በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ጀምረዋል

ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2013 ዓ.ም በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የሕግ ማስከበር ዘመቻው በስኬት ከተጠናቀቀበት ማግስት ጀምሮ ነዋሪዎች በነጻነት መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ዞኑ አስታውቋል። መንግሥትም ዞኑን መልሶ ለማደራጀት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የዞኑ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸተ ደምለው ገልጸዋል። በዚህም አብዛኛው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል። አቶ አሸተ እንደተናገሩት በዞኑ ከሚገኙ አራት ሆስፒታሎች መካከል ሦስቱ ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ከ21 ጤና ጣቢያዎች ውስጥም 18 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፣ ቀሪ 66 ጤና ኬላዎችን ሥራ ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል። የጤና አገልግሎት ተቋማት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመለሱ የአማራ ክልል መንግሥት ባለሙያዎችን ልኮ በማገዝ፣ መድኃኒትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁስ እና የሰው ኀይል በማሟላት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በትምህርት ዘርፉም ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን አስረድተዋል። በዞኑ ከሚገኙ 219 ትምህርት ቤቶች መካከል 131 የሚሆኑት ተከፍተዋል፣ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል። ባንኮችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን ነው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊው የተናገሩት።
አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ የዞኑ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን የተናገሩት አቶ አሸተ የአገልግሎት አሰጣጡን የተሟላና ተደራሽ ለማድረግም አበረታች እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል። የአማራ ክልል መንግሥት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ደመወዛቸው ሳይከፈላቸው ችግር ውስጥ ለነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ወር ደመወዛቸውን እንደከፈለም ተናግረዋል። አቶ አሸተ እንዳሉት የመንግሥት ሠራተኞቹ በሚሠሩባቸው ተቋማት ተመልሰው መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩም ተደርጓል።
ይሁን እንጂ የፍትሕ ተቋማት ተሟልተው አገልግሎት እንዳልጀመሩ አስታውቀዋል። ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የፍትሕ ተቋማትን ለማሟላት የዳሰሳ ጥናት መደረጉን በመግለጽም በቅርቡ ለመክፈት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተጓዳኝ በሕግ ማስከበር ሂደቱ በልዩልዩ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰላማዊ ሰዎችን የመመለስ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አምስት የከተማ አስተዳደርና አራት የገጠር ወረዳዎች አሉ። በዞኑ ይኖሩ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነባር የአማራ ተወላጆች በደረሰባቸው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት መፈናቀላቸውን አብመድ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
አብመድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.