልፍ ነገሮች ቀዳሚው ነው። የማነ ንጉሴን በትግራይ መሬት ላይ ገድለው እንኳን ደስ አላችሁ የሚባባሉ ሙታኖች ባሉበት የራስንና የሃገርን ከፍታ ለማረጋገጥና በጋራ ለመስራት የማይቻል ነገር ነው። ለምሳሌ በ Sub-Saharan post, My views on the News, Hagere Tigray, Military and Foreign affairs, UN outlets, UNHCR entities, CNN, and numerous other news sites carry the alleged atrocities by the Eritrean and Ethiopian forces. የሚያቀርቡት መረጃ ግን የተለጣጠፈና በስማ በለው የሚነገራቸውን ነው። እነዚህ ለምሳሌ ተጠቀሱ እንጂ በሌሎች የሶሻል ሚዲያ ላይ የሚለጠፉት የፈጠራ ወሬዎችን እና ሽኩቻ ለሚመለከት እልፈት የማይገኝበት የእብዶች እሰጣ ገባ እንደሆነ ያስረዳል። ልብ ያለው መጠየቅ ያለበት ለማን ታዝኖ ነው ይህ ሁሉ ጋጋታ የሚደረገው? ለትግራይ ህዝብ? በጭራሽ። የትግራይ ህዝብ ሰዎች በስሙ ሲነግዱበት የኖሩና አሁንም በስሙ ሱዳናዊው/የትግራይ ነጻ እውጪ ነኝ የሚለው/ነጩና አረቡ በስሙ ትርፍ የሚያስገባብት ህዝብ ነው። ትርፍ በገንዘብ ብቻ አይመነዘርም። የፓለቲካ ትርፍም አለና! ዛሬ በሱዳን በረሃ በረሃብና በበሽታ የሚረግፉት አወጣጣቸው ለወያኔ ደጀን እንዲሆኑ እንጂ ሌላ ትሩፋት የለውም። ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የፈለጉትን እየከለከሉ እንደሆነ ከሥፍራው የሚወጣው ዘገባ ያስረዳል። በዚህ እብደት ነው እንግዲህ “ምነዋ ኢትዮጵያ” የምትለን። ሰው በሌላው ወገኑ ተጠቅቶ ላሸለበ ዘር አይቶ እንባ በሚያፈስበት ምድር ሰው መሆን ፍሬ ቢስ ነው። አኩስም ላይ የትግራይ ልጆች አለቁ ተብሎ ያየነው የጫማ ክምር ሱዳን ውስጥ የተነሳ ፎቶ እንጂ አኩስም የሆነ ነገር አይደለም። ይህን ስል ግን በሃበሻው ምድር ግፍ አይሰራም የትግራይ ልጆች አልሞቱም እያልኩ አይደለም። ግን ልክ እንደ በፊቱ ወያኔ አልቅሱ፤ ሞተብን በሉ፤ መሬት ቆፍሩ በማለት ሰዎችን እያንገላታ ያልሆኑትን ሆነናል በሉ እንደሚል እውነትን የተላበሱ የእርዳታ ሰራተኞች አጫውተውኛል። ጥያቄው ” ምነዋ ኢትዮጵያ” ሳይሆን ልቡ እንደ አለት የጠጠረው፤ ወንድምና እህቱን ገድሎ የሚፎክረው የሙታን ስብስብ መቼ ነው እይታውን አሳምሮ የወደቀን ደግፎ በማንሳት በሰውነት ባህሪው የሚቆመው ብለን እንጠይቅ። የችግሩ ፈጣሪዎች የሚኖሩባት ህዝቦችን እንጂ ምድሪቱ አይደለችም። ህይወትና ዋና ብቅ ጥልቅ ነው። አሁን በሃገራችን በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የምናየው የአሜሪካ ጥሪ፤ የአውሮፓ ኡኡታ፤ የተባበሩት መንግስታት ጩኽት በወያኔ ሰርጎ ገቦችና ደጋፊዎቻቸው ግፊት የሚደረግ ለመሆኑ ምስክር አያሻም። ጊዜ ግን ሁሉን ይሽራል። የሃገራችን ይበልጡ ችግር እኛው በራሳችን ወይም አዞህ በርታ ተብለን በተላላኪዎች የምናደርሰው ገመና ነው። የኢትዮጵያን የወደፊት እድል ፈንታ እናውቃለን የሚሉ ሁሉ በስኒ ቡና ጠጥተው አተላውን እያዪ ከሚጠነቁሉት ልበ ቢሶች አይሻልም። ሃገሪቷ ገመናዋ ብዙ ነው። ደስታን ለክቶ ለመጎንጨት ያልታደለች ሃገር ናት። ይህ ጉዳይ ደግሞ እኛው ራሳችን የምናዘንበው የመከራ ዶፍ እንጂ ከፈጣሪ የመጣ ነገር አይደለም። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.