የጁንታው ቡድን መነሻ አድዋ ያለው ኃይል መሰበሩ የጁንታው አከርካሪ መበጠሱን እንደሚያሳይ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ አስታወቁ

መከላያ ሠራዊቱ የሚቀረው ከጉድጓድ ውስጥ ያለውን ጁንታ አውጥቶ ለሕግ ማቅረብና ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ነጻ ማድረግ መሆኑንም የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት ትህነግ በምዕራብ ግንባር ድል እየሆነ እየፈረጠጠ ነው፡፡ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትናንትና ዛሬ ወሳኝ የሚባሉ አክሱም፣ አድዋና አዲግራትን አስለቅቋል፡፡ ባደረገው ኦፕሬሽንም በርካታ የጁንታውን ታጣቂ ኃይል ማርኳል፤ ደምስሷልም፤ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ እንዳሉት የትህነግ በርካታ ኃይል ተመትቷል፤ በርካታውም እጅ ሰጥቷል፡፡
ነጻ የወጡት አካባቢዎች ለተኩስ የማያመቹ፣ ትልልቅ የልማት ተቋማት ያሉባቸው፣ በርካታ የሕዝብ ቁጥር የሰፈረበትና ወደ መቀሌ በተለያዬ አቅጣጫ ለመሄድ የሚያስችሉ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በጁንታው መንጋጋ የነበሩትን ቦታዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፈልቅቆ ማውጣቱ ለቀጣይ ድል ወሳኝ ናቸውም ብለዋል፡፡
ስግብግቡ የትህነግ ቡድን ከመነሻውም የሕዝብን መብት ረግጦ የራሱን የስልጣን ጥቅም የሚያረጋግጥ እንደሆነ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ጠቅሰዋል፤ የሕዝቦች ልማትና ደኅንነት የትህነግ አጀንዳ እንዳልነበርም አንስተዋል፡፡ ለዚህም የመከላከያ ሠራዊቱ ነጻ ያወጣቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡
ትህነግ ሲፈረጥጥ በርካታ ድልድዮችን እያፈረሰ፣ መንገዶችን እያፈረሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የአክሱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያውንም ከጥቅም ውጭ አድርጎ መሸሹንም ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡
የጁንታውን ኃይል ከሕዝብ ነጥሎ በመምታት የሕግ የበላይነትን ማስከበርና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ሰላም ማድረግ የሠራዊቱ ግዳጅ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ የጥፋት ቡድኑን ሲመታ የአካባቢው ኅብረተሰብ እንዳይጎዳና ንብረት እንዳይወድም በከፍተኛ ጥንቃቄ ኦፕሬሽኑን እየፈፀመ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሜጄር ጄኔራል መሀመድ እንደተናገሩት አክሱም ከተማ የቱሪስት መዳረሻና ትልልቅ ቅርሶች ያሉባት ከተማ ናት፤ አድዋም ሀገር ሊወሩ የመጡ ጠላቶችን ቀደምት አባቶች አሳፍረው የመለሱበት ታሪካዊ ሥፍራ ነው፤ እናም ሕዝቡና ተቋማት እንዳይጎዱ ኦፕሬሽኑ በጥንቃቄ ተፈጽሟል፡፡
ዘረኝነትን እስከ መንደር የከፋፈሉት የጁንታው ቡድን መነሻ አድዋ ያለው ኃይል መሰበሩ የጁንታው አከርካሪ መበጠሱን ያሳያል ነው ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ፡፡ “ይሄም ለቀጣይና ለመጨረሻው ምዕራፍ ውጊያችን ወሳኝ ነው” ብለዋል፡፡
የጁንታው በርካታ ኃይል መመታቱን፣ ከበባ ውስጥ መግባቱንና ከኅብረተሰቡ መነጠሉንም ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀረው ከጉድጓድ ውስጥ ያለውን ጁንታ ከገባበት ጉድጓድ አውጥቶ ለሕግ ማቅረብና ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ነጻ ማድረግ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ትናንትና እና ዛሬ መከላከያ ሠራዊቱ የያዛቸው ስፍራዎች ለቀጣይ ድል ወሳኝ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

free web page hit counter
free web page hit counter