የአድዋ ትዝታዬ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

1

በቅድሚያ እንኳን ለ125ኛው የአድዋ ድል በዐል አደረሰን። ዛሬ ሁለት የአድዋ ትዝታዎቼን ላካፍላችሁ ወደድሁ።

 1. ትዝታ አንድ አዲስ አበባ
 2. ትዝታ ሁለት ሎስ አንጀለስ

አዲስ አበባ

ከጥቂት አመታት በፊት በወርኅ የካቲት ሴት ልጃችን ኮሌጅ ከመግባቷ በፊት ሀገሯን ተዘዋውራ በማየት ማንነቷን ይበልጥ እንድታውቅ በማለት ሁለተኛ  ደረጃ ተማሪ እያለች ኢትዮጵያ ሄደን ነበር። እናም አባትና ልጅ የአድዋ ድል በዐል እለት አራዳ ጊዮርጊስ ሄደን የምኒልክ ሐውልት ጋር የመታሰቢያ ፎቶግራፍ ለመነሳት ፈለግን። አራዳ ጊዮርጊስ ስንደርስ ግን በዓል እንደነበረና ሰፈሩም  የክብረ በዓሉ ማእከል እንደሆነ የሚያሳይ ብዙም ምልክት አልነበረም። እለቱ የጊዮርጊስ ቀን ባይሆን እና ቅዳሴም ባይኖር አካባቢው ከዚህም የባሰ ጭር ባለ ነበር። የአርበኞች ማሕበር አባል የነበሩትና ያሳደጉን ባለ ግርማ ሞገሰ የሴት አርበኛ ትዝ አሉኝና እንባዬ አቀረረ። ለዚህ በዐል የነበራቸው ፍቅርና ዝግጅት ትውስ አለኝ። እንኳንም ይህንን ሳያዩ ሞቱ አልኩኝ።

ልጄ በአደባባዩ መካከል ሐውልቱ ባለበት ቅጽር ውስጥ ፎቶ ለመነሳት ፈለገች። ለዚሁ ብላ የሀገር ባሕል ልብስ ለብሳ  ነው የመጣችው። በአደባባዩ ቅጽር የቆመው ጥበቃ አትገቡም ብሎ እንደመከልከል ሲቃጣው ”የልጄ ቅድመ አያቷ ሐውልታቸው እዚህ ለቆመው ሰው የሥራ ባልደረባ ነበሩ“ ስለው በሐዘን ስሜት እሺ ብሎ አስገባት እና ጥቂት ፎቶግራፎች ተነሳች። ሰውየው የአርባ አመት ገደማ እድሜ ያለው ገጠር ቀመስ ሰው ሲሆን ሐውልቱ የምኒልክ ስለመሆኑም ይሁን ምኒልክ ማን ስለመሆናቸው የሚያውቅ አይመስልም። ብቻ ከንግግሬ ዝምድና አላቸው ብሎ በመገመትም ይሁን እንዲህ ተዘጋጅተው በባህል ልብስ ደምቀው መጥተው እንዴት እከለክላቸዋለሁ ብሎ ይሁን እንጃ ብቻ ፈቀደልን። እጅግ ያስገረመን ግን ከዚህ በኋላ የተከሠተው ነገር ነበር።

ፎቶግራፍ ተነስተን ጨርሰን ከአደባባዩ ልንወጣ ስንል የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ወደ እኛ ጠጋ ብለው

“ይቅርታ  ዛሬ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወርን የከተማውን  ወጣቶች ስለ በዐሉ  እየጠየቅን ስለሆነ መልካም ፈቃዳችሁ ከሆነ ለወጣቷ ቃለ መጠይቅ ብናደርግላት” አሉ።

እኔም “ እሷ ፈቃደኛ ከሆነች  በእኔ በኩል ምንም ተቃውሞ የለኝም አልኳቸው” ልጄም ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸችላቸው።

ጋዜጠኛው መጀመሪያ አለባበሷን ቀጥሎም የአማረኛዋን ጥራት በማየት ከኢትዮጵያ ውጭ ተወልዳ ያደገች ናት ብሎ ፈጽሞ አልተጠራጠረም።

ስሟን፣  የትምህርት ደረጃዋን፣  በዐሉ ምንን አስመልክቶ  እንደሆነ ወዘተ ከጠየቃትና ከመለሰችለት በኋላ ፊቱ ላይ የፌዝ ፈገግታ እየታየበት

“የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ምክንያቶች ምን ምን ይመስሉሻል? ” አላት

እሷም ኮስተር ብላ ስትመልስ ጋዜጠኛው ጆሮውን ማመን እንዳቃተው በሚያሳብቅ ሁኔታ ነበር የሚያዳምጣት። እኔም ከሱ ባልተናነሰ ከየት አመጣችው? በሚል መገረም ውስጥ ገብቼ ነበር። ስለአድዋ ይህንን ያክል የምታውቅ አይመስለኝም ነበር። እንዲህ ነበር ያለችው

‘’ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ለማሸነፏ ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች ነበሩ።

አንደኛው የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ የነበራት መሆኑ ነው። በነዚህ ረጅም ዘመናት ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ ልዩነትን ወደ ጎን አድርጎ ተባብሮ መሥራትን ተምረዋል። መንግሥታዊ አስተዳደር እና ዘመቻን ጭምር አሳክቶ የመምራት ረጅም ልምድ አዳብረዋል።

ሁለተኛው ደግሞ ጣይቱና ምኒልክ የጣልያንን ተንኮል ከማወቅና  ስልታዊ ዝግጅት ከማድረግ ጀምሮ ሕዝቡን አስተባብረው ዘመቻውን በስኬት ለመምራት የቻሉ ከፍተኛ የአመራር ብቃት የነበራቸው መሪዎች ስለነበሩ ነው።

ሦስተኛው ሕዝቡ በዚህ ዘመቻ ጦርነታችህን ፍትሐዊ፣ አምላካችንም ከኛ ጋር ነው የሚል የጸና እምነት፣ የምንዘምተውም ከርስታችን ከቤተሰባችን ከባህላችንም  በተጨማሪ እምነታችንን ለማስጠበቅ ነው የሚል የጸና እምነት ይዞ ለዚህም የጊዮርጊስን ታቦት አስቀድሞ በመዝመቱ ነው። ይሄም ሞትን እንዲንቀው አስችሎታል። እነዚህ ይመስሉኛል ዋናዎቹ ምክንያቶች ሌሎች ብዙዎች ቢኖሩም።“

ጋዜጠኛው “እጅግ የምትገርሚ ወጣት ነሽ። ሙሉ ቀን ወጣቶች ስጠይቅ ነው የዋልኩት። የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ጭምር ጠይቂያለሁ። እንዳንቺ አድርጎ የገለጸው የለም። በፍጹም። እጅግ አመሰግናለሁ።“ ብሏት  ወደ እኔም ዞረና ”የምትገርም ልጅ ናት። በሉ ቃለ መጠይቁን በቴሌቪዥን ተከታተሉ።“ ብሎን ሄደ።

ባጋጣሚ ቅዳሴ ገና ስላልወጡ ጊዮርጊስን በውጭ ተሳልመን መንገዱን ስንሻገር ሌላም ጋዜጠኛ ይሄኛው ከቻይና ቴቪ ነኝ ብሎ ቃለ መጠይቅ ላድርግልሽ? አላት። የሀገር ባሕል ልብሱ ይሆን የሳባቸው? እያልኩ ነበር። ይሄኛው ጋዜጠኛ ከፊተኛውም ይበልጥ እየተገረመ ቃለ መጠይቁን ጨረሰና ዛሬውኑ ማታ ይቀርባልና አደራ ተከታተሉ ብሎ ሄደ። የጥያቄዎቹ ዐይነት በሚገርም መልኩ ተመሳሳይ ነበር።

ማታ አንድ ዘመድ ቤት እራት ተጋብዘን ነበርና ለዚሁ ዘመዴ ልጄ ፍንድቅድቅ ብላ ”ዛሬ በቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ ስለተደረገልኝ በቲቪ እታያለሁ። ትለዋለች።

እንዴትና በምን ምክንያት ብሎ ይጠይቃትና ስለ አድዋ መሆኑን ትነግረዋለች።

እና ሌላ አገር ነው ተወልጄ ያደግሁት ስለ አድዋ በዐልም ሆነ ጦርነት የማውቀው ነገር የለም አልሽው? አላት።

ለምን? የማውቀውን አስረዳሁት እንጂ!  እንዲያውም ከሌላ አገር መምጣቴን አልነገርኩትም። አለችው።

ምን ብለሽ ነው ያስረዳሽው? አላት በመገረም መልክ።

ልክ እንደተናገረችው አድርጋ ደገመችለት።

በቃ! በቃ! እንደዚህ ከሆነ የመለስሽለት ያንቺ ቃለ መጠይቅ በቴሌቪዥን መቼም አይተላለፍም አላት።

እኔ ደግሞ ትንሽ እንደመበሳጨት አድርጎኝ፣ ምንም ቢሆን እንዴት የልጅ ተስፋና ጉጉት ላይ በረዶ ትቸልሳለህ? አለሳልሰህ እንኳን ለማስረዳት አትሞክርም? አልኩት።

እሷ ግን ጋሼ ለምን እንደዚህ አልክ? ባንደኛው ጣቢያ ባይተላለፍ በሌላኛው ጣቢያ እንደሚተላለፍ፣ ዛሬ ባያስተላልፉትም ነገ  እንደሚያስተላልፉት እርግጠኛ ነኝ። በደንብ እኮ ነው ያስረዳሁት አለች።

ለምን መሰለሽ የማይተላለፈው? አላትና ቀጠለ። ቃለ መጠይቆቹን የሚያደርጉት ሕዝቡ ስለ በዐሉ ያለውን እውቀት ለማዳበር ሳይሆን ትውልዱን ስለታሪኩ ይሄንን ያክል አደንቁረነዋል ብለው ለመሳለቅ ነው። ጭራሽ አንቺ የዘረዘርሻቸው ምክንያቶች ከሕዝብ  አእምሮ  እንዲፋቁ የሚፈለጉትን ነው። የሦስት ሺህ አመት ታሪክ? የሚኒልክና የጣይቱ አመራር? እምነት? ይሄንን ጨርሶ መስማት አይፈልጉም።  ላስደነግጥሽ ሳይሆን የአድዋን ታሪክ እንዲህ በደንብ እንዳወቅሽው አሁን የሚሠራብንን ታሪክም እንድትረጂው ብዬ ነው አላት።

እውነትም የጎዳና ላይ ቃለ መጠይቆቹ ሲተላለፉ የሷ ባንዱም ጣቢያ ሳይተላለፍ ቀረ። የሚገርመው ደግሞ ዘመዴ እንዳለው በትውልዱ ለመሳለቅ ያስተላለፏቸው ቃለ መጠይቆች የተጠየቁት የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ እና የኮሌጅ ተማሪዎች ስለ አድዋ እጅግ አሳፋሪ መልስ የሰጡባቸውን መርጠው  ይመስላል።

አንዱን ተማሪ የዛሬው በዐል ምንን አስመልክቶ  ይመስልሃል?

እኔ እንጃ በዐል ነው እንዴ?

በዐል ስለሆነማ … ትምህርት ቤት ዝግ ነው።

ትምህርት ቤት ዝግ ነው እንዴ?

ትምህርት ቤት ሄደህ ነበር ዛሬ? እንዴት ዝግ ነው ወይ ብለህ ትጠይቃለህ።

ለነገሩ አልሄድኩም። ትምህርት የለም ነበር በለኛ!

ሌላዋን ተማሪ (11ኛ ክፍል ናት)

የዛሬው በዐል ምንን አስመልክቶ ነው?

እንጃ  በዐል ነው እንዴ?

ትምህርት የለም አይደል? ለምን እንደሌለም አታውቂም?

አይ የመምህራን ስብሰባ ምናምን ስላለ ነበር የመሰለኝ።

ሌላዋ ተማሪ (ይቺም 11 ኛ ክፍል ናት)

የዛሬው በዐል ምንን አስመልክቶ ነው።

እኔ እንጃ! ግን የአድዋ በዐል ሲሉ ሰምቻለሁ።

የአድዋ በዐል ስለምን እንደሚከበር አታውቂም?

እንጃ… ሕወሃት የተመሠረተበት ይሆን?

እንዴት እንደዚህ ልትይ ቻልሽ?

አድዋ ትግራይ ውስጥ መሰለኝ።

ሁለት እህትማማቾች ይጠየቃሉ (12ኛና 2ኛ ክፍል)

ትልቋ ትምህርት ቤት መዘጋቱን እንጂ ምክንያቱን እንደማታውቅ ትናገራለች።

ጋዜጠኛው ተመልካቾችን ይበልጥ ለማሳቅ (ወይም ለማበሳጨት) ትንሿን ልጅ ይጠይቃታል።

ኮልተፍ በሚል ጣፋጭ አንደበት ”አድዋ የሚከበረው በድሮ ጊዜ ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረ ጊዜ አባቶቻችን አሸንፈው ያባረሩበትን ታሪክ ለማስታወስ ነው“ ትላለች።

ታላቅ እህቷ “ምን ትዘባርቂያለሽ? ” ብላ በክንዷ ጎሸም ታደርጋታለች።

ትንሿ እውነቴን እኮ ነው። ትላለች እንደመናደድ ብላ።

ከየት የሰማሽው ወሬ ነው ጣልያን ምንትሴ የሚል?

ትናንትና ሚስ “ነገ ትምህርት አይኖርም። የአድዋ በዐል ነው። ምክንያቱ ደግሞ እንደዚህ እንደዚህ ነው ብላ ክፍል ውስጥ አስተምራናለች።”

ጋዜጠኛውም ተያት ሚሚዬ እውነቷን ነው።  ይላል።

ብዙ እርር ድብን የሚያደርጉ ቃለ መጠይቆች ከተላለፉ በኋላ የዚችን ትንሽ ልጅ መልስ እያስታወስኩ የተስፋ ጭላንጭል እንዳለን መጽናኛ ሆኖኛል። ይሄ ነገር በተከሠተ በጥቂት አመታት ጊዜ ውስጥ ነገር ተለዋውጦ የአድዋ በዐል ድባብ እንደዛሬው ደምቆ አያለሁ የሚል ግምት ግን ፈጽሞ አልነበረኝም።  እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

ይሄ ነገር ረዘመ። ሁለተኛውን ትዝታዬን በሚቀጥለው ባቀርበውስ?

በቸር ይግጠመን።

እስከዚያው ግን

እንኳን ለ125ኛ የአድዋ ድል በዐል በሰላም አደረሳችሁ

እያልኩ ይቺን ግጥም እጋብዛችኋለሁ።

 

እፍ………

በዛሬዪቷ ቀን

ተገኝተናል ወድቀን

አጉል ተዘናግተን!

ግና ተንሰራርተን

ያድዋን ችቦ አብርተን

ጨለማን ድል ነስተን

እንወጣለን እንጂ

በባእዳን ሴራ አንቀርም ተቀብረን

እጅን በእጅ ይዘን ዳግም ተፈቃቅረን

የአበው ልጆች ሆነን እንወጣለን ሰብረን።

አይዞን!

እንወጣለን ሰብረን መቃብር ወጥመዱን

የድል ችቦ አብርተን የሚያሳይ መንገዱን

እሳቱን ለኩሰን

የተዳፈነውን እፍ ብለን አመዱን።

እፍ…………………..

 

 

 

1 Comment

 1. ሲበድሉ ኖረው ተበደልን ይላሉ
  በደልን ቢያውቁ ተበደልን ባላሉ።
  እየገደሉ ያሉ አልገደልንም ይላሉ
  ምን ይሉ ነበር እነሱ ቢገደሉ?
  በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርምና
  ቢያስቡበት ይሻላል የ ፍርድ ጊዜ ቀርቧልና።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.