አደዋ መሥክሪ ! ” ምኒልክ የጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት ነው። ” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አባሻ

በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ

ተፈጠመ ጣሊያንአበሻ እንዳይደርስ

ምኒልክ ተጉዞ የምትጠይቀኝ

ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ

አባተ በመድፉ አምሳውን ሲገድል

ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል

የጎጃም ንጉሥ ግፋ በለው ሲል።

እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ብርሃን

ዳዊቷን ዘርግታ ስምዐኒ ስትል

ተማራኪው ባዙቅ ውሃ፣ውሃ ሲል

ዳኛው ስጠው አለ ሠላሳ በርሜል።

እንደ በላዔ ስብእ እንደመቤታችን

ሲቻለው ይምራል የኛማ ጌታችን

መድፉን መትረየሱን  ባድዋ መሬት ላይ ዘርቶ

እንክርዳዱን ነቅሎ ሥንዴውን ለይቶ

የተዘራውን ውል አጭዶና ወቅቶ

ላንቶኔሊ አሳየው ፍሬውን አምርቶ

እንፋቀር ብሎ ለምኖ መሬት

ንግድ ሊያሰፋበት ሊዘራ አታክልት

እያመጣ ሊሰጥ ግብሩን ለመንግሥት

ለጓዙ ማረፊያ አገር ቢሰጡት

ተጠማኝ ሰንብቶ ሆኖ ባለርስት

ወሰን እየገፋ ጥቂት፣ በጥቂት

እውነት ርስት ሆነው ተቀበረበት

ባሕር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጅ

እንደ ተልባ ሥፍራ ትከዳለች እንጅ

አትረጋምና ያለ ተወላጅ።

የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ

ብልት መቆራረጥ አንድነት ያውቃሉ

አድዋ ከከተማው ሥጋ ቆርጠው ጣሉ

የእስክንድር ፈረስ መቼ ተወለደ

የምኒልክ ፈረስ በክንፎቹ ሄደ

ዳንግላሳ ሲባል እየተጓደደ

የሮማውን ኩራት በእግሩ አሰገደ።

አገርህን ምኒልክ እንዳሁን ፈትሻት

ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት

እጁን ቀምሼ አላውቅ  እያለ ሲያማህ

ቀመሰና እጅህን መጥቶ ጠላትህ

ሮማ ላይ ተሰማ ለጋስ መሆንህ

(ከኢትዮጵያ ታሪክ መፀሐፍ የተወሰደ።)

*************************

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

“ኢትዮጵያ አንድነት የሌላት አገር ነች።ጦርነቱ ገና ሳይዠመር የኢትዮጵያ መሣፍንትና መኳንንት ምኒልክን ከድተው ወደ አውራጃቸው ይመለሳሉ። ወይም ወደኛ ይገባሉ።”

የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒሥትር ክሪስፒና ጠቅላይ የጦር  አዛዥ ባራቲዪሪ ። ይህንን ብለው ነበር።

ኢትዮጵያዊያን አንድነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጥቂት የነቁ ምሁራኖቻችንን በየጎሣቸው በማቦደን የአገሬን ባላገር በዘውግ ማዋቀር በመጀመራቸው ና  ሰው መሆናቸውን እንዲዘነጉ  ለማድረግ እየቀሰቀሱ  ሥለነበር ፣ የእነዚህ ህሊና ቢሶች ራእይ አልባነት ፣በአውራጃዊነት ፣በወንዜ ልጅነት ፣ በቋንቋዊኝነት መታወር ፣ ብዙሃኑኑን በጎሠኝነት እያሥፋፋው ሥለነበርም ፣ የጋራ አገር አለኝ በማለት ፣ ተባብሮ  ፣   ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያዊነት ሊዋጋ አይችልም የሚል      እምነት እነ ክሪስፒ ነበራቸው ና ነበር ይህንን የድፍረት ንግግር በአደባባይ የተናገሩት።

ይሁን እንጂ በለአገሩ ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሉአላዊ አገር እንዳለው ያውቅ ነበርና ፣ አገሩ በባአድ ሥትወረረ ፣ ጎሣዬ ፣ቋንቋዬ ፣ወንዜ አልተነካም በማለት እጁን አጣምሮ አልተቀመጠም። ይልቁንም ባዶ እጁን በጨበጣ ተፋልሞ ወራሪውን ጠላት ከአገሩ ለማሶጣት ፣ ሥንቁን ቋጥሮ ወደ አደዋ ተመመ እንጂ።

 

እኛ ኢትዮጵያዊያን ፣  አደዋ ላይ በጨበጣ ወይም በእጅ በእጅ ውጊያ ነው _ በጦር ትምህርት ቤት ገብቶ የሠለጠነ 20 ሺ የአውሮፖ ጦርን እና ቁጥሩ በውል ያልታወቀውን በሺ የሚቆጠር  ቅጥረኛ ሠራዊቱን ድል ያደረግነው።

በወቅቱ የኢጣሊያንን ጦር የሚመሩ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩና ልምድ ያላቸው ጀነራሎች ነበሩ።

1ኛ / ጀነራል  ባራቲዬሪ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ነበር።

2ኛ/ ጀነራል ዦሴፔ አሪሞንድ የክፍለ ጦር አዛዠ ነበር።

3ኛ/ ጀነራል አማኑኤል ዳቦር ሚዳ የክፍለ ጦር አዛዥ ነበር።

3ኛ / ጀነራል ማቴዎስ አልቤርቶኒ የክፍለ ጦር አዛዥ ነበር።

4ኛ/  ጀነራል ዦሴፔ ኤሌና         የክፍለ ጦር አዛዥ    ነበረ።

 

ኢትዮጵያ የምትተማመንባቸው ሊሞቱላት የተዘጋጁ  በመቶሺ የሚቆጠሩ በበዝታ ዱላና ጎራዴ የያዙ በለአገሮች እና ከጠላት ጋራ ተመሣሥለው የሚሰልሉላት የቁርጥ ቀን ደረሻ ጀግና ልጆች ብቻ እንደነበሯት በታሪክ ተፅፏል።

ለምሳሌ  እሥከ አፍንጫቸው የታጠቁ እብሪተኛ ወራሪዎችን የየዕለት ምሥጢር እየሰለለ ለራሥ መንገሻ የሚያቀብል  ጀግናው አርበኛ ባሻ አውአሎምን ታሪክ ደጋግሞ ይጠቀሳል።

ለአደዋ ድል የጎላ አሥተዋፆ ያደረገው ባሻ አውሎም  የኢጣሊያ ጦር  ምሥጢርን  ለራሥ መንገሻ ያደርሳል። እራሥ መንገሻም ለንጉሱ ያደርሳሉ።   የሥንቅ ማለቀን እና ሥንቅ ፍለጋ ጦሩ መበታተኑንን የካቲትት 22   በባሻ  አውሎም በኩል ለባራቲዬሪ ሐሰተኛው ሪፖርት በባሻ አውአሎም በኩል እንዲደርስ ተደርጓል። በእዚህ ሃሰተኛ ሪፖርት በመገፋፋትም  ማታውኑም በበር ጠባቂው በራሥ መንገሻ ጦር ላይ ባራቲዬሪ ተኩሥ እንዲከፈት በማደረግ የመጀመሪያዋን የጦርነት ጥይት ተኩሷል።  ይህም አድራጎቱ በአድዋ ሸንተረር የሰፈረውን የምኒልክ ጦር አንቅቷል።

ጦርነቱ የተጀመረው ኢጣሊያኖችን በሐሰት ከምሽጋቸው እንዲወጡ በማድረግ ነው። ( በምሽግ ጦርነት __ በመቀሌው ውጊያ ሥንት ጀገና ኢትዮጵያዊ በከንቱ ማለቁን ኢትዮጵያዊያኑ የጦር እሥትራቴጅሥቶች ተገንዝበው ነበር።)

እናም ሐሰተኛ ወሬ በሰፊው በማሶራት ወራሪው የኢጣሊያ ጦር ከምሽጉ እንዲወጣ አድርገውታል።

ከሐሰተኛ ወሬው ጥቂቱ ፦

1_የኢትዮጵያ ወታደር ሥንቅ አልቆበት ለዘረፋ በየአገሩ ተበታትኖል።

2_ከፊሉ የኢትዮጵያ ሠራዊትም በረሃብ ከምሞት ብሎ ወደ መጣበት የትውልድ አካባቢው ጉዞ ጀምሯል።

3_ እነራሥ እገሌ ንጉሡን ከድተዋል። የታወቁት የጦር ሹሞችም ታመዋል።አራሥ እገሌም ሟቷል

4_ንጉሡም በጠና ታመው ከመኝታቸው መነሳት አቅቷቸዋል ። በምሥጢር ተይዞ ነው እንጂ ጦሩ ተፈትቷል።…

በማለት  ሐሰተኛ ወሬ ከማሶራታቸውም በአሻገር ፣ ጦርነቱን ከጀመረክ ከአንተ ጎን እንቆማለን የሚል መልዕክትም ፣ከነራስ ሚካኤል ፣ከንጉሥ ተ/ኃይማኖት ፣ ከነራሥ መኮንን የተፃፈ በማለት በሐሰት ለኢጣሊያን ጦር አዛዦች  ለኢትዮጵያ የወገኑ ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያ ሰላዮች ያቀርቡ ነበር።

ይህም ሃሰተኛ ወሬ ለኢጣሊያ ጦር መሪ በታማኝ ምሥጥር አቀባዮች አማካኝነት በመድረሱ ፣ ጣሊያኖች ከምሽግ ወጥተው የመዋጋት ድፍረት እንዲኖራቸው ማድረጉን ታሪክ ዘግቦታል።

ሌላው አሳማኙ እውነት ግን ለአምሥት ወር የመሸገው የኢጣሊያን ጦር የሥንቅ እጥረት ሥላየለበት ፣ በሥንቅ እጥረት ከማዋረዱ በፊት ጦርነቱን ለመጀመር መወሰኑ ነው። (እርግጥ ነው፣ኢትዮጵያኑም የሥንቅ ችግር እንደነበረባቸው አይካድም ።)

ጦርነቱን ለማካሄድ የጦሩ መሪ ባራቲዬሪ ሲወሥን በድንገት የደረሰውን ሃሰተኛ  መረጃ መሠረት አድርጎ ነው ቢባልም ፣ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ  ለጦርነት ድንገት  የተነሳበት ተጨማሪ ምክንያት      የሥንቅ ማለቅ እና እሱን ተከትሎ የሚመጣው የውርደት ሽንፈት ነው።ከዚህ በተጨማሪም ይህ የገበሬ ጦር በባዶ እጁ እኛን ሊያሸንፈን አይችልም ፣ በቃት ፣ ችሎታ ና እውቀትም ስለሌለው በቀላሉ እንደመስሰዋለን የሚል የነጭ እብሪት ጦርነቱን በልበ ሙሉነት ባልታቀደ ጊዜ እንዲጀምሩ ገፋፍቶታል።

እርግጥ ወሬዎችቹን እና እነዚህን ምክንያቶች ተተርሰው  የካቲት 23/1888 እሁድ ጎህ ሲቀድ ጣሊያኖች ጦርነቱን መጀመራቸው   የኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ቤተክርሥቲያን የሚሄድበት ሰዓት በመሆኑ   ፣ ነጉሱ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በማድረግ ፣ ንጉሱን ከገደልን ጦሩ  ይሸሻል። በቀለላሉም ድሉ የእኛ ይሆናል ብለው አሥበው ነው ለማለትም ያሥደፍራል።ይህንን እቅድ በማውጣት  እርግጠኛ ሆኖው ጦርነቱን ቢጀምሩም ፣ የንጉሱን ድንኳን እና ማደሪያ ግን በውል የሚያውቅበት አንዳችም ምልክት ባለመኖሩና እሳቸውም የጦር ልብሥ ለብሰው ከሠራዊቱ ጋር በመቀላቀላቸው ለጠላት በግላጭ ለመታየት ባለመቻላቸው እቅዱ አልተሳካም።…

የጋራ ሥም ያላቸው ጀግና ፣ አንበሳ ፣ነበር በመባል የሚሞካሹት  ጀግኖቹ የኢትዮጵያና የመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆኑት ድንገት ጥቃት የሰነዘረውን በእጅ ለእጅ ጨበጣ ገጥመው ፣ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንንቀው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ፣ ወራሪውን የአውሮፖ ነጭ ሠራዊት ድል አደረጉት።

እነዚህ በደማቸው ፣ በመሰዋትነታቸው ዛሬ በኩራት እንድንራመድ ያደረጉን ወላጆቻችን ፣ ባለአገሮቹ ፣ አገር አልባ ሊያደርጉን የሚጥሩትን ባንዳዎች የሚያጠፉሉን መድሃኒቶች ናቸው።  ) ከምር ከተጠቀምንባቸው።በመሰዋትነታቸው ካመንን ።)

ጀግኖቹ ፣ ኩሩዎቹ ፣ ለኢትዮጵያ ለመሞት የተሽቀዳደሙት ፣ “ሂድ እኔን አታንሳኝ ቁሥሌንም አታክም።ለአገሬ በደሥታ እሞታለሁ ። የአገሬን ጠላት ግን እንዳያመልጥህ ፤  አባረህ በለው ! በለው ! በለው ! …” እያሉ ወኔውን መቶ እጥፍ በማድረግ ለአገራችን አንፀባራቂ ድል ታላቅ አሥተዋፆ አድርገው ህይወታቸውን በደሥታ ጥተዋል።

” ነጉሰ ነገሥቱ ሳይመለሱ የምን ማረፍ ነው። ምርኮህን እዚህ አሥቀምጠህ ጠላትን እያሳደድክ በለው ! በለው ! በለው ! …”በማለት ሲያበረታቱና ቁሥለኛውን ሲያክሙ የነበሩት እናቶቻችን ዘላለማዊ ክብር የሚገባቸው ናቸው። ጀግኖቹ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ወላጆች  የአገርን አፈር በልተው ፣የአገርን ውሃ ጠጥተው ያማረባቸው ሰዎች እንደሆኑ የሚያውቁ ኩሩ ህዝቦች እንደነበሩ ይህ  ትውልድ በቅጡ መገንዘብ አለበት።

ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን   ለአገራቸው ክብር ሲሉ አንገታቸውን ለሰይፍ ግንባራቸውን ለጥይት በመሥጠት በመሰዋትነት ኢትዮጵያ የምትባል አገርን አሥረክበውናል።

አባቶቻችን  ዘራቸውን በመላ ኢትዮጵያ  ያበዙት  ፈጣሪ የለገሳቸውን ይህቺን ድንቅ ምድር ፣ እሥከዛሬ ጠብቀውልን ያቋዩን ፣ የዚችን የድንቅ ፣ ውብ ለምና እፁብ ድንቅ የሆነች አገር ባለቤት ያደረጉን ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው ነው። ቁር ፣ ሐሩር ፣ እና ማንኛውንም የተፈጥሮ ችግር ተቋቁመው ነው።ከዚህ ሁሉ በላይ በወቅቱ ከነበሩት መንግሥታት ቀለብ ሳይጠይቁ ፣ ያለደሞዝ ለአገራቸው ክብር ሲሉ ለትዳር አጋሮቻቸው ፣ለሽማግሌ ወላጆቻቸው  ና ፣ለህፃናቱ ና ለታዳጊዎቹ  ውርደትን አላወርስም  በማለት ነው ።

 

የዛሬ 125 ዓመት  በአደዋ   ጎህ ሲቀድ ጀምሮ ለሥድሥት ሰዓታት ፣በሸንተረሩ ፣በሜዳውና በጋራው   ዙሪያ በተደረገው ፍልሚያ ድሉ የኢትዮጵያዊያን የሆነው 5 ሺ ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ተሰውተው ነው። 40ሺዎች  ቆሰለው ነው ።

በኢጣሊያ በኩል     … ጎህ ሲቀድ ጀምረው  እሥከ እኩለ ቀን  የባራቴሬ ሁለት ክፍለ  ጦርን  እምሽክ  ( 7ሺ ጦር ) ያደረጉት በጦር ፣በጎራዴ ፣በዱላ ና በጥቂት ናሥማሥርና ውጅግራ ነው። (…)

ኢትዮጵያ የጨዋና የኩሩ ህዝብ ባለቤት መሆኖንም በአድዋ ጦርነት 3000 የኢጣሊያ ምርኮኞችና በሺ የሚቆጠሩ ቁሥለኞችን  በሥርዓት ይዛ ፣ ለኢጣሊያ በመመለስ አረጋግጣለች ።…

ከድሉ በኋላ መላው ጥቁር ህዝብ አንገቱን ቀና አደረገ።  ለክብሩና ለነፃነቱም ተነሳሳ። በየአህጉሩም የጥቁሮች አልገዛም ባይነት እያየለ መጣ።

ናሙዳ አዝኪዊን የመሰለ   ጥቁር ታጋይ የናጄሪያ ምድር ፈጠረ። ኳሚ ኑኩሩሐማንን ጋና፣ኪኒያም ጆሞ ኬኒያታን  ያፈራችው ከዚህ የጥቁር ህዝብ አንፀባራቂ ድል በኋላ ነው።

የዌሥት ኢዲሱ ፖለሞይም፣፣ጃማይካው ማርክስ ጋርቬ ና አሜሪካዊውው  ማርቲን ሎተርም ለትግል የሚያነሳሳ ውሥጣዊ ጉልበት ያገኙት ኢትዮጵያዊያን ነጮቹን ማበርከካቸውን በማየታቸው ነው። የኢትዮጵያውያኑ የአደዋ ድል ፣ የጥቁር ህዝብ ትግል መሣሪያ ሆኗል። (…)

 

የጣሊያን መንግሥት በተጭበረበረው የውጫሌ  ውል ፦

“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ  መንግሥታት ጋር ለሚዋዋሉት ጉዳይ ሁሉ በግርማዊ የኢጣሊያን ንጉሠ ነገሥት አማካይነት ለመጠቀም ተስማምተዋል። ” በማለት የውጫሌ ውል ካሉት 20 አንቀፆች በ17 ኛው አንቀፅ ላይ ፣በአማርኛው “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ፍቃድ ከሆነ “የሚል አሥገብቶ  በኢጣሊያንኛው ሳያሥገባ ከላይ እንደተቀመጠው አጭበርብሮ የፃፈው ፣ ምንም እንኳ ለዚህ ሁሉ ሰው እልቂት ቢያበቃም ፣የአደዋ ድል ፣ የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት ፣ አረቆ አሳቢነት ፣ለሰው ያላቸውን ክብር ፣ፍቅር ፣ ሰብአዊነትን እና ጥቁሮች ሁሉ ከነጮች እኩል እንደሆኑ ያሥመሰከሩበት በመሆኑ ለዘላለም በጥቁር ህዝቦች ልብ ውሥጥ ሲከበርና ሲወደስ ይኖራል።

ሚኒሊክ የዛሬ 125 ዓመት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው  የሚያሥተዳድሩትን ህዝብ እየመሩ ፣ በለአገሩን የታላቅ አገር ህዝብ ባለቤት እንደሆነ  አረጋግጠው ና የዓለምን ጥቁር ህዝብ በነጭ ላይ በተገናፀፉት ድል ከጫፍ፣ ጫፍ አነቃንቀዋል ።

ከድሉ 12 ቀን በኋላ ማያዚያ 8 ቀን ነው፣አዲስ አበባ የተመለሱት። በታላቅ የድል አድራጊነት ግርማ ታጅበው። ህዝቡም በሆታ ና በእልልታ ተቀብሏቸዋል። ግዳይ ሲጣልና ሲፎከርም ከላይ መግቢያ ያደረኩት ግጥም ፣ በተለያዩ ዜማ በህዝብ ተዜመ። ጀግኖች ተወደሱ ። ጀግኖች ተሞገሱ።  ዛሬሥ ?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.