ብልጽግና ፓርቲ ለመቀየር የሚያመነታበት በኦሮሞ ክልል ያለው አስከፊ ገጽታ #ግርማካሳ

1
ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን በኢሕአዴግ መንግስት ሁለት የህዝብ ቆጠራዎች ተደርገዋል፡፡ የመጀመሪያው የተደረገው በ1986 ዓ/ም ሲሆን ሁለተኛው የተደረገው በ1999 ዓ/ም ነው፡፡ እነዚህ የሕዝብ ቆጠራዎች የራሳቸው ችግሮች እንደነበራቸው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም እስከነ ችግሮቻቸው፣ ያሉት ኦፊሴላዊ ሪፖርቶች እነርሱ ብቻ በመሆናቸው፣ እርሱን ተጠቅመን ነው መነጋገር የምንችለው፡፡
በ1999ኙ ሪፖርት፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመለየት በከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎችን ቁጥር አልተዘረዘረም፡፡ ስለሆነም በከተሞች ያለው ስብጥር ለማየት የ1986ቱ ሪፖርት ተብቻ ለማለየት እንገደዳለን፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተለወጡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች የአማርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ቁጥር በብዙ እጥፍ የጨመረ ስለመሆኑ አዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖር ሰው ያጣዋል ብዬ አላስብም፡፡
በዚህ ሪፖርት 17 ከተሞች ተመርጠዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ፡
  • በአምቦ፣ በመቱና በጊምቢ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ ነዋሪዎች ከግማሽ በላይ ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በአምቦ ከ42% በላይ፣ በጊምቢ ደግሞ ከ39%፡ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አይደለም፡፡
  • በ 5 ከተሞች፣ ጂማ፣ ወሊሶ፣ ፍቼ፣ አሰበ ተፈሪና ሰበታ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ ከአንድ ሶስተኛ በታች ሲሆኑ በ 9 ከተሞች ከአንድ አራተኛ በታች ናቸው፡፡ሰሞኑን የጽንፈኞች ስለባ በሆነችው በአርሲ ኔጌሊ 3% ብቻ ናቸው፡፡ በሻሸመኔ ደግሞ 13%፡
  • ከአምቦ፣ መቱና ጊምቢ በስተቀር በሁሉም የተጠቀሱ ከተሞች አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ ከግማሽ በላይ ናቸው፡፡
  • በአስር ከተሞች ፣ ናዝሬት፣ ጂማ፣ ሻሸመኔ፣ ደብረዘይት፣ አሰላ፣ ወሊሶ፣ ሞጆ፣ ፍቼ፣ መተሃራና ወለንጭቲ አማርኛ ተናጋሪዎች ከ2/3ኛ በላይ ናቸው፡፡
እነዚህ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት፣ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ደግሞ በጥቂቱ በሚኖሩባቸው ከተሞች፣ አሁን ባለው የጎሳ አወቃቀር፣ የጎሳ ፈዴራሊዝምና፣ የጎሳ ሕገ መንግስት ምክንያት ፣ አብዛኛ ነዋሪዎች በከተማቸው መጤና ሰፋሪ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት፡፡ በከተሞቹ ያሉ ፖሊሶች፣ ተመርጠው ሆነ ተቀጥረው የሚሰሩት የቀበሌ ሃላፊዎችና የከተሞቹ መስተዳደር ሰራተኞች፣ በሙሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
ያ ብቻ አይደለም አብዛኞቹ ፖሊሶችና አመራሮች ከከተሞቹ ነዋሪዎች መካከል የወጡ አይደለም፡፡ ከሌላ ቦታ የመጡ፣ የከተሞችን ህዝብ ስነልቦና የማይረዱ፣ ለነዋሪው ክብርና ፍቅር የሌላቸው፣ በሹመት በኦህዴድ/የብልጽግና ኦሮሞ ክልል ቅርንጫፍ ከፍተኛ አመራሮች በቀጥታ የተሾሙ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ጽንፈኞቹ በአንዳንድ ከተሞች ጥፋት ሲፈጽሙ ፖሊሶቹና የመንግስት ሃላፊዎች ዝም ብለው ሲመለከቱ፣ አንዳንድ ቦታም መሳሪያ በማቀበል ከጽንፈኞች ጋር ሲተባበሩ የነበሩት፡፡
ለምሳሌ የአሰላ ከተማን ከንቲባ ብንወስድ፣ ወ/ሮ ዘይነባ ይባላሉ፡፡ የጃዋር ተከታይ ጽንፈኛ የኦህዴድ/ብልጽግና አመራር ናቸው፡፡ የአሰላ ከተማ ነዋሪ አልነበሩም፡፡፡ ከሌላ ቦታ መጥተው ነው በአሰላ ከንቲባ የተደረጉት፡፡
እኝህ ከንቲባ በአሰላ ከተማ ሕዝብ በጣም የማይወደዱ ከንቲባ ናቸው፡፡ አብዛኛው የአሰላ ከተማ አማርኛ ተናጋሪንና የኦርቶዶስክ እምነት ተከታይ ማህበረሰብን ፣ ከአሰላ ውጭ ጽንፈኞች ጭነው በማስገባት፣ ሲያስጨንቁ የነበሩ ናቸው፡፡ የመስቀል ደመራና ጥምቀት የመሳሰሉ በዓላትን አታከብሩም በሚል የነወ/ሮ ዘይነባ ቄሮዎች ባደረጉት ትንኮሳ ብዙ ጊዜ በአሰላ አለመረጋጋት የተከሰተበት ሁኔታም ነበር፡፡
እንግዲህ በኦሮሞ ክልል ያለው አሳዛኝና አፓርታይዳዊ ገጽታ ይሄን ነው የሚመስለው፡፡ አዎን የብልጽግና ፓርቲ ይሄንን አፓርታይዳዊ አሰራር ለመቀየር ነው እያመነታ ያለው፡፡ የኦሮሞ ክልል ከተሞች ከራሳቸው ከነዋሪዎቻቸው በተወጣጡ ጥበቃና ፖሊስ፣ ራሳቸው ከከተማ ነዋሪዎች በተመረጡ ከንቲባዎች ፣ የከተማዎቹ ነዋሪዎች በሚፈልጉት ቋንቋ እንዲማሩና የመንግስት አገልግሎት እንዳያገኙ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ እንቅፋት የሆነው በቀዳሚነት የብልጽግና ፓርቲ ራሱ ነው፡፡
በጥቅምት 2012 የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ነበሩ፡፡ የኦሮሞ ክልል መሪ ደግሞ አቶ ሺመልስ አብዲሳ፡፡ በሰኔ 2012 እነዚሁ አመራሮች እያሉ ነው የጥቅምቱ እልቂት በከፋ ሁኔታ የተደገመው፡፡ መሪዎቹ ነዋሪዎችን እንደሚጠብቁ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ግን ቃላቸውን አላካበሩም፡፡
እነ ሻሸምኔ አሁንም በላያቸው ላይ ሌሎች እየተሾሙባቸው፣ የነዚህ ከተሞች ነዋሪዎች መብት እየተረገጠ፣ ከተሞቹ የኦሮሞ ብቻ ናቸው በሚል በአገራቸው ዜጎች እንደ መጤና ሰፋሪ እየተቆጠሩ፣ የዘር ፖለቲካውና የዘር አሰራሩ እየቀጠለና በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ አንደኛ ሌሎች ሁለተኛ ወይም ውራ እየተባሉ፣ በጥቅምት 2012 የታየው ሰቆቃና እልቂት በሰኔ 2012 በከፋ ሁኔታ እንደተደገመው፣ ከስድስት፣ ሰባት ወር በኋላ ተመሳሳይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አይፈጸምም ለማለት እንዴት እንችላለን ?
ምንም የተለወጠ መሰረታዊ ነገሮች በሌሉበት፣ ጥቂት ታች ያሉ አመራሮችን ብቻ መቀየሩ፣ በምትካቸው ሌሎች ( ምንአልባት ከተተኩት የማይሻሉ) ሃላፊዎች መሾሙና የነ ዶር አብይን መልካም ንግግሮችንና ተስፋዎችን መስማቱ ለሕይወታችን ዋስትና በጭራሽ አይሰጠንም፡፡ ጥቅምት 2012 የሆነውን ሰኔ 2102 እንዳይደገም ያደረገ አመራር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ካልተደረገ ማመን እጅን እሳት ላይ አድርጎ አያቃጥለኝም ማለት ነው፡፡
ዶር አብይ አህመድ “ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ መባባል ያተረፈልን ነገር ድህነትና እከክ ነው” ያሉት አባባል አለ፡፡ ትክክለኛ አባባል ነው፡፡ ይኸው አየነው እኮ፡፡ የሻሸመኔ፣ የዝዋይ፣ የኮፈሌና ሌሎች በኦሮሞ ክልል የተፈጸሙ ዉድመቶች፣ እልቂቶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች  ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡
እባክዎትን ዶር አብይ አህመድ፣ ከፕሮዘዳንት ፖል ካጋሜ ተመረው፣ እርስዎ ራሱ በአደባባይ የተናገሩትን ለእከካችንን ድህነታችን ምክንያት የሆነውን የጎሳና የዘር ፖለቲካን ያግዱልን፡፡ የዘር አከላለንም ያፍርሱልን፡፡ የዘር ሕገ መንግስቱ እንዲቀየር መንገዱን ያመቻቹልን፡፡ ከምርጫ በኋላ አይደለም፡፡ አሁን፡፡
ይሄን ለማድረግ በርግጥ ከተነሱ ግርማ ካሳ አይኑን ሳያሽ ከጎንዎት ይሰለፋል !!! እኔ ብቻ ሳልሆን ይመኑኝ ከ80 እስከ 90% በላይ የሚሆነው የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደግፍዎታል፡፡

1 Comment

  1. ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ ለምሳሌ ከማል ሶይደር ሚስት የቷ ናት ትሉና ኦኬ ስንለዉ አይመጣም እና እሱ ቢስተካከልልን እላለው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

free web page hit counter
free web page hit counter