ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

ወርሃዊ መግለጫ
Habesha | zehabesha.info የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ቡድን ከዜጎች ደህንነት ጋር በተያያዘ ችግር ወደተፈጠረባቸው አካባቢዎች በመላክ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በመመርመር እና ነዋሪዎችን በማነጋገር ችግሮቹን በተመለከተ የሚደርስበትን ግኝትና መደምደሚያ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጥር 06 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ኮንሶ፣ መተከል፣ ማይካድራ እና መቐለ ልዑክ ቡድን በመላክ በስፍራዎቹ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማጣራት ሙከራ አድርጓል፡፡
መቐለ
ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሕወሓት ቡድን መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥትም የህግ ማስከበር ዘመቻ ባደረገ ማግስት የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች ወደ መቀሌ ተጉዘው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል፡፡
ኢዜማ የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በትግራይ በመክፈት በክልሉ ስላለው ሁኔታ ከአባላትና ከደጋፊዎቹ ጋር ውይይት ካደረገ በኃላ በስምንት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል፡፡ ከሰሜን እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው ከ1700 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ወደተጠለሉበት ኢትዮ – ቻይና ት/ቤት በማቅናት በመጠለያው ውስጥ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት በላይ የቆዩ ወጣቶችን፣ ሕጻናትን እና ሴቶች እንዲሁም አቅመ ደካሞች በተለይም የሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮቹ በአካል በማግኘት ለማናገር ተችሏል፡፡
19 ቀበሌ በሚገኘው ቅሳነት ትምህርት ቤት በመሄድ ከዛላምበሳ፣ ከኢሮብ እና ከእዳጋ ሐሙስ የመጡ ከ2500 በላይ ተፈናቃዮች ያሉበት ምግብ፣ ውኃ፣ ፍራሽ፣ እና የአልባሳት እጥረት ያለበትን መጠለያን ለማየት ተችሏል፡፡ በአንድ ክፍል በውስን ፍራሾች ላይ ከ30 በላይ ሆነው የሚተኙ አራስ ሕጻናት የያዙ እናቶች እና የጤና ችግር ያለባቸው ወገኖች በመጠለያው ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ኤልሻዳይ የተሰኘ ስደተኞችን እና ጎዳና ተዳዳሪዎችን በማቋቋም ሥራ ላይ የተሰማራ ግብረ ሰናይ ድርጅት በክልል ከተፈናቀሉት በተጨማሪ ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ፣ ከኤርትራ የመጡ ስደተኞች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በስሩ ይዟል፡፡ በዚህ ጣቢያ ላይ ያሉ ዜጎች ቋሚ የሆነ እርዳት እንደሚደረግላቸው ቢነገርም ለሕጻናት ለታማሚዎች እና በምግብ ለተጎዱ ሰዎች የሚሆን የአልሚ ምግብ ፉርኖ ዱቄት፣ የዘይት የመድኃኒት እና የሕጻናት ንፅሕና መጠበቂያ እጥረት እንዳለ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች ምግብ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ፣ ብርድልብስ ለተፈናቃዮች እያቀረበላቸው ያለው በመቐለ ከተማ ነዋሪዎች እና በአንዳንድ በጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች አማካኝነት ነው፡፡
የኢዜማ አመራሮች የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ከመጎብኘት በዘለለ ከከተማዋ ወጣቶችም ጋር ለመወያየት ጥረት አድርገዋል፡፡ ወጣቶቹም፡-
• በኤርትራ ወታደሮች ፈፀሙት ያሉትን አሰቃቂ ጥቃቶች ገልጸዋል፣
• በትግራይ ሕዝብ ላይ ከ40 ዓመት በላይ ተጭኖ የቆየ ሥርዓት በቅርቡ ከጫንቃው ቢነሳም ሕዝቡን በፍጥነት ማሳመንና ወደ ቀድሞ ሕይወት ለመመለስ ጊዜ ስለሚፈልግ የመንግሥት ታጋሸነት እንደሚያስፈልግ፣
• በትግራይ በየ20 ዓመቱ ጦርነት እየተቀሰቀሰ ልጆቿን የምትገብርበት ሁኔታ መቀጠሉ እንደጎዳቸው በምርጫ የሚያምን ትውልድ መፈጠር እንደሚያስፈልግ፣
• የሕውሓት አመራሮች ተመልሰው ይመጣሉ በማለት ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች እንደአሉ፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ከዚህ ስሜት እንዲወጡ ጊዜያቸውን በሥራ እንዲያሳልፉ ማድረግ እንደሚገባ፣
• አብዛኛው አቅም ያላቸው ወጣቶች በመሸሻቸው ስልክም ስለማይሠራ የሸሹትን ቤተሰቦቻቸው ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ አለመቻላቸው ከፍተኛ ጭንቀት
እንደፈጠረባቸው፣
• አሁን ላይ ፖለቲካውን ለጊዜው በማቆየት ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ሁሉም ርብርብ ሊያደረግ እንደሚገባ ነዋሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው ለአመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
ወደመቐለ የተጓዘው ቡድን በመጠለያ ያሉ ወገኖች ተዟዙሮ ከማየት ጎን ለጎን በቦታው ከነበሩ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲሁም ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ እና መፍትሔዎች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከዶ/ር ሙሉ ነጋ ጋር በመገናኘት ‹‹በክልሉ አመራር የነበሩ ታዋቂ ፖለቲከኞችን ፤ ታዋቂ ግለሰቦችን እና የሌሎች ፓርቲዎች አባላት በመዋቅሩ ውስጥ አካተው ቢጠቀሙባቸው ጥሩ እንደሚሆን ለዚህም ኢዜማ በዞን፣ በወረዳ፣ እና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ አባላቶቹ በመመደብ ጊዚያዊ አስተዳደሩን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጾላቸዋል፡፡
ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ የሠራተኛ እና የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ከአብርሃ ደስታ ጋር በተደረገ ውይይት ከሰብዓዊ ድጋፍ አንጻር በክልሉ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመገንዘብ ቢቻልም ከመቐለ ከንቲባ ከአቶ አታክልቲ ጋር የታቀደው ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ማይካድራ
ወደ ማይካድራ የተጓዘው ልዑክ ቡድን መረጃ ያሰባሰበው የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ቀብር አስፈጻሚዎችን እና ወታደሮችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የጅምላ ቀብር ቦታዎችን፤ ሰፋፊ ሜካናይዝድ እርሻ ቦታዎችን፤ የተለያዩ ጥቃት ለመፈፀሚያነት የተዘጋጁ ድምዕ አልባ መሣሪያዎች የተከማቹባቸውን ሕንጻዎች፤ በከፍተኛ ደረጃ ግጭት የተካሄደባቸው ሥፍራዎችን (ለምሳሌ ከአዲስ አበባ 970 ኪሜ ላይ ከባድ እልቂትና ከሕወሓት ጋር የመጨረሻ ከባድ ግጭት የተካሄደበትን ንጓራ ድልድይን የመሳሰሉ)፤ በባህላዊ ጦር መሳሪያ እልቂት የተፈጸመባቸው አካባቢዎችን፤ ቀደም ሲል የሕወሓት ወታደራዊ ካምፕ ነበሩ የተባሉ ቦታዎችን ወዘተ… በመጎበኘት መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተሞክሯል፡፡
በግጭቱ ወቅት የታዩ ክስተቶች
ሕወሓት ያስተዳድራቸው በነበሩ አካባቢዎች በተለይም ማይካድራ እና ሑመራ ግጭቱን ተከትሎ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ሞት እና የሀብት ውድመት ተከስቷል፡፡ የማይካድራው እልቂት የተጀመረው ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም አጥቢያ ሲሆን፤ እስከ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በነዋሪዎቹ ላይ እልቂት እንደተፈፀመ ልዑክ ቡድኑ ከነዋሪዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር በሚመለከት ልዑክ ቡድኑ የተለያዩ መረጃዎችን የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ ቀብር አስፈጻሚዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ መረጃ ለማሰባሰብ ሙከራ አድርጎ የነበረ ሲሆን የሟቾቹ ብዛት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ትክክለኛ ቁጥር ለማስቀመጥ እንደሚያዳግት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቡድኑ ከላይ የተጠቀሱትን አካላት ቃለመጠይቅ ከማድረግ በተጨማሪ የጅምላ ቀብር ሥፍራዎችን ተመልክቷል፡፡
ሟቾቹን አንድ በአንድ ለመቅበር ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የሟቾቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ጉድጓድ መቆፈር እና አስክሬኖቹን መሸከም ስላቃተ በጅምላ ከመቅበር ውጪ ሌላ አማራጭ ስላልተገኘ አስክሬኖቹን በዶዘር መቅበር ብቸኛ አማራጭ እንደነበር ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ ሟቾች ማንነታቸው እየተለየ የተጠቁ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ወደ ማይካድራ የተጓዘው የኢዜማ ልዑክ ቡድን ፖለቲካዊ ቀውስ ወደተባባሰባቸው ማይካድራ፣ ሑመራ እና አካባቢው በደረሰበት ወቅት የቀውሱ መጠን ካለፈው አንጻር እንደቀነሰ ተረድቷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም እልቂቱ እንዲያበቃ፤ ቂመኝነት እንዲቀር፤ ሀዘኑ እንዲለዝብ የሃይማኖት አባቶች መገዘታቸው እና በሕዝቡ ውስጥ ሆነው ችግሩ እንዲፈጠርና የተፈጠረውም እንዲባባስ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች ከአካባቢው በመሰወራቸው መሆኑን ልዑክ ቡድኑ መረዳት ችሏል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የአካባቢው ሚሊሺያ አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና እንደ ግለሰብ የታጠቁ ነዋሪዎች በጋራ ተቀናጅተው በመሰለፍ የሕወሓትን ኃይል በመፋለማቸው ጦርነቱ ሊወስድ ከሚችለው ጊዜ ባነሰ መቋጨቱን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
የአካባቢው ፀጥታና ተያያዥ ሁኔታዎች
የመኖሪያ ቤቶችን እና የንግድ ተቋማትን እየሰበሩ ዝርፊያ መፈፀም ዛሬም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ያሉ ንብረቶችም ዝርፊያ እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ስጋቶች ተደቅነውባቸዋል፡፡
የሱዳን ጦር ሊመታን ይችላል፤ ‹‹ሳምሪ›› የሚባለው አደረጃጀት ሙሉ ለሙሉ ስለመጥፋቱ እርግጠኞች ስላልሆንን በድጋሚ ሊያጠቃን ይችላል፤ በየአካባቢው ተቆርጦ የቀረው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ ጥቃት ሊፈፅምብን ይችላል፤ በአማራ ክልል አስተዳደር በኩል የአድሎዊነት ስሜት እየተስተዋለ ስለሆነ ስጋት ውስጥ ወድቀናል በማለት ነዋሪዎች ያለባቸውን ስጋት ጠቁመዋል ፡፡
በአጠቃላይ ቡድኑ ማይካድራን እና አካባቢውን በጎበኘበት ወቅት ነዋሪው በከባድ ፈተና ውስጥ እንደሚገኝ ለመረዳት ችሏል፡፡ የደህንነት ስጋት መኖር እና የመሰረተ ልማቶች ያለመኖር ነዋሪውን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገው እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኮንሶ
ወደ ኮንሶ የተጓዘው ቡድን በካባቢው ለተፈጠሩ ችገሮች መነሻ ምክንያት ሆኖ ያገኛው የታችኛውን አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቀየር የተደረገው ማሻሻያ እና በተለይ ከአከላለል ጋር በተያየዘ በነዋሪዎች የተነሱ ቅሬታዎች ናቸው። ምንም እንኳን መነሻ ምክንያቱ ይሄ ይሁን እንጂ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍለጎት ለማሰካት የተንቀሳቀሱ ኃይሎች ለግጭቱ መባባስ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።
ከላይ ተጠቀሰው ምክንያት ከህዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት
1. በገርጩ ቀበሌ የግብርና ማሠልጠኛ፣ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጤና ኬላ በዚሁ ቀሸሌ በኢፈዮ ንዑስ መንደር ከ1—4ኛ ክፍል ትምህርት ቤት ሙሉ በመሉ ተቃጥሏል።
3. በችሆ፣ ሰገን ገነት እና ዱባያ ቀበሌዎች ከፍተኛ የቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆኑ በአይሎታ ዶከቱ 5 ንኡሳን መንደሮች ሙሉ በሙሉ ተቀጥሏል
5. ፉጩጫ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በርካታ መኖርያ ቤቶች ተቃጥለዋል
በአጠቃላይ በተፈጠሩት ግጭቶች 9,541 የሳር ቤቶች፣ 1,871 የቆርቆሮ ቤቶች፣ 198,418 ኩንታል እህል፣ 64,381 የቤት ውስጥ ቁሶች 33,566 የእርሻ መሳርያዎች፣ 32, 345 የቁም እንስሳት እና 22 ወፍጮ ቤቶች መውደማቸውን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በዞኑ 14,167 አባወራዎች፣ በአጠቃለይ 84,244 ዜጎች ተፈናቅለዋል። ከዚህም ውስጥ 51,000 የሚሆኑት ቤት ንብረታቸው ሙሉ ለሙሉ የወደመባቸው መሆናቸውን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በኮንሶ የሚታዩ ሰብዓዊ እና የደህንነት ችግሮች
የምግብ ችግር፣ ተፈናቃዮች ከእንስሳት ጋር በመጠለያዎቹ አብሮ መኖር፣ የሚሞቱ ሰዎች መብዛት፣ በግጭት ቀጠናው የትምህርት ቤት መዘጋት፣ የታጠቁ ኃይሎች የሚያካሂዱት ዝርፊያ እና ንብረቶችን ማቃጠል፣ አሁንም የተኩስ ልውውጥ አለመቆሙ፣ ከአንድ ወር በኋላ የዝናብ ወቅት የሚጀምር ቢሆንም ለእርሻ አለመዘጋጀታቸው፣ ተፈናቃዮቹን የሚጎበኝ እና ለማቋቋም የሚሞክር አካል አለመኖሩ፣ ዛሬም ሰላምን የሚያደፈርሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው አለመቆጠባቸው እና በአካባቢው ሰላም ለማስከበር የሚንቀሳቀሰው የሰላም አስከባሪ ኃይል ቁጥር አነስተኛ መሆን አሁነም ዜጎችን እያሳሰቡ ያሉ ጉዳዮች ናቸው።
የመተከል ሪፖርት
በመተከል ዞን የተፈጠረውን ችግር ለማጥናት ወደ ዞኑ የተጓዘው የኢዜማ ልዑክ ቡድን ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ያለበትን ቡለን ወረዳን ለመጎብኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ወረዳው ለመጓዝ አልተቻለም፡፡ ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ሥራውን የጀመረው ኮማንድ ፖስት ስር ያለው የመከላከያ እዝ የመተከል ዞን፣ ወረዳዎችን እና ቀበሌዎችን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀጠና በማለት ለሶስት የከፈላቸው ሲሆን፤ አረንጓዴ ቀጠናው በአካባቢ ሚሊሽያ እየተጠበቀ መደበኛ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ቢጫ ቀጠናውን በሚሊሽያና በተመረጡ ልዩ ኃይሎች እያታገዘ ጸጥታውን እያስከበሩ መደበኛ የኑሮ እንቅስቃሴን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀይ ቀጠና፣ ነዋሪዎች የተገደሉበትና የተፈናቀሉበት አካባቢ በመሆኑ የነዋሪዎችን መደበኛ ሕይወት ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ ከኮማንድ ፖስቱ ኃኃፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት ለማወቅ ተችሏል፡፡ አካባቢው በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እዝ ስር ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህ አካባቢ ላይ ከመንግሥት አካላት ውጪ ያሉ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መሣሪያ የታጠቁ አካላት ከልዩ ኃይልና ከመደበኛ ፖሊስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህን ሰንሰለት ለመቁረጥ መከላከያ ስምሪት መጀመሩን ተረድተናል፡፡ ግጭት እንዲቀሰቀስ እያደረጉ ነው የተባሉ ልዩ ኃይል አባላት እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፖሊስ የተቀነሱ እና የተባረሩ አባላትም ችግር እየፈጠሩ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመተከል ዞን 181 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 44 ቀበሌዎች ወታደራዊ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸውና ቀይ ቀጠና ተብለው የተከለሉ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 22 ቀበሌዎች ላይ ጠንከር ያለ ወታደራዊ ኦፕሬሽን እየተካሄደ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡
በመተከል ዞን የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ከ126ሺህ ዜጎች በላይ የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከተፈናቃዮቹ መሀል 15ሺህ ዜጎች ብቻ ነው መንግሥት ወደ ቀዬያቸው ሊመልስ የቻለው፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተከስቷል፡፡ እየተሰጠ ያለው እርዳታም ለታለመለት የማኅበረሰብ ክፍል እየደረሰ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ከእርዳታው እየወሰዱ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ለመረዳት ችለናል፡፡ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ክፍተት እንዳለ ተረድተናል፡፡ የተከሰተውን ማኅበራዊና ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታትም ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋል፡፡ እርዳታው ለታለመላቸውና ተጎጂ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲደርስ ግን የተለየ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ መረጃ እያገኘ ያለው ከክልሉ መንግሥት አካላት ነበር፡፡ መረጃዎቹ ሀሰተኛ ሆነው ስለተገኙ በየቀበሌው ያለው ማኅበረሰብን ኮማንድ ፖስቱ በማነጋገር ላይ ይገኛል፡፡ መከላከያው ፀጥታውን ለማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በአቅሙ የሚቻለውን እያደረገ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ማጠቃለያ
1. በትግራይ ክልል፣ በቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልል መተከል ዞን እና በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እና የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊገነዘቡት ይገባል። በእነዚህ አካባቢዎች የምግብ እህል፣ የሕክምና መገልገያ ዕቃዎች እና መድሃኒት፣ አልባሳት እንዲሁም የንፅሕና መጠበቂያዎች ከፍተኛ እጥረት እንዳለ በመረዳት መንግሥትም ሆነ የተቀረው ኅብረተሰብ በእነዚህ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው እና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቅን ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ እና የዕለት ጉርሻቸውን ለማግኘት እየተቸገሩ የለሚገኙ ወገኖቻችን በአፋጣኝ የተቻለንን ሁሉ ድጋፍ በማሰባሰብ ለዜጎች ልንደርስላቸው እና አጋርነትንም ልናሳይ ይገባናል ስንል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
2. የመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝቡ በማድረስ በተለይ በትግራይ ክልል ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ውዥንብር እንዲያጠሩ እና በትግራይ ክልል፣ በቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል መተከል ዞን እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማሰባሰብ የሚደረገውን ጥረት በስፋት እንዲያግዙ ጥሪ እናስተላልፋለን።
3. መንግሥት እስካሁን ለዜጎች እየተደረጉ ያሉት ድጋፎች በቂ አለመሆናቸውን በመረዳት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለሕዝብ ለማድረስ ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርግ እና ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የዜጎችን ሕይወት የመታደግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
4. በትግራይ ክልል የተጠናከረ መደበኛ የፀጥታ መዋቅር በአፋጣኝ እንዲቋቋም እና የዜጎችን ሕይወት፣ ሰብዓዊ ክብር እና ንብረቶቻቸውን ከየትኛውም አካል ከሚመጣ አደጋ መከላከል የሚችልበት አቅም እንዲኖረው ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ እንጠይቃለን።
5. የመንግሥት የፀጥታ አካላት በተደጋጋሚ ንፁሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል በሚያስችል ደረጃ ራሳቸውን የሚያበቁበት ሥራ በአፋጣኝ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። አሁንም ቢሆን ጥቃት ሊደርስብን ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ከስጋታቸው ተላቀው ወደ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሕይወታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በፍጥነት ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
ከምርጫ 2013 ጋር በተያያዘ
ኢዜማ ከፍተኛ ሀገራዊ ፈይዳ አለው ብሎ ለሚያምንበት ለምርጫ 2013 ዝግጅት ሲያድርግ ቆይቶ ከሰኞ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በ3 ደረጃ ባወቀራቸው የዘመቻ መዋቅሮቹ የምረጡኝ ዘመቻውን ይጀምራል። በዚህ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት እንደ ሀገር ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ እና ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊወስዱ የሚችሉ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይለዩናል፣ የተሻሉ ናቸው ብለን ያዘጋጀናቸውን የመፍትሄ አማረጮች ይዘን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ እና ምረጡን ለማለት እንቅስቃሴ የምናደርግ ይሆናል።
በሚቀጥሉት 100 ቀናት በየወረዳው የተዘረጉት የዘመቻ መዋቅሮቻችን ምርጫ በሚደረግበት የሀገራችን ክፍል ሁላ የኢዜማን ሀሳቦች ለማስተዋወቅ ይንቀሳቀሳሉ። በክልል ደረጃ የተዘረጉት የዘመቻ መዋቅሮች እንደየክልሉ ሁኔታ በተለያየ መንገድ ኢዜማን ለማስተዋወቅ የሚንቀሳቀሱ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜማ በቀጣዩ ሳምንት ሁለት አበይት ክንውኖችን የሚያከናውን ይሆናል። የመጀመሪያው ክንውን በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የዓመቱ መካሄድ የሚኖርበት የፓርቲ ኮንፈረንስ አርብ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል። ኮንፈረንሱ ቀደም ብሎ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም መካሄድ በነበረበት ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከፍተኛ ስጋት የደቀነበት ወቅት በመሆኑ ተራዝሞ ነበር። የኢዜማ የፓርቲ ኮንፈረንስ ፓርቲው አባላትን ካደራጀባቸው የምርጫ ወረዳዎች አንድ ተወካይ የሚወከልበት እና ሦስት ዓመት አንዴ ከሚሰበሰበው የፓርቲው ጉባዔ ቀጥሎ ትልቁ ሥልጣን ያለው የፓርቲ አካል ነው። ኢዜማ ከተመሰረተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው ይህ ኮንፈረንስ የፓርቲውን ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ እና በጉባዔ የተመረጡ አካላትን የእስካሁን እንቅስቃሴ ሪፖርት በማዳመጥ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም በተጨማሪ ኢዜማ በቀጣዩ ምርጫ የሚወዳደርባቸውን ፖሊሲዎች እና ማኒፌስቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን የሚያፀድቅ ይሆናል።
ሁለተኛው አበይት ክንውን በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርጫ ዘመቻ ማስጀመሪያ ዝግጅት የካቲታ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ይደረጋል። በዚህ ዝግጅት ላይ ከመላው ሀገሪቱ ካሉት 435 የምርጫ ወረዳ መዋቅሮች የሚመጡ የፓርቲው የኮንፍረንስ አባለት ጨምሮ በአዲስ አባበ የሚገኙ አባለት እና ደጋፊዎቻችን የሚታደሙበት ይሆናል። በዚሁ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ከተማ የምትኖሩ አባላት እና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም ኢዜማ በቀጣዩ ምርጫ ይዟቸው የቀረቡትን የመወዳደሪያ ሀሳቦች መስማት እና ዕጩዎችን መተዋወቅ የምትፈልጉ የከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ በዚህ የምርጫ ዘመቻ መክፈቻ ክንውን ላይ እንድትካፈሉ ግብዣችንን እናቀርባለን።
ኢዜማ በሁሉም ደረጃ ለሚደረጉ የምርጫ ዘመቻ እንቅስቃሴዎች በየደረጃው ያሉ የፌደራል እና የክልል አስተዳደራዊ መዋቅሮች፣ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ ዘርፎች እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቀና ትብበር እንድታደርጉልን ስንል እንጠይቃለን።
የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.