የእርስ በርስ ጦርነት፣ መንሥዔው፣ መዘዙና መፍትሔው – ባይሳ ዋቅ-ወያ

1

የእርስ በርስ ጦርነት፣

መንሥዔው፣ መዘዙና መፍትሔው

(ከሌሎች አገራት የርስ በርስ ግጭቶች የምንማረው ካለ)

 

wakwoya2016@gmail.com

ስቶክሆልም፣ ጥር 2021 ዓ/ም

****

መግቢያ

በአገራችን በተለያዩ ክፍላት እየተከሰቱ ባሉ የርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት፣ የዜጎች መገደልና ያለ አግባብ መፈናቀል ጉዳይ እኔንም እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ እጅግ በጣም አሳስቦኝ፣ ሁኔታውን በጥልቀት ከተረዳሁ በኋላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደተለመደው ለውይይት መነሻ ይረዳሉ ብዬ የማስባቸውን  መጣጥፎች ለአንባቢዎች ለማቅረብ ሳስብ ነበር። ጊዜ ወስጄ የችግሮቹን ምንጮች በውል አውቅ ይሆናል የሚለው ግምቴን ግን ብዙም አልረዳኝም። እንዲያውም የባሰውን ያወሳሰበብኝ መሰለኝ። አንድ ቦታ ላይ ይህን ያህል የዚህ ብሔር አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ ብሎ በአንድ ሚድያ ሲነገረን፣ ሌላኛው ሚዲያ ደግሞ፣ የለም ሟቾቹ የሌላ ማህበሰረብ አባላት ናቸው ይለናል። እውነቱን ለማወቅ የሚቻለው በማፈናቀሉና በመግደል ድርጊቱ የተጠረጠሩ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ሲፈረድባቸው ብናይ ወይም ብንሰማ፣ ወይም ደግሞ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ባለ ድርሻ አካላት የምርመራውን ሂደት/ውጤት ግልጽ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ሲያሳውቁ ነበረ። ግን እስከ ዛሬ ወንጀለኞቹም ሲያዙ፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ወይም ሲፈረድባቸው የምናይበት ግልጽ (transparent) የሆነ የፍርድ ቤት ሂደት ስለሌለ፣ ስለ ወንጀል ፈጻሚዎችና፣ ሰለባዎቹ እውኔታ የምናውቀው በሙሉ ግምታዊ ነው ማለት ይቻላል። ዶ/ር ዓቢይ ላይ ማን ቦምብ እንደ ወረወረ፣ እነ አምባቸውንና ጄኔራል ፀዓረን ማን እንደገደለ፣ የደምቢ ዶሎ ሴት ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎችን ማን እንዳገታቸው እና ዛሬ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳን ማን እንደ ገደለው፣ በመተከል እየተካሄደ ያለው ጭፍጨፋን ማን እያካሄደ እንዳለ፣ የጉራ ፈርዳን ጭፍጨፋ ማን እንዳቀናበበረ፣ ለጉሊሶው እልቂት ተጠያቂ ማን እንደሆነ፣ ቁጥራቸው ብዙ የሆነና በኦነግ ደጋፊነት ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ባልታወቁ አካላት ከፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ሲገደሉ ለምንና ማን እንደ ገደላቸው የማይታወቅበት፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ዳኛው ሲፈርድ ፖሊስ ደግሞ አልለቃቸውም ብሎ የዳኝነትን የበላይነት ሲገዳደር፣ በዋስ የተለቀቁት ደግሞ በቀጠሮው ቀን ወደ ፍርድ ቤት እየሄዱ እያሉ በጠራራ ጸሃይ “ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት” መንገድ ላይ ተጠልፈው መድረሻቸው ሲጠፋ፣ እና ሌሎችም ሌሎችም ብዙ ብዙ ሕገ ወጥ ተግባሮች የሚፈጸሙበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። ሁሉም ነገር ግልጽነት የሌለው፣ መንግሥትም ሆነ የፖሊቲካ ድርጅቶች ሁሉንም ነገር “በምስጢር የሚይይዙበት”፣ ነገር በስሎ ያረረበት እንጂ አንዳችም የፖሊቲካ ሲቪሊቲ የሌለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ይህ ሁሉ ላዬ ላይ ተጭኖብኝ ነው ሃሳቤን ሰብሰብ አድርጌ ለብዙ ጊዜ “የርስ በርስ ግጭት” በሚል ርዕስ ልጽፍ ያሰብኩትን መጣጥፍ በፈለግሁበት ጊዜ ላካፍላችሁ ያልቻልኩት።

 

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በብዙ አገራት የተከሰቱትን የርስ በርስ ግጭቶች በተለያዩ ደረጃዎች ከቅርብ ሆኜ ያስተዋልኳቸው ስለሆነ፣ ስለ የርስ በርስ ግጭት ምንነት አፌን ሞልቼ ለመናገር እችላለሁ ባይ ነኝ። ዛሬ ዛሬ አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶችና እንዲሁም አንዳንድ የኃይማኖትና የፖሊቲካ ጽንፈኞች ለግል ፖሊቲካ ዓላማቸው ስኬት ብቻ ሕዝባችንን ለእርስ በርስ ግጭት ዓመጽ ሲቀሰቅሱ ሳይ፣ ያየኋቸው የርስ በርስ ግጭቶች ምንኛ አሰቃቂ እንደነበሩ በዓይነ ኅሊናዬ ይታዩኝና፣ እነዚህን ወገኖቼን እንዴት ባስረዳ ነው እየተጓዙበት ያለው ጎዳና መጨረሻው ጥፋት ብቻ እንደሆነ ተናግሬ የማሳምናቸው እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት እገጥማለሁ። አንድ ቀን ግን ሁላችን ወደ ቀልባችን ተመልሰን፣ እውነትም እየተጓዝንበት ያለው ጎዳና ወደ የጋራ ጥፋት እንጂ ወደ አገራዊ ልማት እንደማያመራን ተገንዝበን ሰከን ባለ መንፈስ ልንወያይበት የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ተስፋ ቢጤም ሰንቄአለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን እንደው ለውይይት መነሻ ይሆነን ዘንድ፣ ስለ የርስ በርስ ጦርነቶች መንሥዔና፣ ሊሆኑ ይችላሉ ስለምላቸው መፍትሔዎች፣ ካየኋቸውና ካስተዋልኳቸው ተነስቼ የግሌን ሃሳብ ላካፍላችሁ። ለማንኛውም ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በግርድፉም ቢሆን ማንሳቱና አንዳንድ ብዥታዎችን ከወዲሁ መግፈፉ አስፈላጊ ስለመሰለኝ በሱ ልጀምር።

 

የዛሬው ያገራችን ሁኔታና ወቅታዊ ችግሮቻችን

 

ዛሬ አገራችን ያለችበት የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ እጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ከኸያ ሰባት ዓመት የወያኔ መራሹ ግፈኛ አገዛዝ መገርሰስን ተከትሎ የመጣውን ለውጥ እልል ብለን እንዳልተቀበልን፣ ዛሬ በየክልሎችና በክልሎች መካከል እንዲሁም በተለያዩ ብሔሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶችና መጠነ ሰፊ የሆነ በአገራችንም ዘመናዊ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የመገዳደልና መፈናቀል ክስተቶችን ስናጤን፣ የአገሪቷ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን እያልን በየቤታችን ከማጉረምረም አልፈን በአውሮፓና አሜሪካ አደባባዮችም እየወጣን ቅሬታችንን እየገለጽን ነው። አሳዛኙ ነገር ግን፣ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አብዛኛው የተማረው የማኅበረሰብ አባሎቻችን፣ ሂደቱ አደገኛ መሆኑን ቢገነዘቡም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶቹን ለመብረድ በሚደረገው በእንቅስቃሴው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ ራሳቸውን ሲያገልሉ ይስተዋላላሉ። አገር በለውጥ ማዕበል ወይም በግጭቶች ስትታመስ የምሁራን ዝምታ ግን ምን ያህል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ከኢራን አንዳችም ትምሕርት የቀሰምን አይመስልም። ለማንኛውም እስቲ ዛሬ ስለምንገኝበት ሁኔታ አንዳንዶቹን ልጥቀስ፣

) በተለያዩ ምክንያቶች ለኸያ ሰባት ዓመታት ላይ ላዩን ተከድኖ በውስጥ ግን ሲፈላ የነበረው የሕዝቦች እርካታ ማጣት ገና የለውጡ ቡድን ሥልጣን ላይ እንደወጣ፣ በተለያዩ ክልሎች በግልጽ መታየት ጀመረ። በፌዴራል ሥርዓቱ ራስን በራስ የማስተዳደር በሚለው መሪህ መሠረት በተፈጠሩት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ክልላቸውን እንደ አንድ ነጻ አገር እና የክልል ድንበራቸውን እንድ አንድ አገር ዳር ድንበር በመቁጠር፣ ለዘመናት ሌላው እንኳ ቢቀር በመልካም ጎረቤትነት አብሮ ይኖር የነበረውን የሌላ ብሔር ተወላጅን አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ማፈናቀልና መግደል ተጀመረ። እነዚህ ተፈናቃዮች አብዛኞቻቸው እስከ ዛሬም ድረስ ወደ ቄያቸው ተመልሰው ሰላማዊና የተረጋጋ ኑሮ መምራት አልቻሉም።

 

) የሕዝባችን ቁጥር መጨመርና በዚያውም ልክ ደግሞ ተምሮ ሥራ ያጣው ትውልድ ብዛት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በተለያዩ ኃይማኖታዊና ማሕበረሰባዊ ጫናዎች ምክንያት መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን በኃይል እየጨመረ ያለውን የአገራችንን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ ያላቸውን አጄንዳ እስከ ዛሬ ድረስ ለሕዝብ ግልጽ አላደረጉም። ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ 65% ማለትም ወደ 72 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝባችን ዕድሜው ከ24 ዓመት በታች ነው። ከሕዝባችን 4% ብቻ ነው ከ55 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት ብሎ መደምደም ይችላል። በዚያው ልክ፣ ዛሬ ወደ አሥራ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተምረው ሥራ ያጡ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከመናገሻ ከተማችን እስከ ትናናሽ መንደሮች ድረስ መንገድ ላይ ተኮልኩለዋል። የዚህን ያሕል ወጣት ትውልድ ሥራ አጥ የሚያስተናግድ አገር ደግሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ከባድ ያለመረጋጋትን እያመቻቸ ነው። መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ድርጅቶች፣ ለዓላማቸው ማሳኪያ በዋናነት የሚጠቀሙትም ይህንን፣ ጡንቻን እንጂ ሃብትን፣ ወይም ብሩሕ ተስፋ የሌለውን ሥራ አጥ የማህበረሰቡን አካል ነው።

 

) የኢትዮጵያ “የሃገረ ብሔር” ምሥረታ አለመሳካት ዛሬ ለሚስተዋሉት የርስ ብርስ ግጭቶች ምክንያቶች ዋነኛው ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም። ከመቶ አምሳ ዓመት በፊት ዘመናዊዋን ኢትዮጵያን ለመመሥረት ፕሮግራሙ ሲጀመር የነበሩ ሰማኒያ አምስት ብሔሮች/ሕዝቦች ዛሬም የየራሳቸውን ቋንቋና ባሕል እንደ ጠበቁ፣ አንዳቸውም በአንዳቸው ውስጥ ሳይቀልጡ፣ ውሃና ዘይት ሆነው ጎን ለጎን እየኖሩ ነው። ከ85ቱ ብሔሮች መካከል ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላቸው ብሔሮች 9 ብቻ ሲሆኑ[1]  21ዱ  ደግሞ ከአሥር ሺህ (10,000) በታች ሕዝብ ያላቸው ናቸው።[2] ይህንን ያክል አናሳ ሕዝብ ያለው ብሔር በምን ተዓምር በሌሎች ኃያላን ብሔሮች ከመዋጥ (assimilation) ተርፎ እስከ ዛሬ ድረስ የራሱን ባሕልና ቋንቋ ይዞ እንደ ቆየ ለማወቅ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ለዚያ ሁሉ ዘመን መዋጥን ተቋቁመው (ወይም እንዲዋጡ ስላልተፈለጉ) ከቆዩ በኋላ ዛሬ ግን “ማንነታቸው ታውቆላቸው” በዞንና በአውራጃ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ፣ “ማንነታችሁን ተውና ለኢትዮጵያ አንድነት ቅድሚያ ስጡ” ቢባሉ ምን ያሕል ፈቃደኛ እንደሆኑ መገመት ያዳግታል።

 

) ሌላው ትልቁ ያገራችን ችግር ደግሞ ሳይታሰብ የተፈጠረ የትውልድ ክፍተት (Generation gap) ይመስለኛል። ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች የመኢሶንና የኢሕአፓ አባላት፣ እንኳን ተራማጅ ዓላማቸውን ከግቡ ለማድረስ ይቅርና ከወጣቱ ትውልድ ጋር የጸና ግንኙነት ሳይፈጥሩ ስለተሠዉ፣ ከደርግ መንግሥት በኋላ ለመጣው ትውልድ የረባ የትግል ቅርስ ሊያወርሱ አልቻሉም። ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ፣ የሁለቱ ድርጅቶች አመራር አባላት የተማሩት፣ እና አብዛኛውን የዓዋቂ ዕድሜያቸውን ያሳለፉት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈነባቸው አገራት ቢሆንም  ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ግን የአስተሳሰብ ልዩነቶቻቸውን በዲሞክራሲያዊ ውይይት ሳይሆን በነፍጥ ለመፍታት መወሰናቸው ላሁኑ ትውልድ መጥፎ አርዓያ ሆነው አልፈዋል።  ከ85% በላይ የሆነው የዛሬው ትውልድ ከኢሕአዴግ ሌላ መንግሥት ስለማያውቅ የትግል አልፋ ኦሜጋ አድርጎ የሚያየው ወያኔን ለመጣል ያደረገውን ትግል ብቻ እንጂ ስለ ፊውዳሉ ሥርዓት አስከፊነት፣ የመሬት ላራሹ ዓዋጅ አስፈላጊነት፣ የነበረው የብሔር ጭቆና እና የመሳሰሉ “የዚያ ትውልድ” በወቅቱ መሠረታዊ የሆኑ ፖሊቲካዊና ማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች እምብዛም ትርጉም አይሠጣቸውም። የችግሮቹን ይዘት ሳይሆን፣ የችግሮቹን መኖር እንኳ በቅጡ የሚረዱት አይመስለኝም።

 

) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ቀልጠው አንድ ወጥ አገር ብሔር ለመመሥረት ባይችሉም ከጊዜ ብዛት ቀስ በቀስ አብሮነትን በተወሰነ ደረጃ እየተለማመዱ መጥተው ጥሩ ጎረቤትማማችነትን ማጣጣም እንደ ጀመሩ የወያኔ ኸያ ሰባት ዓመታት አገዛዝ ኢትዮጵያዊነትን አመንምኖ የብሄር ማንነትን በማግዘፉ፣ ዛሬ የአብዛኛው ብሔር አክቲቪስት ወይም የፖሊቲካ ድርጅት ተቀዳሚ የቤት ሥራ የማንነት ጥያቄ እንጂ ኢትዮጵያዊነት አይመስለኝም። ከመቶ በላይ ከሚሆኑ የአገሪቱ ፖሊቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ብሔር ተኮር መሆናቸው በራሱ የትግል ጉዞን ገና “ሀ” ብለን እየጀመርን መሆኑን ይጠቁማል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም።

) የምሑሩ በኅትመትና በሌሎች የማሕበራዊ ሚዲያ ልፈፋዎች ጫና ሥር ውሎ፣ የአገሪቷን ሕዝቦች አንድ ላይ በሚያመጣቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደ መወያየት፣ አንደኛውን ቡድን አወድሶ ሌላውን መኮነኑ ደግሞ ሌላው ችግራችን ነው። በኔ ግምት ይህ የተሳሳተና ሕዝቦችን ለመከፋፈልና ብሎም ለማጋጨት ካልሆነ በስተቀር ለሕዝቦች አብሮነት አንዳችም ፋይዳ የለውም። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ብዙ “የዚያ ትውልድ” አባል የሆንን ምሑራን፣ ከዚያ ሁሉ ዓለም አቀፋዊና ፍትሓዊ  ራዕያችን ወርደንና የጽንፈኛ ብሔርተኞችን ቡድን በመቀላቀል የነሱን ብሔርተኛ ዓላማ ደግፈን መታየታችን ነው።

 

) የብዙዎቹ አክቲቪስቶች እና የፖሊቲካ ድርጅቶች ብሎም የጽንፈኛው ቡድን ዋናው ዓላማ፣ ዛሬ እየተከሰቱ ላሉት ችግሮች መንስዔያቸውን በጥልቅ መርምሮ መፍትሔ መፈለግ ሳይሆን፣ ችግሮቹ ባስከተሏቸው ምልክቶች ላይ ብቻ በመረባረባቸው፣ የችግሩ መፍትሔ ፈላጊ ሳይሆን የችግሩ አካል መሆናቸው በግልጽ እየታየ ነው። እንደው አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ በደቡብና ምሥራቅ ኦሮሚያ ውስጥ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ብቻ ከሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮችና (ፕሮቴስታንቶች) እና ተቋማት ተለይተው በተደጋጋሚ ለግጭቶች ሰለባ የሆኑበትን መሠረታዊ ችግር አንስቶ በመወያየት እልባት እንደ መፈለግ ዝም ብሎ ጥቃቱ በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ ነው ብሎ መደምደሙ ይቀልላቸዋል።

 

የእርስ በርስ ጦርነት

 

የእርስ በርስ ጦርነት ከጦርነቶች ሁሉ እጅግ በጣም አስከፊው ነው። የውጪ ወራሪ ሲመጣ ለወረረው አገር ውስጥ አዋቂ ባለመሆኑ ከተወረረው ሕዝብ መካከል ባንዳዎችን ፈልጎ እስኪያገኝ ድረስ የሚያደርሰው ጥፋት ያን ያህልም አስከፊ አይሆንም። ባንዳዎቹም እስኪገኙ ደግሞ ጊዜ ስለሚፈጅና ወራሪውም ጓዳ ቀዳዳውን ስለማያውቅ፣ ወራሪው ኃይል በሕዝቡ ላይ ቅጽበታዊ ጥቃት ሊያደርስ አይችልም። የእርስ በርስ ጦርነት ግን አንዴ ከተጀመረ፣ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የርስ በርስን ጓዳ፣ መውጫና መግቢያ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለመጠፋፋት ጊዜም አይፈጅባቸውም። የመንገዶችን ጥበትና ስፋት፣ የቤቶችን መስኮቶችና በሮች እያንዳንዱን ማጀትና ጓሮ ሳይቀር በደንብ ስለሚያውቁት ለሰላማዊው ሕዝብ በጊዜ የመሸሸ ዕድል አይሰጡትም። አንዴ ተክሱ ተጀምሮ፣ ዘመድ ወይም ጓደኛ ከቆሰለ ወይም ከተገደለ በኋላ ደግሞ “የተኳሹ ወገን” በሙሉ እንደ ጠላት ብቻ ሳይሆን እንደ እንስሳ ስለሚቆጠር፣ በዚህኛው ወገን ያለው ተፋላሚ “እንስሶቹን” ገድሎ ካልጨረሰ ዕረፍት አይኖረውም። መጨረሻው ሁለቱም ወገን መልሰው እንዳያገግሙ ሆነው ይቆሳሰላሉ። የሚገደለው ሕዝብ ቁጥር፣ የሚፈናቀለው፣ ተገድሎ የትም ወድቆ የሚቀረው፣ የሚጠፋው ንብረት እና በአጠቃላይም በሕዝቦች ላይ የሚያደርሰው የአካላዊና አዕምሮያዊ ጉድለት ማንም ከሚገምተው በላይ ስለሆነ፣ መገዳደሉ ካበቃ በኋላ እንኳ፣ ማኅበረሰቡ ተመልሶ አብሮ በሰላም ለመኖር ቢያንስ ቢያንስ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ይጠይቃል። ያውም አብሮነትን ለማስፈን ሓቀኛ እንቅስቃሴ ከተደረገ!

 

ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለእንደዚህ ዓይነት የርስ በርስ ግጭት የሚያደርሰው ምንድነው? ድሕነት? ድንቁርና? ስግብግብነት? የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት? ወይስ ሌላ የማናውቀው ነገር? የሆነ ቁርጥ ያለ ሂሳባዊ ፎርሙላ ዓይነት መልስ የለኝም። ከነዚህ የአንዱ ወይም የሁሉም መኖር እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይቻላል። ካስተዋልኳቸውና መጠነኛ ጥናትም ካደረግሁ በኋላ የደረስኩበት ድምዳሜ ግን፣ ለርስ በርስ ግጭት መንሥዔ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ የገመትኳቸውን እና ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ ምክንያቶች እንደሚከተለው ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። ድምዳሜዬ ግን ግላዊ እንደሆነ ከወዲሁ ይታወቅልኝ።

የእርስ በርስ ጦርነት መንሥዔዎች

 

ስለ እርስ በርስ ጦርነት ያደረገሁት ሳይንሳዊ ጥናት የለም። የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያነቴም ወይም የግጭቶች መቅረፍያ (Conflict management) ኤክስፔርት መሆኔም ይህንን ማህበረሰባዊ ችግር ሙሉ በሙሉ እንድረዳ አላደረገኝም። በአንጻሩ ግን በአጋጣሚ የሥራ ተልዕኮ ምክንያት ከላይ በጠቀስኳቸው የግጭቶች ቀጠና ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በሠራሁባቸው ዓመታት፣ የግጭቱ ሰለባ ከሆኑት የማኅበረሰቡ አባላት ማለትም፣ ሴቶች፣ ሕጻናትና አዛውንት፣ እንዲሁም ከአክቲቪስቶችና ከፖሊቲከኞች ጋር በመገናኘትና በመወያየት፣ አልፎ ተርፎም ሁኔታዎችን ከቅርብ ሆኜ እከታተል ስለነበር፣ በትምሕርት ቤት ካገኘሁት የቲኦሪ ዕውቀት በላይ ስለ ችግሩ የበለጠ አረዳድ አግኝቻለሁ ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህም ነው፣ የዛሬውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ስገመግም፣ እነዚህን የዓመታት ተሞክሬዬን በቀላሉ ካገራችን ሁኔታ ጋር አዛምጄ፣ ከዚህ በታች የማነሳቸው እውኔታዎችና ካገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሳስተያይ፣ እጅግ በጣም ተመሳሳይና በቀላሉ ወደ የርስ በርስ ግጭቶች ሊመሩን የሚችሉ ሆነው ስላገኘኋቸው ላካፍላችሁ የወሰንኩት።

 

) ከላይ ከጠቀስኳቸው የርስ በርስ ግጭቶች የተማርኩት ትልቁ ነገር፣ የሰው ልጅ ከሰው ልጅነት ወደ እንስሳነት ባህርይ ለመለወጥ የሚያስፈልገው ጊዜ እጅግ በጣም አጭር መሆኑን ነው። ከግጭቱ በፊት በመልካም ጎረቤትነት፣ አበልጅነት፣ ሚዜነት አማችነት እና ተመሳሳይ ቤተ ዘመድነት፣ ብሎም በጓደኝነት ተዋድዶና ተከባብሮ አብሮ በሰላም እየኖረ ማኅበረሰባዊ ችግርን አብሮ እየፈታና ክፉና ደጉን አብሮ ያሳለፈ ሕዝብ፣ ግጭቱ በተጀመረ እጅግ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ከዚህ በፊት እንደማይተዋወቁ ሆነው በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገዳደሉ አስተውያለሁ። ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ፣ የኃይማኖት ተቋማት እንኳ ሳይቀሩ ያላቸውን የሞራል የበላይነት ተጠቅመው ሕዝቡን የዕምነት መጽሓፎች በሚያዙት መሠረት ለጠብ ሳይሆን ለፍቅር ማዘጋጀት ሲገባቸው፣ የራሳቸው ብሔር ብቻ ንጹሕና ሥራቸውም ቅዱስ እንደሆነ፣ ተቃራኒውን ብሔር ግን እንደ ሠይጣን በመሳል በእሳት ላይ ቤንዚን ሲጨምሩ ማየቱ የሰው ልጅን የጭካኔ ባህርይ ፍንትው አድርጎ ያሳያል[3]። በሰባዎቹ መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ በተከሰተው “የቀይ ሽብር” ጊዜ የአንድ አባት ልጆች፣ የተለያየ ፖሊቲካ አስተሳሰብ ስላስተናድጉ ብቻ ወገን ለይተው ሲገዳደሉ ያየነው ስለሆነ፣ ለአገራችንም ሕዝቦች፣ አያድርስና፣ ዛሬም ወንድማማች፣ ጓደኞች ወይም አበልጆች፣ በአስተሳሰብ ስላልተጣጣሙ ብቻ ለመገዳደል ቢነሱ እንግዳ አይሆንብንም ማለት ነው። የሚያስፈራው ደግሞ የዛሬው ለግጭቶች መንሥዔ ሊሆኑ የሚችሉ ሰበቦችና ምክንያቶች ብዛት በቀይ ሽብር ጊዜ ካየነው በቅርጽም በይዘትም እጅግ በጣም የሰፉ መሆናቸው ነው።

 

) በነዚህ የርስ በርስ ግጭት በተካሄደባቸው አገራት ሌላ ያስተዋልኩት ነገር ደግሞ፣ ከሁሉም በላይ የወጣቱ ትውልድ ለሌሎች የፖሊቲካ ሥልጣን ጥማት መናጆና ተቀዳሚ ሰለባ መሆን ነው። ወጣቱ በአገራዊ ቀውስ ምክንያት ሥራ አጥነት ናላውን አዙሮ ተስፋው በጨለመበት ሰዓት፣ “የፖሊቲካ እንስሳት” ቀርበዋቸው፣ የወጣቱ ችግር አልፋና ኦሜጋ “የአንድ የሆነ ብሔር/ሕዝብ” የቀድሞ የግፍ አገዛዝና ያለፈ የተዛባ ታሪክ ስለሆነ “የድሮውን ዝናና ክብር ለማስመለስ ተነስና ተሟገት” ብለው ለአመጽ ያነሳሱታል። ወጣቱም በየጎዳናው ተስፋ የሌለውን ኑሮ ከሚመራ ለዚህ “የተዛባ የፍትሕ ታሪክን የማቃናት ቅዱስ ዓላማ” መዋጋትን ብሔራዊ ግዴታው አድርጎ ይወስደውና፣ ያለ አንዳች ማመንታት ጽንፈኞች ባዘጋጁለት ወጥመድ ውስጥ ይገባል። ጦርነቱም ካለቀ በኋላ በዕድሜያቸው የገፉ ተፋላሚ ወገኖች ጉልበታቸው ዝሎ “ሰላምን” መሻት ሲጀምሩ እንኳ፣ ትልቁ የማኅበረሰቡ ችግር ወጣቱን ከጠብመንጃ አላቅቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ ነው። ጠብመንጃ “ጠላትን” ያሸነፉበት፣ የግል ጸጥታን ለማስፈን የተጠቀሙበት፣ የዕለት ጉርስ ያገኙበት እና ቀንም ሌትም የማይለያቸው አስተማማኝ ወዳጃቸው ስለ ነበረ፣ ወጣትን ከጠብመንጃ አላቅቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ እጅግ በጣም አድካሚ ሥራ ነው።

 

) ብዙ ብሔሮች ባለቤት የሆነች አገር ውስጥ ለርስ በርስ ግጭት መንስዔዎች አንዱ፣ የአንድን ሕዝብ “የድሮ ታሪክ፣ ክብርና ዝናን ለማስመለስ” ሲባል አንዳንድ ጽንፈኛ ብሔርተኞች የሚያቀነቅኑት ትርክት ነው። ለዩጎዝላቪያ ግጭት ትልቅ አስተዋጽዖ የነበረው የሚሎሼቪች “የታላቋን ሴርቢያ ክብርና ዝናን ለማስመለስ” ሲባል የሌሎችን ሬፑብሊኮች (ክልሎች) ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስ ፕሮፖጋንዳ መጀመሩ ነበር። በአብካዚያ ለተጀመረው ግጭት ዋናው ሰበብ የጆርጂያው መሪ ጋምሳ ኩርዲያ “የታላቋን ጆርጂያን ገናናነት መልሶ ለመገንባትና በአብካዚያ ግዛት ላይ ያለውን የበላይነት አገዛዝ መልሶ ለማስፈን” የጀመረው እንቅስቃሴ ነበር። የዩክሬይን ጽንፈኞች ያላቅማቸው “የዩክሬይንን ሕዝቦች የበላይነት በክራይሚያ ባሕረ ሰላጤና በምሥራቅ ዩክሬይን ለማስፈን” ሲባል የክራይሚያንና የዶንባስ ሕዝቦችን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጣስ ሲጀምሩ ነበር ዛሬም በመካሄድ ላይ ያለው አስከፊው የርስ በርስ ግጭት የተጀመረው።

 

) አንድ ሕዝብ ወይም ቡድን የራሱን አገዛዝ ወይም ዕምነት በሌላው ቡድን ላይ ለረጅም ጊዜ ካሰፈነ፣ የራሱ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ኃይማኖትና ባሕል ብቻ ትክክለኛ ይመስለዋል። ለምሳሌ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለትም በኔ ዕድሜ፣ ለአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ፣ የአማርኛ ቋንቋ፣ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት፣ ባለ ጥበብ ሸማና ተነፋነፍ ሱሪ፣ ዶሮ ወጥና ሽሮ ወጥ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ባሕል ይመስለዋል። የኦሮሞ ኢሬቻና ዋቄፋና፣ የሲዳማው ጨንበላላ ወይም የሙርሲ ሕዝቦች አካላቸውን የሚያገጡበት ዘዴ ወዘተ ኢትዮያዊ እንዳልሆነ አድርገው ነው የሚወስዱት። ዛሬ ለምሳሌ፣ እያንዳንዱ ብሄር የየራሱን ቋንቋ በየክልሉ ኦፊሴላዊ የመሥርያ ቋንቋ አድርጎ ሲጠቀምበትና ሥነ ጽሁፉን ሲያዳሳድግብት ማየት ያልለመደው የኔ ትውልድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት አደጋ ላይ እንዳለ አድርጎ ይወስደዋል። በዚህም መሠረት፣ ሌላ አዲስ የሆነ እና ፊት “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ሥርዓት ወይም ኃይማኖት ነው ተብሎ የተነገረለትን የሚቀናቀን እና እኩልነትን እንኳ የሚሰብክ አዲስ ሓሳብ ቢመጣ፣ ነባሩ ሥርዓት በጭራሽ አይቀበለውም። “የበላይነትን ለለመደ እኩልነት ጭቆና ይመስለዋል” የሚባለውም ለዚሁ ነው። በዚህ፣ በአዲስ መልክ በተዋቀረ አገር ውስጥ፣ ድሮ ተበድለን ነበር የሚሉ ሕዝቦች እኩልነትን ማጣጣም ሲጀምሩና ነባሩ “በዳይ” ደግሞ ያለፈን “ታሪክ” ስሕተት መቀበል ሲያቅተው፣ ለግጭቶች መቀስቀስ ጥሩ ሰበብ ይሆናል።

 

) በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለሕዝብ የሚደርሱ ዘገባዎች ሁሌም ወገናዊ ናቸው። አንድም፣ በዘጋቢው ማንነት ወይም ዘጋቢው በሁለቱም ወገን በአካል ተገኝቶ የመዘገብ ዕድል ባለማግኘቱ ምክንያት አብዛኛው ዘገባ ገሚሱ ብቻ እውነት ነው። በዩጎዝላቪያው ጦርነት ጊዜ እኔ ከነበርኩነት የክሮኤስሽያ ከተማ በቦታው ከማየው ተጨባጭ መረጃ ተነስቼ ስለ ሴርቦች ጭካኔ በየቀኑ ስዘግብ፣ ሴርቢያ ውስጥ የተመደበው አሜሪካዊው ጉዳኛዬም ልክ እንደ እኔው በቦታው ከሚያየው ተነስቶ ስለ ክሮአቶች ጭካኔ ይዘግብ ነበር። በየቀኑ የምንዘግበው ስለ አንድ ግጭት ቢሆንም ጄኔቫና ኒው ዮርክ ያሉ አለቆቻችን የሚደርሳቸው ዘገባ ግን የሚቃረን ነው። የኛን ዘገባ ከዛሬ አምሳ ዓመት በኋላ አንድ ተመራማሪ ስለ “እውነተኛው የዩጎዝላቪያ ጦርነት ታሪክ” ለማወቅ ከማለት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ቤተ-መጽሃፍ ሄዶ የኛን ዘገባ ቢያጠናቸው፣ ሊኖረው የሚችለውን የተምታታ መረጃ መገመት አያዳግትም። ለዚህም ነው፣ በግጭቶች ወቅት የሚቀርቡ ዘገባዎች ወገናዊ የሚሆኑትና ለሚቀጥለውም ትውልድ የግጭቱን እውነተኛ ገጽታ ለማሳየት የማይችሉት። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ጽንፈኞች ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት፣ በዚያ ባልተማረ ማኅበረሰብና ኋላ ቀር የፊውዳል ሥርዓት ውስጥ በአብዛኛው በውጭ አገር ዜጎች የተጻፉትን “ታሪኮች” እያጣቀሱ ለዛሬው ችግራችን “መፍትሔ” አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ከሌላው ወገን በሚነሳው የአጸፋ ምት የርስ በርስ ግጭቶች የሚቀሰቀሱት።

 

) አንድ ብዙ ብሔሮችን ያቀፈ አገር የአስተዳደር ሥርዓቱን ሲያዋቅር፣ በምሥረታው ወቅት የነበሩ ሕዝቦች (ብሔሮች) በሙሉ በአገሪቱ ፖሊቲካዊና ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የእኩልነት መብት እንዲኖራቸው ተደርጎ መሠራት አለበት። አለበለዚያ፣  አንዳንድ ብሔሮች በተለይም በሕዝብ ቁጥር ብዛት ወይም በተጽዕኖ አሳዳሪነታቸው ብቻ ከሌሎች የላቀ መብት ለራሳቸው ሲሰጡ፣ ያንን እኩልነት የተነፈጉ ሕዝቦች ደግሞ ጊዜያቸውን ጠብቀው ወደ ግጭት ሊያደርስ የሚችል የማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። በሕዝቦች ስምምነትና ላይ ያልተመሠረተ አገር በቀላሉ ለርስ በርስ ግጭቶች ሰለባ ሊሆን ይችላል።

 

) የአገረ ብሄር ምሥረታው ባልተሳካላቸው አገራት የሚገኙ የየብሔሩ ምሑራንና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች በተፋላሚዎቹ መካከል የሚከሰተው የመወነጃጀል ዘመን አልፎ ወደ መገዳደል ተግባር ከማምራቱ በፊት፣ ሙያቸውንና ልምዳቸውን ተጠቅመው፣ ገፍቶ የሚመጣው ግጭት ለማንም የማይጠቅም እና ልዩነቶችን በድርድር እንዲፈቱ እምብዛም አስተጸዋጽዖ አያደርጉም። በተቃራኒው፣ በጽንፈኞች በተዘረጋው ወጥመድ ተጠምደው ራሳቸው ማኅበረሰቡን በመምራት ፈንታ በጽንፈኞች እየተመሩ ዝም ብለው ወደ ጥፋት ጎዳና ሲጓዙ ይስተዋላሉ። ይህ የምሑሩ ዝምታ፣ ትምሕርቱም ሆነ የአስተዳደር ልምዱ የሌላቸውን የሰፈር አለቆችና ወጣት ጉልበተኞችን በቀላሉ ወደ አመራር ደረጃ አምጥቶ “እንወክለዋለን” ለሚሉት ሕዝብ ብቸኛ መሪ ያደርጋቸዋል። የነበረው ማኅበረሰባዊ መዋቅር እየፈረሰ ስለሆነ እነዚህ ትናንት በማኅበረሰቡ ውስጥ አንዳችም ቦታ ያልነበራቸውና ምንም የአመራርም ሆነ የአስተዳደር ልምድ ያልነበራቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በተገኘው አጋጣሚ “መሪዎች” በመሆን ግጭቱን ያባብሱና፣ የችግሩ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ራሳቸው የችግሩ አካል ይሆናሉ።

 

) በነዚህ ከላይ በጠቀስኳቸው አገራት እንዳየሁት ከሆነ፣ የእርስ በርሱ ጦርነት እንኳ “በሰላም” ካለቀ በኋላ፣ ለዘመናት አብሮ በጉርብትና የኖረ ብቻ ሳይሆን በዘር ግንዱም አንድ የሆነ ሕዝብ በእጅጉ ስለሚቆሳሰል፣ ተመልሶ በሰላም አብሮ ለመኖር እጅግ በጣም ያዳግታቸዋል። የረጅም ዘመን የትዳር ጓደኞች አንዴ የርስ በርስን ገበና አውጥተው “አንሶላቸውን በአደባባይ ማጠብ ከጀመሩ” ዕጣ ፈንታቸው ለፍቺ እንኳ ባይዳርጋቸው፣ ተመልሶ ጤነኛ ትዳር ሊሆን አይችልም። በቦስኒያ ሄርሴጎቪና ያሉት ሶስቱ ጎሣዎች ጦርነቱ ካለቀ ዛሬ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ እንደ ውሃና ዘይት ሳይደባለቁ ጎን ለጎን ይኖራሉ እንጂ እንደ ድሮያቸው ተፈቃቅሮ በሰላም አብሮ መኖር ይቅርና እንደ መልካም ጎረቤት እንኳ ተቻችለው መኖር እየከበዳቸው ነው።

 

) የርስ በርስ ግጭት የፈለገውን ያሕል አስከፊ ቢሆንና ቢረዝም፣ መጨረሻው ድርድር ነው። የሚያሳዝነው ግን፣ ከመጀመርያው ጀምሮ ሕዝቡን ለግጭቱ ሲያነሳሱ፣ ለስንት ሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ግንባር ቀደም ቀስቃሽ የነበሩና ሕዝባቸውንም ለአደጋ ያጋለጡ ጽንፈኛ ፖሊቲከኞች፣ በዲፕሎማቲክ መዲናዎች ክብ ጠረጴዛ ዙርያ ተሰብስበው “የጦርነቱን ማብቃት” አውጀው ከተቃራኒው ወገን ጋር ፊርማቸውን ያሰፈሩበትን ውል ሲለዋወጡ ማየት ነው። ያ ሁሉ ሕዝብ  አልቆ የግጭቱ ቀስቃሾችና መሪዎች ግን አንድም ቀን በጦርነቱ ሳይካፈሉ የጦርነቱን ማክተም ካወጁ በኋላ ደግሞ ተመልሰው የፖሊቲካ ሥልጣኑን ሲረከቡ ከማየት የበለጠ አሳዛኝ ነገር የለም።።

 

) ብሔር/ሕዝብን በማጥራት ላይ ያነጣጠረ የርስ በርስ ግጭት ሲነሳ፣ ሰለባ እንዲሆኑ የተወሰነባቸው ሕዝቦች (ብሔር) በአንድ አካባቢ እጅብ ብለው የራሳቸውን ማንነት፣ ኃይማኖትና ባሕል ጠብቀው፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ ሳይለምዱና ሳይዋሃዱ ተለይተው የሚኖሩ ከሆነ ለግጭቱ አደጋ በቀላሉ ይጋለጣሉ። ተመሳጥሮ በሚኖር “የሌላው ወገን” ላይ ግን አደጋ ማድረስ በጣም ይከብዳል። “ሌላዎቹ” ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመልካም ጉርብትና አብረው ክፉንም ሆነ በጎን ተካፍለው፣ “የሌላውን” ሕዝብ ባሕልና ደንብ ተቀብለው ስለሚኖሩ፣ በክፉ ዓይን አይታዩም። ስለዚህ ከግጭት አደጋው የመትረፍ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ለመደምደም ያሕል፣

 

የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተው የርስ በርስ ግጭት ሳቢያ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እንደ ነበረ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ዘገባና ተጓዳኝ የቪድዮ ምስሎች ማየት ችለናል። ከመቶ ዓመታት በላይ በአንድ አገር ውስጥ በአንድ ባንዲራ ሥር ሲኖሩ በነበሩ ሕዝቦች መካከል ይህ ዓይነቱ ወንጀል ሲፈጸም ማየቱ፣ በርግጥ ይህ ሕዝብ አብሮ ይኖር ነበር ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ የውጪን ወራሪ ኃይል አብሮ የተዋጋና ያሸነፈ፣ በእንግዳ ተቀባይነቱ የታወቀ ደግ፣ ጨዋና ኩሩ  ነው ተብሎ የሚነገርለት ሕዝብ፣ ምን ቢፈጠር ነው እንደዚህ ሊጨካከን የቻለው?  በዚህ “የማንነት” እንጂ “ኢትዮጵያዊነት” ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ባልተሰበከባት አገር ውስጥ ሁላችንም የብሔር ጭንብሎቻችንን አውልቀን ልንስማማበት የምንችል አንድ ወጥ መልስ ማግኘት ግን የሚከብድ ይመስለኛል።

 

በኔ ግምት ከዚህ ሁሉ “የአብሮነት” ዘመን በኋላ ዛሬ እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸም ለማየት የበቃነው፣ እስከ ዛሬ ድረስ የችግሮቻችንን ግንድ ሳይሆን ቅርንጫፎቹን ብቻ ከላይ ከላይ እየቆረጥን “ተጋብተን ተዋልደን” በሚል ከቃላት አልፎ ወደ ተግባር ባልተመነዘረ መዝሙር ራሳችንን ስናታልል በመኖራችን ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱና ለጠላት ያለመንበርከኩ ታሪክ የሚያኮራንን ያሕል፣ ከኛው መሃል ደግሞ በማንነታቸው ብቻ ለይተን እንደ ዕቃ ስንሸጣቸውና ስንለውጣቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዛሬም ያ የታሪክ ጠባሳቸው ሳይጠግግ አብረውን የሚጓዙ እንዳሉ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ያ አሳፋሪው የታሪካችን ክፍል በአደባባይ እንዳይወጣ ሸፋፍነን ለማለፍ መሞከራችን ዘላቂ መፍትሔ አይሠጠንም። በአጭሩ፣ባለፈው ታሪካችን ወቅት ለተፈጸሙት ወንጀሎች መነሾ የነበሩትትን የችግሮቹን ግንድ በጊዜ መርምረን ከሥሩ ነቅለን በማውጣት ዳግመኛ እንዳያንሰራራ ካላደረግን ቅርንጫፎቹን ብቻ ከላይ በመቆራረጥ ግንዱን አለባብሶ ማለፍ ጊዜያዊ እንጂ ዘላዊ መፍትሔ ሊሠጠን አይችልም።

 

አዎ! የተፈጸመውን የግፍ አገዳደል ተመልክተን ከልባችን ተንግገፍግፈናል። በመሆኑም በወንጀል ፈጻሚዎቹ፣ ባነሳሷቸውና በተባበሯቸው ግለሰብ ዜጎችና የሥልጣን ግዴታቸውን ሳይወጡ በቀሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የማያወላውል ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድም መወትወታችን ሰብዓዊ ግዴታችን ነበር። መርሳት የሌለብን ትልቁ ቁም ነገር ግን፣ ዛሬ ወንጀለኞቹ ስለተቀጡ ብቻ ማሕበረሰባዊ ችግሮቻችን  መፍትሔ አግኝተው የርስ በርስ ግጭት ይቆማል ማለት አለመሆኑን ነው። ቅጣት የወንጀልን መጠን ይቀንስ እንደው እንጂ ወንጀሎችን ከመከሰት አያድንም። የወንጀለኞቹን በአስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ ከመወትወት ባሻገር እነዚህ አሰቃቂ ወንጀሎች ተመልሰው እንዳይፈጸሙ የችግሮቹን ግንድ ቆፍሮ በማውጣትና አካፋን ኣካፋ ብሎ በስም ጠርቶ፣ በግልጽ በመወያየት የጋራ መፍትሔ መፈለጉ ላይ መረባረቡ ግን ቅድሚያ ሊሠጠው ይገባል ባይ ነኝ።

 

አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ በዚያ ጹሑፋቸው ውስጥ ባካተቷቸው መሠረታዊ እውነቶች ምክንያት በዘመኑ በነበሩ ባለ ሥልጣናትም ሆነ ምሑሮች ዘንድ ምንኛ እንደ ተኮነኑ ይታየኛል። እንኳን ያኔ ይቅርና ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚያደርጋቸው ምልክት ትንሽ ነው ብሎ መናገር በድንጋይ የሚያስወግር ይመስለኛል። እውኔታው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ የአንድነት ስሜቱ ዝቅ ወዳለ ደረጃ የወረደ ነው። ዛሬ ፋሽኑ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እንሞታለን ሳይሆን፣ መጀመርያ ማንነቴን እወቁልኝና ከዚያ በኋላ ስለ አብሮነት እናወራለን የሚለው ነው። ለብዙ ዘመናት እንደ አንድ የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው ይኖሩ የነበሩ የአገውና፣ የቅማንት እንዲሁም ሌሎች ለመክሰም የተቃረቡ ሕዝቦች “ተጨቁነን ድምጻችን ታፍኖ ነው እንጂ በሕይወት አለን” ብለው ብቅ ብቅ ያሉ አናሳ ብሔሮች በማንነታቸው የተቀዳጁትን ነጻነት በደንብ ሳያጣጥሙ ወደ አሃዳዊነት ይገባሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ይመስለኛል። ያለፈው 25 ዓመት ኢትዮጵያዊነትን አክስሞ የማንነት ጥያቄን ያጎለምስ የነበረው መንግሥታዊ መሪህን ወደ “አብሮነት” መንፈስ ለመቀየር ትልቅ የቤት ሥራ ሆኖ ይታየኛል።

 

እርግጠኛ ሆኜ የመፍትሔ ፍለጋው ፍኖተ ካርታ ይህንን ይመስላል ወይም መምሰል አለበት ለማለት ባልችልም፣ ያላንዳች ማወላወል ለማለት የምችለው ግን የችግሮቻችንን ግንድ የት እንደ ሆነ ለይተን ካወቅን በኋላ በአንድነት ሆነን ፈንቅለን ማውጣት እንደማይቸግረን ነው። በአንድነት ሆነን ስል ያለ ምክንያት አይደለም። ከልምድ እንዳየነው ከሆነ፣ የኢትዮጵያን ፖሊቲካዊና ማኅበረ ሰባዊ ችግር በተመለከተ፣ ሁሌም በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም “እንዲህ መሆን አለበት” ብለው የሚወስኑት የኢትዮጵያን ፖሊቲካዊ ሕይወት ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በሞኖፖሊ የያዙት የሶስቱ ብሔር (የኦሮሞ፣ የአማራና የትግሬ) ፖሊቲከኞች ብቻ ቢሆኑም፣ ከነዚህ ከሶሶቱ ብሔር/ሕዝቦች ይልቅ እጅግ የከበደ የዘመናት ጭቆናና ኢሰብዓዊ ግፍን ሲሸከሙ የኖሩትን ከሰማኒያ በላይ የሚሆነው ብሔር/ሕዝብ የሚያገልል ውሳኔ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብዬ ስለማላምንበት ነው። አግላይ መንገድ ተሄዶበታል ግን አላዋጣም። አንድ መንገድ እንደማያዋጣ እየታወቀ ደጋግሞ በዚያው መንገድ እየሄዱ መውጫ መፈለግ ደግሞ ዕብደት ነው።

 

ሌላው ችግራችን ደግሞ አንዳንዶቻችን እውነትን ካለመፈለግም ይሁን በየዋህነት፣ ዛሬ በአገራችን እየተካሄደ ያለው ችግር ወያኔ ያመጣው ፊዴራላዊ ሥርዓትና ለሥርዓቱ መተግበር አስፈላጊ የሆነው የክልል አስተዳደር ከመጣ በኋላ ነው ብለን የምናምን አለን። አባባሉ፣ በተለይም አፈጻጸሙን በተመለከተ የእውነትነት ጠብታ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ለዘመናት የተከመረን እና ጥሩ መሠረት ያልነበረውን የኢትዮጵያን ሕዝቦችን አንድነት በአገሪቷ የአስተዳደር ክልሎች ምክንያት የመጣ ነው ብሎ መደምደም የችግሩን መንስዔ በትክክል ካለማጤን አለያም ካለመፈለግ ይመስለኛል። አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ እንዳሉት፣ ተከታታይ መሪዎቻችን የችግሮቻችን ግንድ ቆርጠው ከመጣል ይልቅ ቅርንጫፎቹን ብቻ እየቆራረጡ ስለነበር፣ ዛሬ ችግሩን ለመቅረፍ ክልሎች ጠፍተው ወደ ድሮው የጠቅላይ ግዛትነት ወይም ክፍለ ሓገር አስተዳደር አሠራር እንመለስ ቢባል እንኳን ችግሩን ለጊዜው ያዳፍን እንደው እንጂ የሚያከስም አይመስለኝም።

 

አገራዊ ችግሮቻችን የትየለለ ናቸው። አሳሳቢ የሆነው የቅርብ ጊዜውን አሰቃቂ አደጋን ምክንያት በማድረግ ከእንቅልፋችን የነቃነውን ያሕል ለአደጋው አስተዋጽዖ አበርክተዋል የምንላቸውን አንዳንዶች ምክንያቶችንና ሰበቦችን አነሳን እንጂ፣ የአገሪቷን ችግሮች አቅፎ የያዘውን ቅርጫት ከከፈትን በውስጥ ያዘለው የችግር ብዛት ከምንገምተው በላይ ነው። የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ የሠለጠኑና ለዚሁም ወርኃዊ ደሞዝ የተመደበላቸው የሕግ አስፈጻሚ አካላት ራሳቸው መብት ጣሾች ሆነው በቁጥጥራቸው ሥር የዋለውን ዜጋ ያሰቃያሉ። የፖሊቲካ ድርጅቶቻችንና አክቲቪስቶቻችን የፖሊቲካ ሀሁ የሆነውን የተቃራኒን ሃሳብ አስተናግዶና ልዩነትን አቻችሎ ለጋራ ዓላማ መታገል በጭራሽ አይፈልጉም። ከዘመናት ታሪካችን የፖሊቲካ ልምድ የወረስነው ካንዱ ባላባት ጋር ወግኖ ሌላውን የመውጋት ባሕል ዛሬም የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን የትግል ስልት ሆኖ እያየነው ነው።

 

ምን መደረግ አለበት? ምን ማድረግ አለብን?

 

በኔ ግምት፣ አብዛኛው ያገራችን ምሑራን በትምሕርታቸው ልክ የፖሊቲካ ዕውቀታቸውን አዳብረው ለዲሞክራሲ ከመታገል ይልቅ ትግላቸው ለየመጡበት ብሔር/ሕዝብ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባለመሆኑ ችግራችንን የባሰውኑ አወሳስቦታል። ምሑራን ደግሞ ዶ/ር ቹባ ኦካዲግቦ የተባሉ የናይጄርያ ሴኔት አፈ ጉባዔ እንዳሉት፣ “አንድ ሰው የራሱን ጎሣ፣ የራሱን ኃይማኖት ወይም የፖሊቲካ እምነቱን ከፍ አድርጎ እውነትና ፍትሕን ግን ካሳነሰ ለሰው ልጅ ሸክም ነው” እንዳሉት፣[4] ያገራችን ምሑሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዚህ የወገናዊነት ማጥ ውስጥ እየገቡና እውነት ሲያኮሰሱ ስናይ አገራችን ምንኛ ቀውስ ላይ እንዳለች አመላካች ነው።

 

ከላይ ደጋግሜ እንዳልኩት፣ የዛሬውን በብሄሮችና ሕዝቦች መካከል ያለውን መሠረታዊ ችግር ላንዴና ለመጨረሻው ለመፍታት የችግሩን ግንድ ፈልገን መመንጠር አለብን። ይህ ማለት ባለፈው ታሪካችን ውስጥ የተፈጠሩ የታሪክ ስህተቶችን ፈልጎ ማግኘት ማለት ነው። እዚህ ላይ ያለፈን ታሪክ ምዕራፍ የምናገላብጠው የያኔዎችን በዳይና ተበዳይን በዛሬ ፍርድ ሸንጎ አቅርቦ ለመዳኘት ሳይሆን፣ በመጀመርያ ደረጃ፣ ተበድያለሁ የሚለው ሕዝብ ስሞታውን እያቀረበ፣ የለም አልተበደልክም ብሎ ለችግሩ ጆሮ አለመስጠት ችግሩን አደባብሶ ለማለፍ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ስለማያመጣ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የያኔውን የታሪክ ስሕተት የፈጸሙት እንኳን የዛሬውን ይቅርና የያኔውንም ትውልድ ብሔር ወክለው ስላልነበር፣ የዛሬው ትውልድ ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት ባይኖርም ችግሩን ዛሬ በድፍረት ቀርበን በአደባባይ ከመፍታት ብንቆጠብ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ ምናልባት ከዛሬውም የከፋ ትልቅ የቤት ሥራ ጥለን ማለፍ ስለሚሆንብን ነው። ያ እንዳለ ሆኖ፣ የዛሬ ችግራችንን ለመፍታት ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው የታሪክ ስሕተቶች በስተቀር ሌሎቹን ላሁኑ ችግራችን አንዳችም ፋይዳ የሌላቸውን ያለፈን ታሪክ ዛሬ አንስቶ በሱ ላይ መሟገቱ የተዛባውንም የታሪክ  ስሕተት አያስተካክልም፣ መራራቅን እንጂ መቀራረብንም አያዳብርም።

 

ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን በዚህ ሁሉ ነውጥ ውስጥ ሁለት ተስፋ ሰጪ ነገሮች ናቸው ብዬ የምገምታቸውን በዚህ አጋጣሚ ላነሳ እፈልጋለሁ፣ የመጀመርያው ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ከአንድ መቶ በላይ የፖሊቲካ ድርጅቶች ውስጥ ባለፈ የታሪክ ስሕተትም ሆነ በሌላ ምክንያት ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ የራሴን ነጻ አገር መመሥረት እፈልጋለሁ ብሎ ፕሮግራሙን የነደፈ አንድም የፖሊቲካ ድርጅት አለመኖሩ ነው። ሁላቸውም፣ “በምን ዓይነቷ” የሚለው ያከራክራቸው እንደው እንጂ ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ። ሁለተኛው ደግሞ፣ በዚህ ሁሉ ነውጥ እና የርስ በርስ ግጭት ወቅት፣ የተጎዳዳው ሕዝብ በጥቂት ከተሞች አካባቢ ያለው ነው እንጂ መላው የኢትዮያ ሕዝብ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ሰፊ ሕዝብ በምንም መልኩ አልተካፈለበትም፣ የግጭቱም ሰለባ አልሆነም። በግጭቱ ወቅት ልክ እንደ ድሮያቸው ጎርቤትማማች ተከባብረው አንዳቸውም ሌላውን በክፉ ዓይን ሳያዩ መከራውን አልፈውታል። ያ ባይሆንማ ኖሮ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ብዙ ሚሊዮን የአማራ ሕዝብ ለትልቅ አደጋ ይጋለጥ ነበር።

ወገኖቼ፣

የርስ በርስ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበትና ከጦርነት ዓይነቶች ሁሉ እጅግ በጣም አስከፊ መሆኑን አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋና አንድ ኃይማኖት ባላቸው በሶማሊያ፣ በሊብያ፣ በኢራቅና በሶርያ የተከሰተውን ማየቱ ብቻ ይበቃል። በ1992 ዓ.ም የያኔው የዩጎዝላቪያ ፕሬዚዴንት ሚሎሸቪች “ ችግሮቻችንን በሠለጠነ መንገድ እንፈታለን እንጂ እንደ አፍሪካውያን አንገዳደልም” ብሎ እንዳልነበር፣ በአንጻራዊ ሰላም ለዘመናት አብሮ ይኖር የነበረው አንድ የዩጎዝላቪያ ሕዝብ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንዳችም የጋራ ታሪክ እንዳልነበር ሆኖ እጅግ በጣም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገዳደለ። አገሪቷም በሰባት ቦታ ተከፋፈለች። አንድ ሕዝብ፣ አንድ ኃይማኖት፣ የጋራ ባሕል ኖሯቸው አንድ ቋንቋ እያወሩ ለዘመናት እንደ አንድ ማኅበረሰብ የኖረ የሶማሌ ሕዝብም ከርስ በርስ ግጭት ለመዳን አልቻለም።

 

ደጋግሜ እንዳልኩት፣ የእርስ በርስ ጦርነት መጨረሻው ሁለንተናዊ ጥፋት ስለሆነ ከጦርነቱ በኋላ የሚገኘው ድል አሰቃቂ የሆነና ሰውም አልቆ ሃብትም ወድሞ የሚገኝ ባዶ ድል ነው። ዛሬ ከፊታችን የተደቀኑትን ጊዜያዊ ችግሮች ላይ ብቻ ዓይናችንን ተክለን ነጋም ጠባም ስለዚያው ብቻ ከማቅራራት፣ እነዚህ ችግሮች እንዴት በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱም ቁጭ ብለን መነጋገር መቻል አለብን። በአንድ በኩል “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን አብረን የኖርን” እያልን፣ ዛሬ አንዳችን ሌላውን እያንቋሸሽንና ያልሆነ ስም እየሰጠን ለማዋረድ ከመሞከር፣ ነገ ሰላም ሰፍኖ ተገናኝተን ዓይን ለዓይን ስንተያይ ይጸጽተናልና በማንነታችን ተከባብረን አብረን እየኖርን የጋራ ችግራችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንትጋ! ኦሮሞና አማራን ያላቀፈች ኢትዮጵያ በጭራሽ ልትኖር እንደማትችል ለማንም ግልጽ የሆነውን ያሕል፣ እንቆቅልሽ የሆነብን ደግሞ የነዚህ ሁለት ሕዝቦች አብሮነት ትልቁ ጠንቅ ምንጩ ከነዚህ ሁለቱ ብሔር የወጡ የብሔር ጽንፈኞች ጎራ መሆኑ ነው። ስለዚህ ከነዚህ ሁለት ብሔሮች የወጡ ምሁራንና ከጽንፈኝነት የነጹ ግለሰቦች፣ እነዚህ ጽንፈኞች የሚተፉትን የመከፋፈል መርዝ እየተዋጋን፣ እያንዣበበ ያለውን አደጋ እንዳይከሰት ለማድረግ፣ በአንድ ጣራ ሥር ተሰብስበን፣ አደብ ገዝተን በቅንነት የምንወያይበትን መድረክ ለመፍጠር እንጣር! ሌላ ምርጫ የለንም። የሚከፋፍለን ብዙ ነገር ያለውን ያሕል የሚያዋህደን ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ መሆኑን አውቀን ሕዝባችንን ከአደጋ ለመታደግ በጋራ ሆነን የጸና አብሮነትን ፍኖተ ካርታ የምናዘጋጅበት ጊዜው አሁን ነው።

 

እኛ የሰው ልጆች ከከብት የምንለየው፣አለኝ ውድ ጉደኛዬ ዓለም ሰገድ፣ አስቀድሞ የመተንበይ፣ የማሰብ ወይም የመገመት ልዩ ተሠጥዖ ስላለን ነው። ከብቶች ሰማዩ ሲጠቁር ዳመናው ወደ ዝናብ እንደሚቀየር አስቀድሞ የማሰብ ችሎታ ስለሌላቸው፣ መጠለያ ፍለጋ የሚጀምሩት ዝናቡ መዝነብ ከጀመረ በኋላ ነው። አስቀድሞ ያልታሰበበት ውሳኔ ስለሆነና መጠለያውም በቅርቡ ሊገኝ ስለማይችል፣ በዝናቡም በበረዶውም ይመታሉ። እኛም፣ ተፈጥሮ የለገሠንን አስቀድሞ የማሰብና የመገመት ተሠጥዖአችንን በአግባቡ ተጠቀምን ከአደጋው የምንድንበትን መፍትሔ ካሁኑ በጋራ ካልፈለግን፣ እያንዣበበ ያለው አደጋ ዕውን የሆነ ዕለት፣ ያኔ መጠለያ አጥተን በጅምላ ልንጠፋ እንደምንችል ማወቅ አለብን።

******

 

ባይሳ ዋቅ ወያ

wakwoya2016@gmail.com

 

 

 

 

 

 

 

 

 

[1] ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሃዲያ፣ አፋር፣ ጋሞ፣ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አላቸው።

[2] ናኦ፣ ከም፣ ሙርሲ፣ ከስሜ፣ ቦዲ፣ አርቦሬ፣ ጌዲቾ፣ ብራይሌ፣ ኩናማ፣ ኩዌጉ፣ ፌዳሺ፣ ዙልማን፣ ባቻ፣ ገደቶ፣ ሺታ/ኡፓ፣ ሙርሌ፣ ቀመም፣ ካሮ፣ ዲሜ፣ ሼ፣ ቀወማ፣ ናቸው።

[3] በዩጎዝላቪያ ጦርነት ጊዜ፣ መሥሪያ ቤቴ በሚገኝበት ስፕሊት በምትባል የክሮኤሽያ ከተማ ውስጥ ለቦስኒያ ስደተኞች መጠለያ እንዲሠጡ ማኅበረሰቡን እማጸን በነበረበት ወቅት የተዋወቅኋቸው የከተማዋ ቤተ ክርስቲያን ቄሳውስት አንድ ቀን ለዓመታዊው የቤተ ክርስቲያኑ አመራር “ሽርሽር” ጋብዘውኝ ወደ አንድ ደሴት ሄደን በነበረበት ወቅት፣ ዋናው የክሮአት ቄስ ለምሳ የተዘጋጀውን በግ አጋድሞ አንገቱን ከቆረጠ በኋላ“እዩት ይኸንን የሴርብ ገበሬ አጋድሜ ሳርደው፣ እዩት ፈርቶ ስማጸነኝ፣ የታባቱን የክሮኤሽያን ሕዝብ ጀግንነት ያልተረዳ ደደብ ወዘተ ……” ብሎ ያቅራራበት ሁኔታ ዛሬም ትዝ ሲለኝ ይዘገንነኛል።

[4] If you are emotionally attached to your tribe, religion or political leaning to the point that truth and justice become secondary considerations, your education is useless. Your exposure is useless. If you cannot reason beyond petty sentiments, you are a liability to mankind. Dr. Chuba Okadigbo

 

1 Comment

  1. We Ethiopians got two personalities. One is the humble personality which we show towards our elders and the second personality is the bully personality we show towards the youngers. Most are trained to accept since childhood that bulying whoever they consider is younger age than them is their right , as they also consider being bullied by whoever is older than them is their responsibility. This bullyism trend created so much secret attacks and sabotages which led to the civil war and negativity perpetrated by those who try to escape the bullies attack , they can not openly oppose the bullies because Ethiopia’s societal hierarchy encourages the older even if it is one year older to bully the younger. Be it in a family setting , in a school , neighborhoods or any other place the younger is constantly having to come up with new sneaky attack methods to save itself from the older bully’s attacks. In most cases the younger knows attacking first is the best form of defence. That is why it is almost impossible to find out who is attacking who and serve justice because in most cases the attacks are coming from the least expected directions.

    This bullyism is a little different when it comes to how the women/mothers in Ethiopia practice it . Older Women bully younger women and the older woman also got the authority to bully the children the younger woman has. The younger woman treats the children of the older woman with such especial care and respect because they are the children of a woman who is older than her. This usually results in unconditional right for the older woman’s first born son child to become a leader “የጎበዝ አለቃ” over all men younger than him in his surroundings. Even though he is not fit for the position he just automatically gets it and bullies everyone , giving unreasonable orders. This spoiled leader is usually the person who abuses his power “ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ” and all other type of ridiculous demeaning oppression which will eventually back fire from the very people who he bragged about to be their leader. With investigators usually failing to find out that things are back firing at the so called leader with no court really knowing how to serve justice in such conditions that is why የተገፋው ከምንም ጊዜ በላይ አምርርዋል right now Ethiopians should consciously stop bullying before it destroys each and every last of the people in Ethiopia. Be it your close family member , close friend , someone you fully thrust it does not matter honors bullying because you don’t know how seriously the one at the receiving end is firing back. Parents need to stop others from bullying their children too. We are seeing the consequences in our own eyes right now violence becoming a norm because of the giving orders addiction and he bullyism addiction Ethiopians got.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.